ለሃብታቸው መነሻ ምንጩን ማቅረብ የሚችሉ ሁሉ አይፈሩም፤ ምንጩ የማይታወቅ ሃብት በሙሉ ህገወጥ ነው። ህገ ወጥነትን አይዋጋም የሚባል መንግስት፣ ሌብነትና ሌቦች ላይ ለመዘመት ህግ ሲያዘጋጅ የሚፈሩና ከፍርሃት በመነሳት የሚንጫጩ የጉዳይ ዋና ተዋንያኖች ካልሆኑ በቀር አጥንቱን የሚጋጠው ህዝብ አይደለም….
“በኢትዮጵያ ሌብነት ወይም ሙስና የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል” የሚለው ዜና አያከራክርም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሌብነት፣ ሌቦች ” ሲሉ የሚጠሩት ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ዋና የመንግስት ተዋንያን ያሉበት እንደሆነ ቢጠቆምም በዋናነት ግን ከውጭ ምንዛሬ አጠባ ጋር ሰፊ ቁርኝት እንዳለው ይታወቃል። በዚሁ ምክንያት ከውጭ አገር ምንዛሬ እየወሰዱ በውጭ ባንኮች እያስቀመጡ አገር ውስጥ ከዘረፉት ሃብት ላይ በኢትዮጵያ ብር እየከፈሉ (ሃዋላ እየሰሩ) ሃብት ያከማቹ ዒላማ ሆነዋል።
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ እንደ ችቦ የቆሙ ህንጻዎች ባለቤቶቻቸውን “ከየት አመጡዋቸው?” የሚል ጥያቄ በየአቅጣጫው ስም ሳይቀር እየተጠቀሰ ሲነሳባቸው ነበር። ለአንዳንድ ባለሃብቶችና ሃብታቸው ህዝብ ስም እየሰየመ ሲያሽሟጥጥ በአደባባይ መስማት የተለመደ ነው።
በኢትዮጵያ ከጸጥታ ችግር እኩል ሌብነት አሳሳቢ በመሆኑ በ2015 ዓ.ም ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል። ኮሚቴው ህዝብ ጥቆማ እንዲያደርግ ለህዝብ በይፋ ባደረገው ጥሪ መሰረት በሺህ የሚቆጠር መረጃዎች እንደደረሱት ተሰምቷል። ከህግና ፍትህ አካላት በኩል ደግሞ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሙሉ ህግ እንደሌለም ሲያስታውቁ ነበር። ሰሞኑን የሚዲያዎች ርዕስ የሆነውና ጫጫታ ያስነሳው ረቂቅ አዋጅ ለዚሁ ተግባር ተብሎ እንደተዘጋጀ እየተጠቆመ ነው።
በአንድ ወቅት የፌደራሉ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር በሌብነት የተገኘ ሃብት ላይ እርምጃ ለመውሰድ፣ ሃብቱንም ለመውረስ የሚያስችል የህግ ክፍተት እንዳለ ማስታወቃቸው ይታወሳል። በተደጋጋሚ መንግስት እርምጃ መውሰድ የማይችል ራሱ ሌባ እንደሆነ የሚወቅሱ ብዙ ናቸው።
አሁን ላይ የህጉን መርቀቅ ተከትሎ “እንዴት ይሆናል? ይህ አግባብ አይደለም” በሚል ተቃውሞ በማሰማት ጫጫታ የጀመሩት ክፍሎች ህጉ የመንግስትን ክንድ ለማፈርጠም እንደተዘጋጀ እየገለጹ ቢሆንም። ሌብነት ላይ ያለው የጥቆማ ሥርዓቱ የላላ መሆን የወንጀል ምርመራና ክስ ሥራ በመረጃና በማስረጃ ላይ የተደገፈ እንዳይሆን ማድረጉ፣ የተመዘበረና ከአገር የወጣ ሀብት ማስመለስ ላይ አጥጋቢ ሥራ አለመከናወኑ ለረቂቁ መዘጋጀት ምክንያት እንደሆነ ተመልክቷል።
“ሌብነትን ከወሬ በዘለለ አይዋጋም” በሚል የሚታማው መንግስት ባቀረበው ጥሪ መሰረት ህዝብ በሺህ የሚቆጠር ጥቆማ አቅርቧል። እናም ‹‹ምንጩ ያልታወቀ ንብረት አፍርቷል ተብሎ የተጠረጠረ ሰው፣ ንብረቱን ያፈራው ከውጪ በተላከለት ገንዘብ ነው የሚል ከሆነ፣ ግለሰቡ ገንዘቡ በሕጋዊ መንገድ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያለፉ ግብይቶች ወይም ክፍያዎች ስለመሆናቸው በተገቢው የባንክ ደረሰኝ አስደግፎ ማቅረብ የሚገባው ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ያለው ግን እንደ ምንጩ ያልታወቀ ገቢ ተደርጎ የሚቆጠርና የሚወረስ ይሆናል››። ከስር ሪፖርተር የጻፈውን እንዳለ አትመነዋል።
- በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት የመውረስ ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል
- አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ 10 ዓመት ወደኃላ ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል
ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው፣ ንብረት በመንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ድንጋጌ የያዘ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
ረቂቅ አዋጁ ‹‹የንብረት ማስመለስ አዋጅ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጀመሪያ ንባብ ተካሂዶበታል።
የረቂቁ ስያሜ ‹‹የንብረት ማስመለስ አዋጅ›› እንዲሆን የተመረጠበት ምክንያት ወንጀል የሚለው ቃል ከገባ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን፣ እንዲሁም ወንጀልን ማቋቋም አስፈላጊ ሳይሆን ሲቀርና በወንጀል ኃላፊነት የማይረጋገጡ ንብረቶች በሚኖሩበት ወቅት ንብረቶችን ለማስመለስ አያስችልም ተብሎ በመታመኑ እንደሆነ ረቂቅ አዋጁን ለማብራራት የቀረበው አባሪ ሰነድ ያስረዳል።
የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎችና አባሪ የተደረገው ማብራሪያ ሰነድ እንደሚያስረዱትም፣ መንግሥት ንብረትን ለማስመለስ ሲል በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ንብረቶችን ሊወርስ ይችላል። እነዚህም መንገዶች፣ ‹‹ምንጩ ያልታወቀ ንብረት መውረስ››፣ ‹‹በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ መውረስ›› እና ‹‹በጥፋተኝነት ላይ የተመሠረተ›› መውረስ ናቸው።
በረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ መሠረት፣ ማንኛውም ሰው ምንጩ ያልታወቀ ንብረት አፍርቷል ተብሎ ንብረቱ ሊወረስ የሚችለው፣ ግለሰቡ ያለው ንብረት ወይም የኑሮ ደረጃው አሁን ባለበት ወይም አስቀድሞ በነበረበት ሥራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኘው ወይም ሲያገኝ ከነበረው ሕጋዊ ገቢ ጋር የማይመጣጠን ሲሆንና የንብረቱን ወይም የኑሮ ደረጃውን ምንጭ በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ የወንጀል ጥርጣሬ ሲኖር ነው።
ይህ ሁኔታ መኖሩ ሲታወቅ ወይም ዓቃቤ ሕግ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖረው የፍትሐ ብሔር ክስ መመሥረት የሚችል ሲሆን፣ ክሱ የቀረበበት ሰው ንብረቱ ወይም የኑሮ ደረጃው በሕጋዊ መንገድ የተገኘ መሆኑን ጉዳዩን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት አስረድቶ ማረጋገጥ እንደሚኖርበት ረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ያመለክታል።
ይህም ማለት ምንጩ ያልታወቀ ንብረት መኖሩን ለፍርድ ቤት የማስረዳት ወይም የማረጋጥ ሸክም የከሳሽ ዓቃቢ ሕግ ሳይሆን ምንጩ ያልታወቀ ንብረት አለው ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ ወይም ሕጋዊ ሰው እንደሚሆን የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።
ረቂቅ አዋጁን ለማብራራት የቀረበው አባሪ ሰነድም ንብረት ማስመለስና መውረስ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች የሚዘረዝሩ አንቀጾችን ይዟል። በዚህም መሠረት ምንጩ ያልታወቀ ንብረት የሚወረስበትን ሁኔታ አስመልክቶ የሚከተለውን ማብራሪያ አስቀምጧል።
‹‹ምንጩ ያልታወቀ ንብረት አፍርቷል ተብሎ የተጠረጠረ ሰው፣ ንብረቱን ያፈራው ከውጪ በተላከለት ገንዘብ ነው የሚል ከሆነ፣ ግለሰቡ ገንዘቡ በሕጋዊ መንገድ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያለፉ ግብይቶች ወይም ክፍያዎች ስለመሆናቸው በተገቢው የባንክ ደረሰኝ አስደግፎ ማቅረብ የሚገባው ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ያለው ግን እንደ ምንጩ ያልታወቀ ገቢ ተደርጎ የሚቆጠርና የሚወረስ ይሆናል››።
ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ክስ በሚቀርብበት ጊዜና የንብረቱ የገንዘብ መጠን በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ የተደነገገ ሲሆን፣ ክስ የሚቀርብበት ጊዜን አስመልክቶም አዋጁ ከሚፀድቅበት ጊዜ አንስቶ ወደ ኃላ 10 ዓመት ተመልሶ ተፈጻሚ እንደሚሆን ረቂቅ አዋጁ ይጠቅሳል።
አዋጁ ወደኋላ 10 ዓመት ተመልሶ ተፈጻሚ በሚሆንበት ወቅት ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን ለመክሰስ መሠረት የሚሆነው ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን አምስት ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ተጠያቂነት ያለ ምንም የገንዘብ መጠን ተፈጻሚ እንደሚደረግ የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።
