ሰዎች ሌሎች ሰዎችን በሀሰት ከሰው የማስቀጣት፣ ያልተገባ ጥቅም የማግኘት ወይም ሀሰተኛ ማስረጃ በማቅረብም ሆነ በሀሰት ቀርቦ የመመስከር አዝማሚያ በስፋት ይስተዋላል። በተለይ በአሁኑ የቴክኖሎጂና የሉላዊነት ዘመን ሀሰተኛ ክስና ማስረጃ ማቅረብ ቀላልና የተለመደ እየሆነ መጥቷል። እነዚህ ተግባራት በግለሰቦች መብትና ጥቅምም ሆነ በአጠቃላይ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም። በመሆኑም ሀሰተኛ ክስና ማስረጃ በወንጀል የሚያስጠይቁ ድርጊቶች ተደርገው ተደንግገዋል።
በአንፃሩ ደግሞ በሀሰተኛ ክስና ማስረጃ ሰበብ የዜጎችን የመናገርና ሀሳብን ወይም አስተያየትና ጥቆማ መስጠትን ወይም ትችት ማቅረብና ይጣራልኝ ብሎ ለሚመመለከተው አካል አቤቱታ ማቅረብን ሁሉ የህግ ተጠያቂ በማድረግ የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት መገደብ ተገቢ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ባለጉዳዮች በቅንነት በመጠራጠር የሚያቀርቡት የክስ አቤቱታ በሂደት በሚመለከተው ባለስልጣን መጣራትና መረጋገጥ ያለበት በመሆኑ ነው፡፡
ተከሳሾችም በተከሰሱበት ጉዳይ የመካድ፣ የማመንና ዝም የማለትና ንጹህ ሆኖ የመገመት መብት ያላቸው በመሆኑ በቅንነትና ለፍትሕ ቀናኢ በመሆን የሚቀርቡ ጥቆማዎች ወይም አቤቱታዎች እንደ ሀሰት መቆጠር የለባቸውም፡፡ በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ፅሑፍ ስለበሀሰት መወንጀል እና የሀሰተኛ ምስክርነት ምንነት፣ ስለሚያደርሱት ጉዳትና የሚያስከትሉት የሕግ ተጠያቂነት ይዳሰሳል።
የሀሰተኛ ክስና ማስረጃ ምንነት
በሕጎቻችን ስለሀሰተኛ ክስም ሆነ ሀሰተኛ ማስረጃ ቁርጥ ያለ ትርጉም ተሰጥቷቸው አናገኝም። ሆኖም ለወንጀሎቹ መቋቋሚያነት የተዘረዘሩትን ፍሬ ነገሮች መሰረት በማድረግ፡- ማንም ሰው ወንጀል እንዳልፈፀመ እያወቁ እንዲከሰስ እና በወንጀል እንዲቀጣ ወይም እንዲታሰር እንዲሁም በፍትሐ ብሔር በማያስከስስ ጉዳይ ከሶ የገንዘብ ጥቅምን ለማሳጣት ወይም ለራስ ወይም ለሌላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በሀሰት መወንጀል ወይም መክሰስ ሲባል አንድን ተከራካሪ ወገን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት በማሰብ ፍርድ ቤት ቀርቦ በሀሰት የምስክርነት ቃል መስጠት ወይም በማንኛውም መንገድ እውነተኛ ያለሆነ ማስረጃ ማቅረብ ሀሰተኛ ማስረጃ ብሎ መግለፅ ይቻላል።
ሀሰተኛ ክሶችና ማስረጃዎች በህግ ፊት ያላቸው ውጤት
ሀሰተኛ ክሶች በሀሰት ስለመቅረባቸው ሲረጋገጥ ክሱን ያቀረቡ ሰዎች በወንጀል ወይም በፍትሐብሔር የመጠየቃቸው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የቀረበው ክስ ምንም አይነት ህጋዊ ውጤት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህም ማለት የቀረበው ክስ የክስ ምክንያት ስለማይኖረው ወይም ደግሞ የቀረበው ክስ ከተጠየቀው መብትና ጥቅም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው ከሆነ ወይም የተጣሰ ህግ ከሌለ አለያም በክሱ ላይ የተመለከተው ፍሬ ጋር ሊፈጸም የማይችል ከሆነ ክሱ ውድቅ ይደረጋል (ይሰረዛል) (የፍትሐብሔር ህግ ስነ-ስርዓት ቁጥር 33(2))፣ 229 እና 231፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 18))፡፡
