ሸኔ ቢመጣ ምን ይጠቅማል? “እኔ ብቻ እያለ” ስልጣን ቢያዝ ምን ያደርጋል? አማራ ክልል ያለው ሸኔ ቢመጣ፣ ቢሳካለት ምን ያደርጋል? የአባቶቼን ርስት ብቻዬን እወርሳለሁ እያለ መንግስት ቢሆን ምን ያመጣል? አብይ አሕመድ ይህን ጥያቄ ከጠየቁ በሁዋላ ሁሉም የአባቶቹ ርስት ወራሽ ነው ሲሉ ለፓርላማው ተናግረዋል። እነዚህንና ሌሎቹን ነፍጥ ያነሱ ሃይሎችን ” ስፓናቶ” ብለዋቸዋል። ሲያስረዱም የማያስር ጥርሱ የላሸቀ ብሎን ዝም ብሎ ይዞራልና አያስርም።
በአገሪቱ የተለያዩ አክባቢዎች በመናበብ ከሚካሄዱ የጠብ መንጃ ፍልምያዎች ጎን ለጎን የመፈንቅለ መንግስት ጥሪ ለመከላከያ አመራሮችና መኮንኖች ለሚያቀርቡ ምላሽ ይሆን ዘንድ “መፈንቅለ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም፤ እኛ ወታደሮች ነን መፈንቅለ መንግሥት እንዳይሳካ አድርገን ነው ተቋማት የሠራነው”ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተናገሩ።
ዛሬ በተካሄደው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከም/ቤቱ አባላት የቀረቡላቸው ጥያቄዎች ኢኮኖሚ፣ሰላምና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ። የደህንነት ጉዳዮችን አስመልክቶ ሲናገሩ መፈንቀለ መንግስትን አታስቡት ብለዋል።
ስም ሳይጠቅሱ “በቅርቡ አንዳንድ ቦታ ላይ መፈንቅለ መንግስት እናካሂዳለን ብለው አንዳንድ አባቶቻችን ውይይት ያደርጋሉ” ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር በመለገስ ጉዳዩ እንደማይሳካ አመልክተዋል። “እናም” አሉ አብይ ” እናም ለወንደሞቼና ታላላቅ አባቶች የምሰጠው ምክር በኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግስት አይሳካም የሚል ነው” ሲሉ “ወንድሞቼና ታላላቅ አባቶች” ላሉዋቸው እንዳይደክሙ አሳሰበዋቸዋል።
“እኛ ወታደሮች ነን መፈንቅለ መንግስት እንዳይሳካ አድርገን ነው ተቋማትን የሰራነው” በማለት ስለ ጸጥታ ሃይሉ አወቃቀር ያስታወቁት አብይ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግስት አንዴ ተሳክቷል፣ አሁን ግን ጭራሽ አይሳካም” ብለዋል። አክለውም “ታላላቆቼና አባቶቼ ጊዜያችሁን እና የወዳጆቻችን ሀገር ገንዘብ አታባክኑ፤ ገስት ሃውስም አታጣቡ” ሲሉ የሚወጠነውን ውጥን ሙሉ በሙሉ እንደሚያውቁት በማሳየት አሳቡን ውሃ ቸልሰውበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ በግጭት፣ በጦርነት፣ በሽፍታነትና በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን መያዝ እንደማይቻልም አስገንዝበዋል፡፡
ህግ ማስከበርን በተመለከተ ሲናገሩ “ሶስት ክላሽ ሲይዙ አራት ኪሎ ይታያቸውና ውርውር የሚሉ አካላት፤ ትንሽ ሲቆነጠጡ ደግሞ ጀኖሳይድ ይላሉ፡፡ ይህ ተገቢነት የለውም፡፡ መንግስት በሰለጠነ መንገድ ችግሮች በውይይትና ድርድር እንዲፈቱ ቅድሚያ መስጠቱን እንደ ድክመት የሚቆጥሩ ካሉ፤ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ነው” ሲሉ የመንግስታቸውን ወቅታዊ ቁመናንም እግረ መንገዳቸውን ጠቆም አድርገዋል።
ይህም ሆኖ መንግሥት የትኛውም ዓይነት አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ አሁንም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።
- 971 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበውን የ2017 የመንግሥት በጀት አጽድቋል፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ሰላምን ጨምሮ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በምላሻቸውም፤ ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት በግጭትና ጦርነት አዙሪት ውስጥ ማለፏን አስታውሰው፤ ይህ እርስ በርስ የመገዳደል ታሪክ በእኛ ትውልድ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡ የእርስ በርስ ግጭትን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደማይገባም ነው የተናገሩት፡፡
አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ መንግሥት በሆደ-ሰፊነት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥሪና ማግባባቶችን ማድረጉን አንስተዋል፡፡
መንግሥት በሰለጠነ መንገድ ችግሮች በውይይትና ድርድር እንዲፈቱ ቅድሚያ መስጠቱን እንደ ድክመት የሚቆጥሩ ካሉ፤ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ነው፤ ሲሉም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በግጭትና ጦርነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን መያዝ ፈጽሞ እንደማይቻል ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ ዛሬም ነገም የሚበጀው በሰላምና በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ነው ብለዋል፡፡ የእኔ ብቻ የሚል እና ዋልታ የረገጠ እሳቤ ለሀገር እንደማይበጅም አመላክተዋል።
መንግሥት ለዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱንና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትመች ሀገር ለመገንባት ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም በምክክሩ ተሳታፊ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከመገፋፋት ከመገዳደል በመውጣት በሰከነ መንፈስ ተወያይቶ ለትውልዱ የተሻለ ሀገር ማስተላለፍ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