የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 47ኛ መደበኛ ስብሰባ ለ2018 የበጀት ዓመት ሁለት ትሪሊዮን የሚተጋ የበጀት ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ። ምክር ቤቱ በስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ላይ መወያየቱም ተመልክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይፋ እንዳደረው ካቢኔው ሁለቱንም ረቂቆች ላይ ከመከረ በሁዋላ ረቂቆቹን ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አመልክቷል። 47ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች በተራ ቁጥር ተለይተው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዳተመው ከስር ቀርቧል።
1 – በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የ2018 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ነው፡፡ የ2018 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት በጀት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም፤ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ በተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳት አንጻር፤ የ2018-2022 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ እና የ2017 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸምን በመገምገም ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡
በዚሁ መሠረትም ለፌዴራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ወደ ሁለት ትሪሊዮን የሚጠጋ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግስት የ2018 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2 – በመጨረሻም ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው በስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የስታርታፕ ምህዳርን በመፍጠር ስታርታፖች የሚመሰረቱበት፣ የሚንቀሳቀሱበትና የሚያድጉበት እና ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ አዳዲስ ምርቶችን የሚያመርቱበትና አገልግሎቶችን የሚሰጡበት እንዲሁም በዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችል ሆኖ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