ነገር ግን በዚህ ክስ መነሻ ውሳኔ ከተሰጠና የቀረበው ክስ ወይም ማስረጃ ወይም ሁለቱም ሀሰተኛ ስለመሆናቸው የታወቀው ከፍርድ ውሳኔ በኋላ ከሆነ ውሳኔው እንደገና የሚከለስበት ወይም በይግባኝ የሚታይበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል (በወንጀል ጉዳይ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕጉን ረቂቅ አለመፅደቅ እንደተጠበቀ ሆኖ)።
ሀሰተኛ ክስና ማስረጃ የሚያደርሱት ጉዳት
1. በግለሰቦች ጥቅሞችና መብቶች ላይ፡- በሀሰተኛ ክሶችና ማስረጃዎች መሰረት የሚሰጡ የፍርድ ውሳኔዎችና እርምጃዎች የባለጉዳዮቹን ህይወት፣ ነጻነትና ንብረት የሚመለከት ስለሆነ ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሞራላዊ ጉዳት ያስከትላል።
2. በማህበረሰቡ ላይ፡- ማሀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ አለመተማመንና የገበያ ስርዓቱ የተዛባ መሆን እንዲሁም የወንጀል ሰለባ መሆንና እሴት አልባ መሆን።
3. በፍትህ ስርዓቱ ላይ፡- ተአማኒነት የሌለው የፍትህ ተቋም (የፍርድ ቤቶችና የፍትህ ተቋማት ዓላማ እውነትን ከሀሰት መለየት ስለሆነ)፡፡
4. በመንግስትና በሀገር ላይ፡- አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚና ልማት ውድቀት፣ የሐገር ቀጣይነት አደጋ ውስጥ መውደቅ ሊያስከትል ይችላል።
ሀሰተኛ ክስና ማስረጃ የሚያስከትሉት ተጠያቂነት
በሀሰተኛ ክሶችና ማስረጃዎች ምክንያት የሚመጡትን ተጠያቂነቶች ለመወሰን ቢያንስ ሶስት ነገሮች መሟላት ያለባቸው ሲሆን እነዚህም፡-
1. ሀሰተኛ መግለጫው ወይም የክስ አቤቱታው በቃለ-መሀላ (የፍ/ስ/ስ/ህ ቁጥር 92) ወይም በማንኛውም አይነት ማረጋገጫ ተደግፎ ለዳኝነት ወይም የዳኝነት ነክ ስልጣን ላላቸው አካላት (አስተዳደራዊ፣ ወታደራዊ፣ የሸሪኣ ወይም በአዋጅ የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው አካላት) መቅረብ፤
2. መግለጫው ወይም አቤቱታው ወይም ማስረጃው ከቀረበው ክርክር ጋር ያለው ግንኙነት እና፤
3. ከሳሹ ወይም ቃል ሰጨው ወይም ማስረጃ አቅራቢው ለማሳሳት ወይም በሀሰት ለመክሰስና ጥቅም ለማግኘት ያለው ሀሳብ (በተለይ የወንጀል ተጠያቂነትን በሚመለከት) ሲሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ “የዳኝነት ወይም የዳኝነት ነክ ስልጣን ያለው አካል” የሚለው አገላለጽ ብዙ ጊዜ አሻሚና አከራካሪ በመሆኑ ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወገን ጉዳዩ በፖሊስና በዐቃቤ ህግ ፊት የሚሰጡ ሀሰተኛ ቃሎችን ወይም ማስረጃዎችን አያካትትም የሚል ክርክር ሲኖር በሌላ በኩል ደግሞ “ሀሰት” በፍርድ ሂደት (በዳኝነት አካልም) ተሰጠ በሌላ አስተዳደራዊ ወይም በማንኛውም ባለስልጣን ፊት ቢሰጥ ለውጥ የለውም የሚል ክርክር ይቀርባል፡፡ ከዚህ አንጻር ሁለተኛው ክርክር ሚዛን የሚደፋ ቢመስልም በፍርድ ቤቶች በኩል ግን ብዙም ተቀባይነት ያለው አይደለም። የዳኝነት ስራ የሚያከናውን የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ከሦስቱም የመንግስት አካላት ሕግ ተርጓሚው ወይም መደበኛዉን ፍርድ ቤት የሚያመለክት ሲሆን የዳኝነት ነክነት ስራ የሚካሄድበት ደግሞ በዳኝነት መልክ ወይም መሰል ሁኔታ ክርክር የሚሰማበት፣ የቀረበ ማስረጃ ተመዝኖ ድምዳሜ ላይ የሚደረስበትና የበኩሉን ውሳኔ የሚሰጥበት ተቋም የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሆኑት ተቋማት እንደ ግብር ይግባኝ ጉባኤ፣ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ፣ የግልግል ተቋማትና ሌሎች መሰል ከፊል የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸዉ አስተዳደራዊ ተቋማት መሆናቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 23 በመዝገብ ቁጥር 153228 ላይ ከሰጠዉ አስገዳጅ የህግ ትርጉም መረዳት ይቻላል፡፡
በመሆኑም ሀሰተኛ የክስ አቤቱታና ማስረጃ ማቅረብ የሚከተሉትን የህግ ተጠያቂነቶች ያስከትላል፡-
1. የፍትሐብሔር ተጠያቂነት፡-
በሀሰተኛ ክስና ማስረጃው ምክንያት የደረሰ ቁሳዊ ወይም ሞራላዊ ጉዳት ሲኖር በከውል ውጭ ኃላፊነት ህግ መሰረት በደረሰው ጉዳት ልክ ተጠያቂነትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተጨማሪም በሀሰተኛ ክሱ ወይም ማስረጃው ምክንያት የተበላሸውን ወይም የጠፋውን ነገር ወደነበረበት እንዲመልስ ሊደረግ ይችላል፡፡
2. የወንጀል ተጠያቂነት፡-
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 453 (1) መሰረት የዳኝነት ወይም የዳኝነት ነክ ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ ምስክር ሆኖ የቀረበ ማንኛውም ሰው ማንኛውንም ተከራካሪ ወገን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት አስቦ ሀሰተኛ ምሥክርነት ወይም የልዩ አዋቂነት አስተያየት የሰጠ እንደሆነ ወይም እውነቱን የደበቀ እንደሆነ፣ ያቀደው ሐሳቡ ከግቡ ባይደርስለትም እንኳን በቀላል አስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን በዚሁ አንቀፅ ንኡስ 2 መሰረት ደግሞ ይህ ምስክር እውነቱን ለመናገር ምሎ ወይም ማረጋገጫ ሰጥቶ በለይም የፈለገው ውጤት በሙሉ ወይም በከፊል ያሳካ እንደሆነ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ያስቀምጣል፡፡
