አውሮፕላን ሊበር የሚችለው አውሮፕላኑ እንዲበር የሚፈቅዱ የተለያዩ አካላት ከፈቀዱ በሁዋላ፣ ለደህንነት ስጋት የሚሆንበት አግባብ እንደሌለ ተረጋግጦ መሆኑ ገሃድ በመሆኑ ይህ ሳይሟላ ለምን በረራ አልተካሄደም በሚል አምባ ጓሮ መፍጠር በህግ እንደሚያስቀጣ የህግ ባለሙያው አስታወቁ። አየር መንገዱ “ብሄራዊ ኩራታችሁን እንደ አይናችሁ ጠብቁ” ብሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በረባ ባልረባ ጉዳይ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ስም ማንሳት የተለመደ ተግባር ሆኗል። ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀድሞ አመራሮች አገልጋይ እንደሆኑ የሚታወቁ የሚዲያ ሰዎች ሳይቀር ይህን ተቋም እየዘመቱበት መሆኑ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። በረባ ባልረባ እርምጃ የሚወስደው የህግ የመንግስት ህግ አስከባሪ ሃይልም በዚህ ደረጃ ጣራ የነካ ዘመቻ ሲካሄድ ዝም ማለቱን በርካቶች ነቅፈዋል።
በአየር ጸባይ ምክንያት ወደ ትግራይ ሊደረግ የነበረ በረራ እንዲሰረዝ መደረጉን ተከትሎ፣ ኤከሃያ ሺህ በላይ ተከታይ አለኞኦ ጉዳችሁን አወጣዋለሁ” በሚል ያስፈራራውን ጎረምሳ “ደንቆሮ” ሲሉ በግል የቲወተር ገጻቸው የዘለፉትና እግረመንገዳቸውን የአቪየሽንን ህግ ያስተማሩት የህግ ምሁሩ አልማርያም፣ ጠበቃ ሙሉጌታ በላይን ጠቅሰውና የባለሙያውን የቪዴዮ ማብራሪያ አክለው የሚከተለውን አሰራጭተል።
“ኢትዮጵያ ላይ የሚበሩ ማናቸዉም አውሮፕላኖች ላይ ወንጀል መፈፅም ከፍተኛ ክጣት እንደሚያስከትል ህጉን በሚገባ ያብራራዋል” ያላሉ አልማሪያም። አክለውም፣ ” ጆን ዳንኤል የተባለ የ ቲክቶክ ዕብድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች አስፈላጊ የበረራ ስነስርዓት ሲያስከብሩ አሻፈረኝ ብሎ የማህበራዊ ትስስር ገፁን በመጠቀም የአየር መንገዱን ሰራተኞች ስራቸዉን እንዳይሰሩ ወከባ ፈጥሯል። ሌሎች ተሳፋሪዎችም የአየር መንገዱን ሰራተችኞች ትዛዝ እንዳይቀበሉ አስተባብሯል። የአየር መንገዱ ሰራተኞች ላይ ዛቻ ፈጽሟል። የአየር መንገዱን ስም አጥፍቷል። በጠቅላላ አየር መንገዱንና ተሳፋሪዎቹን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተገባር ፈጽሟል። ይህ የግል ህይወቱን እስከመጨረሻው የሚያበላሽ ወንጀል ራሱ በቀረፀው ቪድዮ ማስረጃ እማኝ አድርጎ አሰራጭቷል። በዚህም ተግባሩ ቢያንስ ለአስራ አምስት ዓመት በእስራት ሊቀጣ ይችላል” የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተከታዮች የጠበቃ ሙሉጌታን ሕጋዊ ትንተና እና ምክር አዳምጡ ። ብለውዋል።
አየር መንገዱ በበኩሉ ብሔራዊ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዐይኑ ብሌን ሊጠብቀው እንደሚገባ አስገንዝቧል። የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሃና አጥናፉ እንዳሉት ሰሞኑን በተፈጠረው ጭጋግ ሳቢያ አርባ ሁለት ዓለም ዓቀፍ በረራዎች አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እንዲስተናገዱ ማድርፈግ አልተቻለም። ወደ ትግራይ የተደፍረገ በረራም በተመሳሳይ ትግራይ ማረፍ ባለመቻሉ ወደ አዲስ አበባ መመለሱን በማስረዳት ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
ሃላፊዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከሰሞኑ ባጋጠመው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ የመንገደኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ በረራዎች እንዲሰረዙና እንዲራዘሙ መደረጉ ደጋግመው በቁጥር የተደገፈ መረጃ ሰጥተዋል።
አየር መንገዱ ዓለም-አቀፍ ደረጃው የጠበቀ፣ ሥነ-ምግባር የተላበሰና ጥራት ያለው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አውስተው፣ ብሔራዊ ኩራት የሆነውን ተቋሙ መደበኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለደንበኞች ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በሚሰራቸው ሥራዎችም የበርካታ ስኬቶች ባለቤት የሆነ አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ከግምት በማስገባት ከሰሞኑ በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ከትናንት በስቲያ ብቻ 42 ዓለም አቀፍ በረራዎች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፍ ባለመቻላቸው ለደንበኞችን ደኅንነት ሲባል አቅራቢያ ወዳሉ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲያርፉ መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡
የሀገር ውስጥ በረራዎችም በዚሁ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ መስተጓጎላቸውን ነው ያስረዱት፡፡
ለአብነትም ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ በነበረው የሀገር ውስጥ የበረራ መርሐ-ግብር ወደ መቀሌ ተጉዘው የነበሩ ሁለት አውሮፕላኖች ማረፍ ሳይችሉ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ሦስተኛ በረራ ወደ መቀሌ ለማድረግ በዝግጅት ላይ የነበረው አውሮፕላን የአየር ሁኔታው ለደኅንነት አስጊ በመሆኑ አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ሳይነሳ በረራው እንዲሰረዝ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በጊዜው በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች ከበረራው መሰረዝ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ደኅንነት መመሪያን በሚጻረር መልኩ ያልተገባ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን አሰራሮችን በጥብቅ ዲሲፕሊን እንደሚተገብር ገልጸው÷ መሰል ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ሊታረሙ እንደሚገባና ማንኛውም መንገደኛ አሰራሮችን ሊያከብር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
አየር መንገዱ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቱም ባሻገር በሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ በተለይም በዓላት ሲኖሩ የተጓዦችን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪና ግዙፍ አውሮፕላኖችን ጭምር በመመደብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሰሞኑን በትግራይ ክልል ለሚከበረው የአሸንዳ በዓል ወደ መቀሌ በቀን እስከ 11 በረራዎችን እየተደረገ መሆኑን በአብነት አንስተዋል።
አየር መንገዱ በሚሰራው ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገልግሎት ጥራትና የላቀ አፈጻጸም ተደጋጋሚ ሽልማቶች እያሸነፈ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በመሆኑም ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀሰውና ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት መሆን የቻለውን ይህን አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዐይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
አየር መንገዱ በደንበኞች የሚነሱትን ቅሬታዎችን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዴስክ በሁሉም ተርሚናሎች ውስጥ ማቋቋሙን ጠቁመው÷ ደንበኞች ቅሬታና ችግር ካጋጠማቸው በቅሬታ ማቅረቢያ ዴስኮቹ ማመልከት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በቀጣይም አየር መንገዱ ለደንበኞች ደኅንነትና ምቾት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን በማንሳት÷ በተለይ የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳይ ላይ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግለሰቦች ደረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሥም የማጥፋት ዘመቻዎችን በማጋለጥ የሚዲያ አካላት ከአየር መንገዱ ጋር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።