በቅርቡ የኢትዮጵያ የጸጥታ ምክር ቤት አጠቃላይ የአገሪቱን ጸጥታ ሲገመግም የባህር በር ጉዳይ ግለቱን ጠብቆ እንደሚቀጥል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህንኑ በመድገም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ “ብሔራዊ ጥቅማችን፣ ሀገራዊ ጥቅማችንን አስመልክቶ ያለን አቋም አይዛነፍም” ሲል በድጋሚ ለተወካዮች ምክር ቤት አረጋገጡ። ከኤርትራም ጋር መንግስት የቃላት ጦርነት ውስጥ እንዳልገባ አመልከቱ። አሜሪካ ኢትዮጵያ በሰላማዊና ህጋዊ መነገድ የባህር በር ለማግነት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አሜሪካ አስታውቃለች።
በኤርትራ በኩል “ትንኮሳ ቢኖርም፤ አንዳንዴ በሆደሰፊነት፣ አንዳንዴ ሰምቶ አንዳልሰማ፣ አንዳንዱን ደግሞ በራሱ በዲፕሎማቲክ ቻናል የሚመለሰውን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን” ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር ጌዲዮን ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው። ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በኢትዮጵያ በኩል”ወደፊትም የቃላት ጦርነትውስጥ የምንገባ አይመስለኝም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ የምትራመድ አገር መሆኗን አበክረው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ “ነገር ግን” አሉ “ነገር ግን ብሔራዊና አገራዊ ጥቅማችንን አስመልክቶ ያለን አቋም አይዛነፍም” በማለት መንግስታቸው አስቀድሞ ከያዘው አቋም ፈቀቅ እንደማይል አጉልተው አሳይተዋል። የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ ያስቻለ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ መሰረቱንም አመልክተዋል። ይህ ንግግራቸው እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት በይፋ ከሰጡት ድጋፍ ጋር የገጠመ ሆኗል።
ከተሰነጠቀው ትህነግ ተለይተው አዲስ ፓርቲ ያቋቋሙት ወገኖች ሻዕቢያ ኢትዮጵያ የባህር በር አጀንዳዋን እንድትቀይር ጫና ለማድረግ፣ ትህነግም በትግራይ ውስጥ ያሻውን እንዲያደርግና በፌደራል መንግስት ውስጥ የሚፈልገውን ቦታ ለማግኘት ስልት ነድፈው ጫና ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን ማመልከታቸው አይዘነጋም። እነዚሁ ክፍሎች ከውስጥ ያገኙትን መረጃ ጠቅሰው እንዳሉት ሁለቱም የመዋጋት አቅም የላቸውም። ሻዕቢያ በተለይ የተዋጊ ቁጥሩ የተመናመነና ተተኪ አልባ መሆኑን ትህነግ መገምገሙን መናገራቸው ይታወሳል። የጌዲዮን መግለጫም ይህንኑ እውነታ ያገናዘበ እንደሚመስል ተመልክቷል። መንግስት በቂ መረጃ ስላለው የጦርነት ስጋት እንደሌለበትም አመላካች እንደሆነ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ ያስቻለ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ ሲል ኢትዮኢንሳይደር የሚከተለውን ዘግቧል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላት በቃል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ የኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወቅታዊ ሁኔታ አንስተዋል።
ኤርትራ እና ኢትዮጵያን “ወደ ጦርነት ጅማሮ” እየወሰዳቸው ያለ “የቃል ጦርነቱ የተጀመረ ይመስለኛል” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ ሁለቱ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ያላቸው “ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት” በምን መልኩ እንደሚገልጽ ጠይቀዋል። ዶ/ር ደሳለኝ ከኤርትራ ጋር “ወደ ጦርነት መግባት እድል አለ ወይ?” ሲሉም ተጨማሪ ጥያቄ አክለዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “ ከኤርትራ መንግስት ጋር የኢትዮጵያ መንግስት የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባም” ሲሉ አስተባብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመወከል “ንግግር” የሚያድርጉ ተቋማት እንዳሉ ያመለከቱት ዶ/ር ጌዲዮን፤ “እስከማውቀው ድረስ የቃላት ጦርነት ውስጥ፤ እንዲህ እና እንዲያ ወደማለት አልገባንም” ሲሉ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል።
ጉዳዩ የሚያሳስባቸው፣ የሚመለከታቸው ዜጎች፣ የህዝብ ተወካዮች እና የቀድሞ የመንግስት ኃላፊዎች “የራሳቸውን ምልከታ” እንደሚያጋሩ ግን ሚኒስትሩ አልሸሸጉም። እነዚህ አካላት “ጆሮ ሊሰጣቸው ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል። “በቅርቡ የእነርሱ ንግግሮችን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሁኑ ቃል አቀባይ በተቋሙ መድረክ ላይ የተናገሩት ንግግር አለ። ያ የቃላት ጦርነት የሚባል አይደለም” ሲሉም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ባለፈው ሳምንት በነበራቸው ሳምንታዊ መግለጫ ላይ፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ ኢትዮጵያ በተመለከተ ስላቀረቧቸው ውንጀላዎች ተጠይቀው ነበር። “ከዚህ ቀደምም ከተወሰኑ ጎረቤት ሀገራት፣ በመሪዎች ደረጃ የተለያዩ inflammatory የሆኑ ንግግሮች፣ ውንጀላዎች፣ ክሶች፣ ዘለፋዎች የመጡበት አጋጣሚዎች ነበሩ” ሲሉ ቃል አቃባዩ በዚሁ መግለጫዎች ላይ አስታውሰዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ እነዚህ በመሰሉ “እንካ ሰላንታ ሳትጠመድ”፤ “የሰከነ ዲፕሎማሲ” አካሄድን ስትከተል መቆየቷን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ “ረጅሙን ርቀት የሚያስኬደውን አማራጭ በማየት፤ አሁንም ቢሆንም ከጎረቤቶቿ ጋር ተባብሮ መስራት ላይ ያተኮረ የውጭ ግንኙነት መርህ ነው የምትከተለው። ስለዚህ በየጊዜው የሚነሱ ጉዳዮች በዚያ አግባብ ነው የሚስተናገዱት” ሲሉ አቶ ነብያት በባለፈው ሳምንት መግለጫቸው አብራርተው ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ጥያቄ እና መልስ ቆይታቸው የቃል አቃባዩን ምላሽ አስተጋብተዋል። “መንግስት ፎርማሊ የሚላቸውን ነገሮች ብሏል። በፍጹም የቃላት ጦርነት የሚባል ነገር ውስጥ አልገባንም። እዚያ ውስጥ የማንገባው፤ እኛ ቀጠናዊ መረጋጋት እና ቀጠናዊ ሰላም እንዲኖር በኃላፊነት ስሜት የምንቀሳቀስ ሀገር ስለሆንን ነው። ዓለም አቀፍ መርሆዎችን፣ ህጎችን እና አሰራሮችን አክብረን የምንቀሳቀስ ሀገር ስለሆንን ነው” ብለዋል ሚኒስትሩ።
ከኢትዮጵያ አመራሮች የሚወጣ ቃል “ትልቅ ትርጉም” እና “ክብደት” እንዳለው የጠቆሙት ዶ/ር ጌዲዮን፤ በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ በመንግስት በኩል “በዘፈቀደ” እና “በመሰለኝ” ንግግሮች እንደማይደረጉ አመልክተዋል። “እንነጋገር ብንል ብዙ የሚያነጋግር ነገር አለ” ሲሉ የተደመጡት ሚኒስትሩ፤ ጉዳዩ መመራት ያለበት “በሚዛኑ”፣ “በጊዜው” እና “በጥንቃቄ” እንደሆነም አስረድተዋል።
በኤርትራ በኩል “ትንኮሳ ቢኖርም፤ አንዳንዴ በሆደሰፊነት፣ አንዳንዴ ሰምቶ አንዳልሰማ፣ አንዳንዱን ደግሞ በራሱ በዲፕሎማቲክ ቻናል የሚመለሰውን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን” ሲሉ ዶ/ር ጌዲዮን ጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ በኩል ወደፊትም ወደ ቃላት ጦርነት “የምንገባ አይመስለኝም” ሲሉ በድጋሚ ማረጋገጫ የሰጡት ሚኒስትሩ፤ “ነገር ግን ብሔራዊ ጥቅማችን፣ ሀገራዊ ጥቅማችንን አስመልክቶ ያለን አቋም አይዛነፍም” ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ረገድ ያለው አመለካከት ያልተለወጠ መሆኑን አስረድተዋል።
“የጋራ ተጠቃሚነት እንዳለው ባለመረዳት ወይ በተለያየ ምክንያት፤ ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ የሆኑ ሀገራዊ ጥቅም ጉዳዮች [ስታነሳ] ትኩሳታቸው የሚጨምሩ ሀገራት አሉ” ሲሉ የተደመጡት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በተመለከተ ያላትን አቋም “አጠናክራ” እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
“ግድብ ስንገነባ ‘እንዴት ይገነባል’ ብለው፤ ‘እንዴት ሲደረግ፣ እኛ ሳንፈቅድ፣ እኛ እሺ ሳንል ወይም ያለ እኛ ቡራኬ’ የሚሉ ነበሩ። ያ ሳያስቆመን ግድቡን እንዳጠናቀቅነው ሁሉ፤ ሌሎች መሰል ስትራቴጂ ፋይዳ ያላቸው የሀገራዊ ጥቅም ፕሮጀክቶቻችንም፤ ቅር ቢላቸውም፣ ደስ ባይላቸውም እውን ማድረጋችን አይቀርም” ሲሉ ዶ/ር ጌዲዮን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።
“የጋራ ተጠቃሚነት እንዳለው ባለመረዳት ወይ በተለያየ ምክንያት፤ ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ የሆኑ ሀገራዊ ጥቅም ጉዳዮች [ስታነሳ] ትኩሳታቸው የሚጨምሩ ሀገራት አሉ”– ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ኢትዮጵያ ጥቅሟን የምታስከብረው “የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ” እና “የዓለም አቀፍ ህግ አሰራር መርሆዎችን ከግንዛቤ ባስገባ መንገድ” እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት “ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን አለባት” የሚል አቋም በጽኑ እያራመደ ይገኛል።

በሌላ የባህር በር ዜና አሜሪካ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ጥረት እደግፋለሁ ብላለች። ኢትዮ ኤፍ ኤም 98 ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት ይደግፋል መባሉን የገለጸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጠቅሶ ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአሜሪካ መንግስት እንደሚደግፍ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አስታወቁ፡ ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች መሆኗንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ አሜሪካ ከወሳኝ አጋሯ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እንደምትሰራ በአጽንኦት መግለጻቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በፈጣን ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ትገኛለች። ሀገሪቱ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት እና ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች እንደምትገኝ ያወሱት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ይህ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚቀጥልም ትንበያ መኖሩን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ህልም ለማሳካት የባህር በር አማራጯን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት የሚደግፈው መሆኑንም አረጋግጠዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ እንዳብራሩት፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ አሜሪካ ከወሳኝ አጋሯ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ትሰራለች።
ኢትዮጵያ ቀጣናው ወደ መረጋጋትና ሰላም እንዲመለስ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አመልክተው፤ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መስራት አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ጠንካራ አቋም መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ግዙፍ ብቻ ሳትሆን አቅም እና ተጽዕኖ ያላት ሀገር ነች ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ፤ በቀጣናው መረጋጋትና ሰላም ለማስፈን ሀገራቱ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።