በሌላ ሁኔታ ደግሞ ጉዳዩ የወንጀል ጉዳይ ከሆነና ተበዳዩ በሀሰተኛ መስካሪው ድርጊት ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት እንደሆነ ወይም ከ10 ዓመት ፅኑ እስራት በላይ ተፈርዶበት እንደሆነ የተመሰከረበት ሰው በስህተት በተወሰነበት ቅጣት ልክ ሀሰተኛ መስካሪውም ሊወሰንበት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉት ሀሰተኛ ምስክርነቶች ብቻ ሳይሆኑ በፅሑፍ የሚሰጡ ትርጉሞችም ጭምር ናቸው፡፡ በመሆኑም አንቀጽ 453(3) መሰረት በዳኝነት ወይም በዳኝነት ነክ ስልጣን ባለው አካል በሚወሰን ጭብጥ አግባብነት ባለው ፍሬ ነገር ሀሰተኛ ትርጉም የሚሰጥ ማንኛውም ተርጓሚ ወይም አስተርጓሚ እንደ አግባቡ ለሀሰተኛ ምስክርነት የተመለከቱት ቅጣቶች ተፈጻሚ ይሆኑባቸዋል፡፡
ከላይ የተመለከትናቸው ቅጣቶች ሀሰተኛ ምስክርነትን የሚመለከቱ ሲሆኑ ሰውን ባልሰራው ወንጀል መክሰስም የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል። በዚህም መሰረት በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 447 ስር በሐሰት ሰዉን መወንጀል ወይም መክሰስ ወንጀል መሆኑን በግልጽ ደንግጎታል።
በመሆኑም የሌላዉን ሰዉ ንፅህና እያወቁ ባልፈጸመው ወንጀል በባለስልጣን ዘንድ መወንጀል ወይም በማናቸውም ዘዴ በተለይም ንፁህ የሆነውን ሰው ባልፈፀመው ወንጀል እንዲከሰስ አቅዶ ወንጀል እንደተፈፀመ በማስመሰል ወይም የራስን ስም ሳይገልፁ ትክክለኛ ባልሆነ ውንጀላ ሌላዉን ሰው መክሰስ ከ5 አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና በገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ይሁን እንጂ በሀሰት በቀረበው ውንጀላ ምክንያት በንጹህ ሰዉ ላይ ከላይ ከተመለከተዉ (ከ5 አመት በላይ ፅኑ እስራት) የበለጠ ቅጣት የተላለፈ እንደሆነ በሀሰት የወነጀለው ወይም የከሰሰው ሰው ተወንጃዩ ሰው ላይ በተላለፈው ቅጣት ልክ የሚቀጣ ይሆናል፡፡
በፍርድ ቤት እውነት እንዲናገር የታዘዘ ተከራካሪ ወገንም ቢሆን ሀሰተኛ ቃል ከሰጠ ተጠያቂነቱ አይቀርለትም። በመሆኑም ተከራካሪው ወገን ጥቅሙን ለማስከበር ከሚል መነሻ ካልሆነ በስተቀር እያወቀ ፍትሕን ለመዛባት ሀሰተኛ የሆነውን ቃል ለፍርድ ቤት ከሰጠ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 452 መሰረት ከቀላል እስራት ጀምሮ እንደወንጀሉ ክብደት ከ3 እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል።
ሀሰተኛ ምስክርነት መስጠት በወንጀል ማስጠየቁ የማይቀር ቢሆንም እድራጊው ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በራሱ ነፃ ፈቃድ ተነሳስቶ ቃሉን ቢቀይርና በሀሰት የተመሰከረበትን ሰው ከመቀጣት ያዳነው እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን እንደሚያቀልለት ወይም እስከነ ጭራሹ ቅጣቱን በመተው በተግሳፅ ብቻ ሊያልፈው እንደሚችል በአንቀፅ 454 ስር ተደንግጓል።
3. አስተዳደራዊ ተጠያቂነት፡- ይህም የዲሲፕሊን ቅጣትን ጨምሮ የገንዘብ ቅጣት፣ ከስራ መታገድ ወይም እስከ መሰናበት የሚያደርስ ሊሆን ይችላል፡፡
እነዚህ የቅጣት ዓይነቶች በአንድ ጊዜ ሊፈጸሙ የሚችሉ ሲሆን አንዱ የቅጣት እርምጃ ሌላውን አያስቀረውም፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት