ለሶስት መንግስት ያገለገሉ “ሎሌ” በሚል የሚወቅሷቸው ሁሉ አደባባይ ወጥተው ባይናገሩም በለመዱት የጓሮ ቧልት ሲሸረክቷቸው ኖረዋል። ልምዳቸውን ከልብ ቢያካፍሉ ጠቀሚታቸው ለአገር ብዙ ነው። በተለይም በዓለም ዓቀፉ የዲፕሎማሲ አግባብ ያላቸውን ግንኙነት ለአገር ቢያውሉት ከሚል የጓጉ የመንግስትን ውሳኔ አወድሰዋል። የአደባባይ ምሁሩ ፕሮፌሰር መስፍን ግን “በፍጹም ስህተት ነው” ሲሉ ተሟግተዋል።

“ዝምታ ነው መልሴ ” ሲሉ ወይዘሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ድምጻቸውን በቲውተር በኩል በዘፈን ምርጫ አጅበው ብቅ ያሉት ለስንብት ሁለት ቀናት ሲቀራቸው ነው። ” የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው ጊዜም እንደ ሰው ሲገፋው፣ መሄጃ መውጫ ሲጠፋው ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው” ሲሉ የተቀኙት ፕሬዚዳንቷ ” ለአንድ ዓመት ሞከርኩት” በሚል ሃረግ መልዕክታቸውን አስረውታል።
ይህኔ ነው የኔታ ” ነብሳቸውን ይማረውና” ሲሉ ፋይል ያገላበጡ ፕሬዚዳንቷ በኤክስ ይፋዊ ገጻቸው ላይ ላሰፈሩት ቅኔ ምላሽ የሰጡት። አንዳንዶች “ህዝብም መንግስትም መሆን አይቻልም” ሲሉ ቀልደውባቸዋል።
ግልጹ ፣ ያመኑበትን ለመናገር ወደሁዋላ የማይሉት፣ የአደባባዩ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ” ለሶስት መንግስት ያገለገለች” ሲሉ በሎሌነት የመሰሏቸው የሳህለወርቅ ዘውዴን ሹመት በፍጹም እንደማይቀበሉት ተናግረው ነበር።
ለስንብት ሁለት ቀን ሲቀር እንጉርጉሮ የመረጡት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የተቀመጡበት ወንበር ለመሆኑ “ዝምታ ነው መልሴ፣ አንድ ዓመት ቻልኩት ” ያሰኛል? አቶ መለስ ለክተውና መትረው ያረቀቁት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ስልጣን ለግንዛቤ እንዲሆን በሚል በርካቶች “ዳግም አስተውሉ። ዝም ብላችሁ አትንጎዱ” ሲሉ ከህገመንግስቱ ጠቅሰዋል።
አንቀጽ 71 የኘሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር በሚል ርዕስ በዝርዝር እንደሚከተለው የደነገገው የኃላፊነት ዕርከን ሳህለወርቅ እንዲያጉረመርሙ፣ በአሽሙር እንዲቀኙ፣ ዘፈን እንዲመርጡ ያስችላል? መለስ ነብሳቸውን ይማረውና ያኖሩላቸው ስልጣን ከታች ያለው ነው
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት ዓመታዊ የጋራ ስብሰበባ ይከፍታል፡፡
- በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቃቸው ሕጐችና ዓለምአቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ያውጀል፡፡
- ሀገሪቷን በውጭ ሀገሮች የሚወክሉትን አምባሳደሮችና ሌሎች መልክተኞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ይሾማል፡፡
- የውጭ ሀገር አምሳደሮችንና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል፡፡
- በሕግ መሰረት ኒሻኖች እና ሽልማቶችን ይሰጣል፡፡
- በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕግ በተወሰነው መሰረት ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጐችን ይሰጣል፡፡
- በሕግ መሰረት ይቅርታ ያደርጋል፡፡
እንግዲህ ይህ ከሆነ ኃላፊነታቸው የቱን ኃላፊነት እንዳያከናውኑ ተከለከሉ? በሚል መጠየቅ ግድ ይላል። በሰበር ታጅቦ አስቀድሞ አልቅሶ ለማልቀስ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አዛኝ፣ አልቃሽ፣ ልቡ የተሰበረ፣ መሄጃ የሌለው፣ የተገፋ ወዘተ መስለው የቀረቡት ተሰናባቿ ፕሬዚዳንት እንግዳ እንዳይቀበሉ ተከለከሉ? የጸደቀ ህግ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ሄደው እንዳያሳትሙ ታገዱ?ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን ሹመት እንዳያጸድቁ ተከለከሉ? ኒሻን አትስጡ ተባሉ? ይቅርታ አታድርጉ ተባሉ? የትኛውን ስልጣናቸውን ተከልክለው ነው ባለቀ ሰዓት አሽሙር የመረጡትይ?

አፈር ይቅለላቸውና መስፍን ወልደ ማርያም በድፍረት በሴትየዋ ሹመት ማግስት ልምድ ያላቸውና ለቦታው ብቁ የሆኑ በሚል አድናቆቱ ለሳቸውም፣ ለሾማቸውም ክፍል እንደ ጉድ በሚጎርፍበት ወቅት “አድሮ ይታያል” እንዳሉት ፕሬዚዳንቷ የኢትዮጵያ ህዝብ ” አልበተንም” ብሎ የህልውና ጦርነት ሲያካሂድ አቋማቸው ልክ እንዳልነበረ ማስታወስ ግድ ይላል። አልፎ አልፎም “አገም ጠቅም” እንዲሉ ዓይነት አቋም ሲያራምዱ የታዘቡ “ስድስቱን ዓመት ከጨረሱ የሚቀጥሉ አይመስልም” ሲሉ ቀድመው አስታውቀዋል። እናም ምኑ ነው የሳቸውን መሰናበት ሰበር የሚያደርገው?
“ዝምታ ነው መልሴ የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው ጊዜም እንደ ሰው ሲገፋው: መሄጃ መውጫ ሲጠፋው ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው ፤ ለአንድ አመት ሞከርኩ ” ያሉት ወይዘሮ ሳህለ ወርቅ፣ ከላይ ትህነግ ባወጣው ህግ መሰረት ይህን መዝፈናቸው ቤተ መንግስት ቁጭ ብለው ዘፈን እያዳመጡ ጊዚያቸውን ማሳለፋቸውን ከማስታወቁ በስተቀር ሌላ ፋይዳ እንደሌለው በስፋት አስተያየት ተሰጥቷል። በሌለ ስልጣን ምሬትና ለቅሶ አይነፋም። ጨዋነትም አይደለም። ልክ አቶ ታዬ ደንደአ እንዳደረጉት ዓይነት መሆን ነው። አቶ ታዬ ደንደአ ከስልጣን ሲሰናበቱ “ተሸውጃለሁ” በሚል በቲውተር ገጻቸው ላይ በአማርኛና ኦሮምኛ የጻፉት ጽሁፍ ልክ እንደዛሬው የሳህለወርቅ “ቅኔ” ሰበር የሚል ታርጋ ተለጥፎለት ሲሰራጭ ነበር። አቶ ታዬ ጥፋተኛ ይሁኑ አይሁኑ ለጊዜው ብዙ ማለት ቢያስቸግርም ከስልታን ሲነሱ ” ተሸውጄ ተከትዬሃለሁ. ተድምሪያለሁ” ማለታቸው አስተችቷችቨው ነበር። ምክንያቱም ስልጣን “በቃዎት” ሲባሉ በመሆኑ።
በደፈናው በቅኔና በሙሾ መልክ የቀረበው የወይዘሮ ሳህለወርቅ የግጥምና የዜማ ጽሁፍ ስለምን ጉዳይ እንደሆነ ፤ ምን ለመናገር ታስቦ እንደሆነ በሰኞው የስንበት ንግግራቸው የተሰጣቸውን ህገመንግስታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው እንዲያብራሩ ይጠበቃል። ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ማብራሪያ ካቀረቡ “በፕሬዚዳንት ደረጃ የቀረበ አሽሙር ” ተብሎ ለትውልድ መማሪያ ይሆናል። ምክር ቤቱም ህጉን እያነበበ ” ምን ጎደለብዎት” ብሎ ሊጠይቃቸው ግድ ነው። በህግ ከተቀመጠው ውጪ ያለ የመጨረሻ ለቅሶ ከሆነ “ቤተመንግስቱን እስክሞት ልኑርበት” ማለት ይሆናልና ምን አልባትም የጡረታ ጥቅማ ጥቅምን ሊያሳጣ ይችላል የሚል ስጋትም እየተሰማ ነው።
አንዳንዶች ” አሁን ባለው ስርዓት በከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቀው ነው እየሰሩ ያሉት ፤ በተለያዩ ጉዳዮች አለመግባባት ውስጥም እንደነበሩ ብዙ ጊዜ በሚዲያ ይሰማ ነበር ፤ ለመናገር እንኳን እድል የላቸውም ፤ ባገኙት አጋጣሚ ግን በገደምዳሜው ስሜታቸውን ስለ ሀገራቸው ይናገሩ ነበር ፤ አሁንም ቦታውን ሲለቁ ስለዚህ ስርዓት ብዙ የሚናገሩት ይኖር ይሆናል ” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
” በዚህ ልክ ትልቅ የስልጣን እርከን ይዘው ህዝብን ግራ የሚያጋባ ድፍንፍን ያለ ፅሁፍ በገጻቸው መጋራቱ ሳያንስ እውነትም እሳቸው መሆናቸውን በግልጽ አለማብራራታቸው ትክክል አይደለም ፤ ችግር ካለም እውነታውን ለህዝብ ማሳወቅ አለባቸው እንዲህ የዘፈን ግጥም ከሚያስቀምጡ ” በሚል አንዳንዶች አስተያየት እንደሰጡት ቲክቨሃ ጽፏል።
በዚሁ ሚዲያ የተጠቀሱ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ” የ6 ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ ይህን አይነት ነገር በገጻቸው መፃፋቸው የህዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ነው። እስከዛሬ በሀገሪቱ ብዙ ነገር ብዙ ግፍ ሲፈጠር ባላየ ሲያልፉ ነበር ። አንዳንዱን ደግሞ እየመረጡ ሲናገሩ ነበር ። ለምን አሁን ? በዚህ ስልጣን እንደማይቀጥሉ ስለሚያውቁ ነው ? ስልጣንም መልቀቅ ከነበረባቸው ቀድሞ ተናግሮ እንጂ አሁን ላይ ይህን አጀንዳ ለህዝብ መስጠት ትክክል አይደለም ። ጊዜያቸው አብቅቷል ይሰናበታሉ። እሱንም ስለሚያውቁ ነው ” ሲሉ ፅፈዋል።
በኢትዮጵያ የፕሬዜዳንት ስልጣን ዘመን 6 ዓመት ሲሆን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ወደ ስልጣን የመጡት ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ/ም ላይ ነበር። ስለዚህ በጥቅምት 6 ዓመት ይሆናቸዋል። ይህ ማለት የስራ ጊዜያቸውን ስለጨረሱ በህጉ መሰረት ይሰናበታሉ ማለት ነው። እና አገልግሎቱን የጨረሰ ሰው ቀኑን ቆጥሮ ሊሰናበት ሲል “ሰበር ዜና” የሚሆነው በምን መስፈርት ነው? ይህ ከሙያም ከስነምግባርም ያፈነገጠ በሽታ ገና ብዙ ያሰማናል።
በገለልተኛነታቸው የሚታወቁ አስተያየት ሰጪዎች፣ የተሰጣቸውን ህገመንግስታዊ ስልጣን እየጠቀሱ የተበደሉትን በአምክንዮ ማስረዳት ስለመቻላቸው አስቀድሞ ማረጋገጥ ሳይቻል ብዙ ማለት አስፈላጊ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ስለ ሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ስልጣንና ተግባርን አስመልክቶ ይደነግጋል። በምዕራፍ ሰባት ስለ ሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንትበአንቀጽ 69 የቀረበው “ኘሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ርዕሰ ብሔር ነው ” ይላል።
አንቀጽ 70 የፕሬዜዳንቱ አሰያየም አስመልክቶ
- ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ የማቅረብ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ይህ ምክር ቤት የመንግሥት ፖሊሲዎችን ማቅረብ እና ምንጭ ሆነው የሚሰሩትን የህዝብ ሃላፊነት በመደገፍ ለምንመለከታቸው ነው።
- የቀረበው ዕጩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ከተደገፈ ፕሬዜዳንት ይሆናል።
- የምክር ቤት አባል ፕሬዜዳንት ሆኖ ከተመረጠ የተወከለበትን ምክር ቤት ወንበር ይለቃል።
- የፕሬዜዳንቱ የሥራ ዘመን 6 ዓመት ነው። አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዜዳንትነት ሊመረጥ አይችልም።
ይላል። በዚህ ስሌት መሰረት ወይዘሮ ሳህለወርቅን ፕሬዚዳንት አድርጎ የሾማቸውና ያቀረባቸው ይህ መድረክ ሰኞ ወደ ወይዘሮነት ይመልሳቸዋል። ይህ መብቱ ነው። በግልጽ በህግ የተቀመጠ ነው። ህገመንግስቱ እስኪቀየር ይህ ይቀጥላል።
አቶ ሀይደር መሀመድ “የወይዘሮ ሳህለወርቅ ለቅሶ አላማረኝም” በሚል በማህበራዊ ገጻቸው ይህን ጽፈዋል። ከስር ያንብቡ።
ባለ ቀይ መስመሯ እናታችን ከቢሯቸው ወጥተው መቶ ሜትር ቢራመዱ የሐገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በግላጭ ማግኘት ይችላሉ። ስልካቸውን አውጥተው ቁጥር ቢመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሃሎ” ይሏቸዋል። ነገር ግን እናታችን ብሶታቸውን እንደአክቲቪሲት ትዊተር ላይ ነው የሚገልፁት።
በዚያ ላይ አንድ አመት የታገሱ ሴት አንድ ቀን መታገስ አቅቷቸው በእለተ “ኢሬቻ” መናገርን መረጡ። ከ 365 ቀን የመሃሙድ አህመድ ዘፈን ትዝ ያላቸው በእለተ ኢሬቻ ነው።
የተከበሩ ታዬ አንቀስላሴ የሆነ ስብሰባ ላይ “መንግስታት እንደአክቲቪስት መሆን የለባቸውም” ብለው የሱማሊያን መሪዎች ሸንቆጥ አድርገው ነበር። እንደው “የራስ እንትን አይሸትም” እንጂ የኛም መሪዎች አክቲቪስት እየሆኑ ነው የተቸገርነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዳንኤል ክብረትን አንዱ ጋዜጠኛ “ድሮ መንግስትን ትተች ነበር አሁን ለምን አቆምክ?” ሲለው “አሁንማ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለራሱ እነግረዋለሁ” ብሎ ነበር።
ፕሬዘዳንትም እንደህዝብ “ተው ልመድ ገላዬ” እያለ ካንጎራጎረማ አራት ኪሎ መቀመጡ ለምን አስፈለገ ታዲያ? እኚህን ስንዱ እመቤት የማግኘት እድሉ ቢኖረኝ በተመሳሳይ ሰዓት ህዝብም መንግስትም መሆን እንደማይቻል እነግራቸው ነበር። ሲሉ ሀይደር መሀመድ በምኞት ያበቃሉ።
ወይዘሮ ሳህለወርቅ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን በተለያዩ አገራት በአምባሳደርነት/ በዲፕሎማትነት አገልግለዋል። በአፍሪካና በተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ ተወካይ ሆነው ሰርተዋል። እ.ኤ.አ. በ 2011 ባንኪሙን ሳህለወርቅን በናይሮቢ (UNON) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አድርጎ ሾመዋቸው ነበር። በዚህ ሹመታቸው ወቅት እሳቸው የተቀመጡበት የናይሮቢው ጽሕፈት ቤት በ2012 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ማዕከል መሆኑ ይታወሳል።
እ.ኤ.አ ሰኔ 2018 ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሳህለ ወርቅን በአፍሪካ ህብረት ልዩ ወኪላቸውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አድርገው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊነት ሾሟቸው። ለዚህ ሹመት ሲበቁ በቦታው ላይ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነዋል። ሳህለ ወርቅ ጡረታ ለመውጣት እየተዘጋጀች ነበር ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ይህን ስልጣን ቢያገኙም ምንም ሳይቆዩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አቅራቢነት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል።
ከበብልጽግና መንግስት ጋር መስራታቸውን ተከትሎ ለሶስት መንግስታት ያገለገሉ ሰው መሆናቸውን ጠቅሰው የተቃወሙት ፐሮፌሰር መስፍን መከራከሪያቸው እሳቸው በዓለም ዓቀፍ መድረክ በነበራቸው ኃላፊነት ወያኔ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን በዚያ ደረጃ ሲረግጥና ሲጨፈጭፍ ድጋፍ ይሰግጡ እንደነበር በመናገር ነው። የውጭ አካላትና ታላላቅ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ወያኔን እንዳይቃወሙ እሳቸው አበክረው ይሰሩ እንደነበር ጠቅሰው ነው “እኚህ ሴት አይሆኑም” ሲሉ የሞገቱት።
ይፋ ባይሆንም ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በፕሬዚዳንትነት ወንበራቸው ላይ ሆነው በጦርነቱ ወቅት ካገኙዋቸው የውጭ አካላት ጋር በትክክል መንግስት የያዘውን አቋም ስለማራመዳቸው ጥርጣሬ ያላቸው፣ መንግስት ሆዱ የቆረጠው ከዛን ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይናገራሉ።

እጅግ ፌሚኒስት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማት ስለሆኑ ሰንዳፋ ባለ ማዕከል ለአዳዲስ ዲፕሎማቶች ልማዳቸውን እንድያካፍሉ ተጋብዝው እንደነበር የሚያስታውሱ እማኝ ለዝግጅት ክፍላችን አሳብ አካፍለዋል። በስልጠናው ላይ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ የተፍለገው የዋናውን የዓለም ዲፕሎማሲ ስለምኪያውቁት፣ ስለኖሩበት፣ ስለተሾሙበትና ስለተንጎራደዱበት ይህንኑ አስመልክተው እንዲናገሩ ነበር።
በንግግራቸው ከኢትዮጵያውያን እሴቶች ጋር የማይገጥሙና ከነጮጩቹ በውሰት የተገኙ እውቀቶችን መናገር ሲጀመሩ ስብሰባው ላይ የተገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ” ይህ የስልጠናው አካል አይደለም አቁሙ” ብለው እንዳስቆሟቸው የገለጹልን ምስክሮች፣ በበርካታ ምክንያቶች ፕሬዚዳንቷ እንደማይቀጥሉ አስቀድሞ የሚታወቅ እንደሆነ አመልክተዋል።