ምንጩ ያልታወቀ ንብረት አፍርቷል ተብሎ በዓቃቤ ሕግ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው የንብረቱን ምንጭ እንዲያስረዳ በዓቃቤ ሕግ የጽሑፍ ጥያቄ እንደሚቀርብለት የሚገልጸው ረቂቅ አዋጁ፣ ይህ ጥያቄ የደረሰው ማንኛውም ሰው ያለውን ማንኛውንም የንብረት ዝርዝርና የተገኘበትን አግባብ የሚያሳይ መግለጫና ዝርዝር ማስረጃዎችን በማያያዝ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጽሑፍ ለዓቃቤ ሕግ ማቅረብ እንዳለበት ያመለክታል።
የንብረቱን ምንጭ እንዲያስረዳ የተጠየቀው ሰው የንብረቱን ምንጭ ለማስረዳት የሚያቀርበው ማስረጃ ሕጋዊ መሆን እንዳለበትም ተደንግጓል።
ማስረጃዎችን ለማቅረብ የተመለከተው የአንድ ወር የጊዜ ገደብ አስገዳጅ ሁኔታ ሲኖር ለዓቃቤ ሕግ በሚቀርብ አቤቱታ ሊራዘም እንደሚችል፣ ሆኖም የጊዜ ገደቡ ከስድስት ወራት በላይ እንደማይበልጥ ሪቂቁ ያመለክታል።
ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ከሚወረስባቸው መንገዶች በተጨማሪ ‹‹በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ›› የንብረት መውረስ የሚፈጸምባቸው ድንጋጌዎችም በረቂቅ አዋጁ ተካተዋል። ረቂቅ አዋጁ በሰጠው ትርጓሜ መሠረት ‹‹በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ መውረስ›› ማለት በማንኛውም ዓይነት ወንጀል በፍርድ ቤት ውሳኔ ጥፋተኛ ባይባልም፣ በረቂቅ አዋጁ በተቀመጡ ድንጋጌዎች መሠረት የሚከናወን የንብረት መውረስ ነው።
በዚህም መሠረት በወንጀል ክስ የጥፋተኝነት ውሳኔ ባይሰጥበትም ከወንጀል ድርጊቱ የንብረት ጥቅም አግኝቷል ተብሎ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ላይ ዓቃቤ ሕግ የንብረት መውረስ ማመልከቻ ለፍርድ ቤት ሊያቀርብበት እንደሚችል ረቂቅ ድንጋጌው ያመለክታል።
በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ የንብረት መውረስ ማመልከቻ ሊቀርብ የሚችልባቸው ሁኔታዎች በረቂቅ አዋጁ የተዘረዘሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረው ወይም የተከሰሰው ሰው ሲሞት፣ ሲያመልጥና ሲጠፋ ወይም ወንጀል ፈጻሚው ሳይታወቅ ሲቀር ነው።
እንዲሁም በይርጋ ምክንያት የወንጀል ጥፋተኝነት ውሳኔ ማሰጠት ሳይቻል ሲቀር፣ የተገኘው ማስረጃ በወንጀል ክስ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማሰጠት የሚያስችል የማስረጃ ምዘና መሥፈርትን የማያሟላ ከሆነ፣ ከወንጀል ድርጊቱ ጥቅም ስለመገኘቱ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር፣ ተከሳሹ ምሕረት ሲደረግለት፣ የቀረበበት ክስ በማንኛውም ምክንያት ሲቋረጥ፣ ተጠርጣሪው በወንጀል ያለ መከሰስ መብት ያለው እንደሆነ በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ የንብረት መውረስ ክስ ሊቀርብ ይችላል።
በተጨማሪም የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኝና በሦስተኛ ወገን ይዞታ ወይም ባለቤትነት ሥር የሚገኝ ንብረት ሲሆን፣ በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ የንብረት መውረስ ክስ ሊቀርብ እንደሚችል ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል።
የወንጀል ቅጣቱ በይቅርታ ወይም በምሕረት ቀሪ የተደረገለት፣ የተገደበለት ወይም በአመክሮ የተለቀቀ ማንኛውም ሰው፣ ይህንን ሁኔታ ከወንጀል ድርጊቱ የተገኘውን ንብረት ለመውረስ ለሚቀርብበት ክስ መቃወሚያ አድርጎ ማቅረብ እንደማይችልም ረቂቁ ያመለክታል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ባለፈው ማክሰኞ የመጀመሪያ ንባብ (ውይይት) ባካሄደበት ወቅት ሁለት የምክር ቤት አባላት ብቻ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ አንደኛው አስተያየት ረቂቅ አዋጁ በፍጥነት ፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል የሚጠይቅ ነው።
ይሁን እንጂ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር ዕይታ እንዲመራ ድምፅ በተሰጠበት ወቅት ሁለት የምክር ቤት አባላት የተቃውሞ ድምፅ ሰጥተው ረቂቁ በዝርዝር እንዲታይ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።