ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በማለት የሚጠራው ስብስብና ደጋፊዎቹ በኢትዮጵያ ሕዝብ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በተደጋጋሚ የጄኖሳይድ ክስ ያለማቋረጥ የሚያሰሙበት ዋና ስልት ይፋ ሆነ። የፕሪቶርያ ስምምነት ማድፈጫ ወይም ማገገሚያ መሆኑን እነዚሁ የትህነግ ክንፎች አረጋግጠዋል፡፡
ራሱን ብቸኛ የትግራይ ሕዝብ ወኪልና ተከላካይ አድርጎ የሚያቀርበው ትህነግ በአገር መከላከያ ላይ የክህደት እርምጃ መውሰዱ በመላው ኢትዮጵያ ቁጣ መቀስቀሱ አይዘነጋም። በተለይም ግፍ የተፈጸመባቸው የመከላከያ አባላት እያነቡ በደላቸውን ሲናገሩ የነበረው የሕዝብ ስሜት መራር ከመሆኑም የተነሳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን በሙሉ ፈቅደኝነት የተቀላቀሉት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነበሩ።

ምርጫ ቦርድ ህልውናውን ገፎ የሰረዘው ትህነግ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደ ማገገሚያ እንደሚጠቀምበት የተገለጸው ከቀናት በፊት በተደረገ የጋራ የዙም ውይይት ላይ ሲሆን፣ ውይይቱን የተዘጋጀው በUTNA ( Union of tigrayans in north america ) እና በገረአልታ ኢንስቲትዩት አማካኝነት እንደሆነ ዝግጅቱን የተከታተሉ አመልክተዋል፡፡
የዙም ምክክር መድረኩ ከላይ የተጠቀሱት ክፍሎች ቢያካሂዱትም፣ ሰነዱ የተዘጋጀው በእነ ዶክተር ደብረጽዮን ትህነግ አማካይነት እንደሆነ ተመልክቷል። UTNA ( Union of tigrayans in north america )እና ገረአልታ ኢንስቲትዩት ሁለት ተመጋጋቢ የትህነግ እህት ቅርንጫፎቹ እንደሆኑ ይታወቃል።
ዜናውን ያሰራጩት ወገኖች እንደሚሉት “ጄኖሳይድ ተፈጽሟል” በሚል በተደጋጋሚ የሚቀርበውን በዙም ስብሰባው “ጄኖሳይድ የፈፀመ አካልና ጄኖሳይድ የተፈፀመበት ህዝብ አንድ ላይ መኖር አይችሉም” በሚል አምባሳደር ፍስሃ አስገዶም በተናገሩት ንግግር ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር ተያይዞ ብቅ ማለቱ ተሰምቷል። ዜናውን ያሰራጩት አምባሳደሩ “ጄኖሳይድ የፈፀመ አካልና ጄኖሳይድ የተፈፀመበት ህዝብ አንድ ላይ መኖር አይችሉም” ሲሉ ንግግራቸው አሁን ላይ አዲስ ቅንጅት ከጀመሩትና በከፍተኛ ወንጅለ፣ አስነዋሪ ተግባራት፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያና አስገድዶ መድፈር የሚከሰሰውን የሻዕቢያዋን ኤርትራን ስለማካተቱ አላብራሩም።
በጦርነቱ ወቅት የትህነግ የውጭ ተወካይ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ፍሰሃ አስገዶም በዙም ምክክሩ ላይ “ትግራዋይ በፕሪቶሪያው ስምምነት አጥር ስር ለመኖር ፍላጎት የለንም” ሲሉ አሳባቸውን አስፍተዋ ማብራራታቸውን ከስብሰባው መረጃ ያገኙ ገልጸዋል።
ፍስሃ አስገዶም “የፕሪቶሪያውን ስምምነት የምንጠቀመው እንደ ማገገሚያ ቤት ነው። የምንጠቀምበት ከበሽታችን ተፈውሰን ሙሉ ጤናችን እስኪመለስልን ድረስ ነው። እናም የፕሪቶሪያው ስምምነትን እንደ ማቆያ የምንጠቀምበት ማገገሚያ ቤት ማለት ነው” በማለት በዙም ምክክራቸው ላይ ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም አማራጭ ስምምነት ትግራይን ገንጥሎ ነፃ ሃገር ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ላይ እስኪደርስ ድረስ ብቻ ለስልት እንደሚጠብቁት አስረድተዋል።
የሩቁ ቢቀር ትህነግ ትግራይን የመገንጠል ዕቅድ ይዞ ይንቀሳቀስ እንደ ነበር በቅርቡ ወ/ሮ ኬሪያ ለርዕዮት በሰጡት ቃለ ምልልስ ገሃድ አድርገዋል። የትህነግ ፖሊት ቢሮ አባልና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ኬሪያ አንቀጽ 39 ክልሎች የሻቸውን መወሰን እንደያስችላቸው የተፈጠረ ህግ መሆኑን እየተማሩ በፖለቲካ ማደጋቸውን አስረድተዋል። ድርጅታቸው ሃምሳ ዓመት ያለ ኮሽታ አገር እንደሚመራና ጊዜው ሲደርስ አንቀጹን ጠቅሶ ፍቺ ሊፈጽም እንደሚችል አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ያደጉበት የአንቀጽ39 አስትምርሆት እንደተባለው ባለመሆኑ “ፌዴራል ሆነን ብዙ ዓመት እንሠራለን፤ ኢህአዴግ ውስጥም የምንከተለውን አዲዮሎጂ እስከ 50 ዓመት ይቆያል የሚል አመለካከት ስለነበር በአብዛኛው የፌዴራሉን ክንድ የሚያፈረጥም ነገር ነበር የምንሠራው እንጂ ክልሎች እንደፈለጉ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን አልገነባንም፤ እንዲሆኑም አላደረግንም፤ ተቋማቱ (የፖሊስ፣ የፍርድቤት ወዘተ ማለታቸው ነው) በፓርቲው ሳምባ ነበር የሚተነፍሱት፤ ባይሆንማ ኖሮ ይህ ሕገመንግሥት እያለ ለምን ጦርነት ውስጥ ገባን” የሚል ጥያቄ “የቆሙ” ላሉዋቸው አለቆቻቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
ይህ ሁሉ ዝግጅት ከከሸፈ በሁዋላ አሁን ላይ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከመጥፋት የዳነው ትህነግ ለሁለት ተከፍሎ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ በተደረገው ውይይት ስምምነቱን “ማድፈጫ” በማደረግ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደሩ አብራርተዋል፡፡
እንደ አምባሰደር ፍሰሃ አስገዶም ትግራይ ተነጥቃለች የሚሉትን ወይም ምዕራብ ትግራይ ሲሉ የሚጠሩትን ክፍል፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት ስር በመሆን ለማስመልስ እንደሚሰሩ መናገራቸውም ታውቋል፡፡ ይህን የሰሙ የአማራ ታጣቂ ኃይሎችም ሆኑ ከትህነግ ጋር እየሰሩ ያሉ ፋኖዎች ምን ለማስፈጸም እንደሆነ ሊያስቡበት እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ትህነግ ከፌደራል ሕግ ጋር የሚጣረስ ስራ እየሰራ፣ የፌደራል ተቋማትን አሰራር እየጣሰ፣ ከመርህ ውጭ ከኤርትራ ጋር እየሰራ መልሶ “የፕሪቶሪያ ስምምነት አልተከበረም” በሚል ደጋግሞ ድምጹን የሚያሰማው ይህንኑ አሁን ይፋ የሆነውን ዓላማውን ለማስፈጸም እንደ ስልት እንደሚጠቀምበት ዜናውን ይፋ ያደረጉ አስታውቀዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብም ሆነ በክልሉ የሚሰሩ ተቀናቃኝ ድርጅቶች የፕሪቶሪያ ሕግ አፈጻጸም ምን ምን ጉዳዮችን እንደሚያካትት፣ ምንን እንደሚከለክል በማጥናት ሕዝቡን እንዲያስተምሩም መክረዋል።
ትግራይን አገር ለማድረግ ምክንያት ስለሚያስፈልግ “ትግራይ ጄኖሳይድ” በሚል በተደጋጋሚ የሚነሳው ለዚሁ አምባሳደሩ በምክክሩ ላይ ይፋ ላደረጉት ስልታዊ እንቅስቅሴ ማስደገፊያ እንደሆነ ያመልከቱ በቅርቡ አሜሪካ የወሰነችውን ውሳኔ አስታውሰዋል። በወቅቱ የተላለፈው ውሳኔ የትህነግ ደጋፊዎችና መሪዎች መቃወማቸውን እነዚሁ ወገኖች ይጠቅሳሉ፡፡ የተቃውሞው መነሻም ጉዳዩ ከላይ ለተገለጸው ምክኛት በመሆኑ እንደሆነ ህጉን ሲቃወሙ የነበሩ ሲያስታውቁ ነበር።
በሁለቱ ወገን የነበረው የክስና መከላከል ሂደት በተጧጧፈበት ወቅት ኢትዮጵያን በጅኖሳይድ ለመጠየቅ በአሜሪካ ሴኔት ቢሮ የታሰበው HR_4350 ውስጥ አንቀፅ 6464 ከረቂቅነት መሰረዙ ሲሰማ በወቅቱ ህጉን ሲቃወሙ ለነበሩ ዜጎች ሰበር ዜና ነበር።
በወቅቱ እንደተሰማው የኢትዮጵያን አሜሪካን ሲቪክ ካውንስል ከከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ለካውንስሉ በላኩት መረጃ አንቀጹ መሰረዙን አስታውቋል።
ኢትዮጵያን በጅኖሳይድ ለመጠየቅ በሴኔት ቢሮ የታሰበው HR_4350 ውስጥ የተሰረዘው አንቀፅ 6464 ከረቂቅ Determination of potential Genocide or crimes Against Humanity የሚለው ነበር።
The “declaration of genocide in Tigray” amendment has been removed from the National Defense Authorization Act (NDAA). የሚለው ዜና ይፋ ሲሆን ካውንስሉ እንዳለው፣ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ዲያስፖራዎች፣ አፍሪካዊያን እና መላው የ NoMore እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ለአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ስልክ በመደወል ኢሜይል በመፃፍ እንዲሁም ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ባደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ ነው።