የነዳጅ ጥራት ፍተሻው የሚደረግበት ላብራቶሪ ድሬደዋ ላይ እየተገነባ መሆኑ ተገለጸ። ላቦራቶሪው አገር ውስጥ ስለሌለ ኢትዮጵያ በጅቡቲ የምታስገባው ነዳጁ ጥራት ተረጋግጦ እስኪመጣ ድረስ ለአንድ ቀን የመርከብ ማቆሚያ እስከ 25,000 ዶላር እንደምትከፍል ተመልክቷል። በሌላ በኩል ነዳጅ የሚከማችበት የጅቡቲ ዲፖ እድሳት ያልተደረገለት በአቅርቦት መጠን ላይ ችግር እያስከተለ ነው።
በጅቡቲ ላይ ጥገኛ እንድትሆን የተፈረደባት ኢትዮጵያ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር በርካታ ችግር ቢኖርባትም የነዳጅ ጥራት ማረጋገጫ ላቦራቶሪ መገንበቷ ከወጪ እንደሚያድናት ተመልክቷል።
ሸገር ሬዲዮ ኃላፊዎችን አነጋግሮ እንደዘገበው ኢትዮጵያ በጅቡቲ በኩል የምታስገባው ነዳጅ ከመርከቦች ወደ ዴፖው ከመራፉ በፊት የጥራት ፍተሻ ይደረገለታል። ኢትዮጵያ መፈተሻ ላብራቶሪ ስለሌላት ነዳጅ የጫነው መረከብ ለመቆም ይገደዳል። ይህም ኢትዮጵያን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋታል።
“ኢትዮጵያ የጥራት ፍተሻውን ለማድረግ የሚያስችላት ላብራቶሪ ስሌላት ናሙናው ወደ ኬንያ እና ሌሎች ሀገራት ይላካል” ያለው ዘገባው፣ የነዳጁ ጥራት ተረጋግጦ እስኪመጣ አንድ መርከብ አንድ ቀን ሲቆም ኢትዮጵያ እስከ 25,000 ዶላር ለሚደርስ ተጨማሪ ወጪ ይዳርጋታል።
በዚሁ ችግር ሳቢያ የነዳጅ ጥራት ፍተሻው የሚደረግበት ላብራቶሪ ድሬደዋ ላይ እየተገነባ እንደሚገኝ በአፍሪካ የንግድና ሊጂስቲክስ ላይ አትኩሮ የሚሰራው እና ትሬድ ማርክ አፍሪካ የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ እውነቱ ታዬ ለሸገር ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጋር በመተባበር እየተገነባ ያለው ይህ ላቦራቶሪ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተመደበለት ነው ተብሏል።
“አንድ መርከብ የጫነው ነዳጅ ጥራቱ እስኪረጋገጥ ድረስ አንድ ቀን እንኳን ወደብ ላይ በመቆሙ የሚከፈለው ሃያ አምስት ሺህ ዶላር ተጠቃሚው ላይም የሚጨመር ነው” የሚሉት አቶ እውነቱ የላብራቶሪው ግንባታ ይህንንም የሚያስቀር እንደሆነ አመልክተዋል።
ጁቡቲ በሚገኘው ሆራይዘን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ በኩል በቀን እስከ አስር ሚሊየን ሊትር ናፍጣ እንዲገባ ቢፈለግም እየገባ ያለው ግን ከስምንት ሚሊየን ሊትር ያልበለጠ እንደሆነ የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ከዚህ ቀደም ተናግሯል።
የሚፈለገውን ያህል ነዳጅ በዴፖው በኩል ማስገባት ያልተቻለው ዴፖው ከተገነባ 18 ዓመት የሞላውና ጥገና ተደርጎለት የማያውቅ በመሆኑ አገልግሎቱ በመቀነሱ ነው ተብሏል።
ጂቡቲ ወደብ ማስተናገድ የሚችለውን ያህል መጠን ነዳጅ በጂቡቲ በኩል እንዲገባ፣ የተቀረው ደግሞ አማራጭ ተፈልጎ በሌላ ወደብ እንዲገባ ተወስኖ ጥናት መደረጉንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መጥቀሱ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ከውጭ ለምታስገባው ነዳጅ በያመቱ ከአምስት ቢሊየን ዶላር በላይ እንደምታወጣ መረጃዎች ያሳያሉ።
ባለፈው ዓመት አገልግሎቱን ጅቡቲ ሄዶ የተመለከትው የኢትዮጵያ ቴትሮሊየም ኢንተርፕራይዝ ልዑክ ቡድን ጅቡቲ ሌላ አማራጭ እንድትፈልግ መተየቁን ገልትሶ ካፒታል ጋዜጣ መዘገቡ የሚታወስ ነው።