ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩትን አዲስ ወዳጅነት ተከትሎ ኢህአዴግ ህወሓት በመሪው አቶ መለስ አማካይነት የተፈረመውን የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ አራት ኪሎ ላይ ከወሰነ በኋላ ትግራይ ገብቶ ውሳኔውን የማያውቀው እስኪመስል ድረስ እየሸራረፈ ሲቃወም ነበር። በዚሁ ተቃውሞ ሲያሟሙቅ ቆይቶ በመጨረሻ ባወጣው መግለጫ የሰላም ድርድሩ ግልጽነት የጎደለውን መሆኑንን ለምክንያትነት ካወሳ በኋላ በዋናነት በድንበር ላይ ያለው የአገር መከላከያ ኃይል እንደማይነሳ አቋሙን አስታወቀ።
መከላከያ ሠራዊት የአገር ሃብትና ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት ነው። ታማኝነቱ ደግሞ ለሕዝብና ለሕገመንግሥቱ ሲሆን ዋና አዛዡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። በዚህ እውነትና መነሻ ህወሓት ዘሎ ሰላም ቢወርድም መከላከያው ከድንበር ጠባቂነቱ ንