ውጫዊ ጸዳሏ፣ የተላበሰችው ውበትና ማዕረግ ከውስጧ ከሚወጡ እሳቤዎቿ ጋር ተዳምሮ ለንግስና አብቅቷታል። የምግባሯን ቅንጫቢ ያደመጡ ውስጣዊ ወበቷን አክብረውላታል። ከምንም ነገር በላይ አገሯን ከፍ አድርጋ የምታይ፣ የአገሯ ልክ የገባት፣ የአገሯን ልክ ብቻ ሳይሆን የውክልናዋንም ክብደት በቅጡ ያወቀች መሆኗ አገራቸውን ለሚወዱ ሁሉ ድሏን ድርብ አድርገው በአድናቆት እንዲያጎሉት አስገድዷቸዋል፡፡ ይህቺ ምርጥ ኢትዮጵያዊ የሚስ ዎርልድ አሸናፊ ሀሴት ደረጄ ናት።

በሕንድ በተካሄደው 72ኛው ሚስ ወርልድ የቁንጅና ውድድር ኢትዮጵያን የወከለችው ሀሴት ደረጄ ከዓለም ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ በመሆን ማጠናቀቋን ተክትሎ ይፋ በሁኑ መረጃዎች ከአንደበቷ የፈሰሰው ድንቅ ንግግር የድፍሏ ቁልፍ ሚስጢር ነው። ንግግሯ ለውበት ማስደገፊያና የቁንጅና አሸናፊ ለመሆኑ የተደረሰ ሳይሆን የምትኖረው መሆኑ ሀሴትን አድምቋታል።
ውድድሩን መነሻ በማድረግ ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 መሰንበቻ ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርጋ የነበረችው ሀሴት፣ ብርቱ ፉክክር በሚደረግበት ውድድር ሀገርን መወከል ክብር እንደሆነ ስታስታውቅ አገሩን ከፍ በማድረግ ነው። ኃላፊነቱ ከባድ ነው እንደሆነ የጠቀሰችውም በዚህ መረዳት ውስጥ ሆና ነው። ሀሴት ለአገሯ በዓለም አደባባይ የሰጠችው ውዳሴና የታላቅነት ክብር ዘወትር እንደ ዘነዘና ሲደበድቧት ውለው ለሚያመሹ ታላቅ ትምህርት ሆኖ የሚያልፍ ነው። ለአዲሱ ትውልድ ደግሞ ትልቅ አርአያነት ነው።
“ኢትዮጵያን የመሰለች ብዙ ባህልን ከተለያዩ እሴቶች ጋር የያዘች ሀገርን መወከል ትልቅ ክብር ነው፤ ከከባድ ኃላፊነት ጋር የሚሰጥም ነው” በማለት ሀሴት በንንግሯ አመልክታለች።
“ሀገርን በመወከል ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ተግባር በጥንቃቄ መከወን አለበት” የምትለው ሀሴት፣ “ምንም ባደርግ ‘ሀሴት አደረገች’ ሳይሆን ኢትዮጵያ ነው የሚባለው፤ ከስሜ ይልቅ ሚስ ኢትዮጵያ የሚሉኝም ይበዛሉ። ሀገርን እንደመሸከማችን የኢትዮጵያን ስም የሚመጥን፣ ክብሯንም ከፍ የሚያደርግ ተግባራትን መፈፀም ግድ ይለኝ ነበር” በማለት ነበር ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 መሰንበቻ ፕሮግራም ያስረዳችው።
በስፋት ስለ ኢትዮጵያ የምታብራራው ሀሴት፣ ከውድድሩ በኋላም ኢትዮጵያ ለዓለም የምታስተዋውቃቸው በርካታ ፀጋዎች ያሏት ሀገር መሆኗን ጠቅሳ አብዛኛው ዓለም የሰው ዘር እንዲሁም የቡና መገኛ ምድር መሆኗን እንኳን አያውቅም ብላለች።
ተስፋ ሳትቆርጥ በመሥራቷ ሕልሟን እንዴት ማሳካት እንደቻለች የምታስረዳው ሀሴት፣ “ለችግሮች እጅ ባለመስጠት ሕልማችንን እንዴት ማሳካት እንደምንችል ምስክር ነኝ” ብላለች።
ሀሴት በቆይታዋ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች የነቃ ተሳትፎ እንዳላት ገልጻ ይህንን ተግባሯን ሕፃናትን ማዕከል ባደረጉ ጉዳዮች አጠናክራ እንደምትቀጠል በውድድሩ ላይ መናገሯን ኢቲቪ ወደ አማርኛ መልሶ ዘግቧሎ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነችው ሀሴት ደረጄ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 መሰንበቻ ፕሮግራም ጋር ለፍፃሜው ከማለፏ በፊት ያደረገችውን ቆይታ ኮመንትስ ሊንኩን እዚህ ላይ ተጭነው ያንብቡ፡፡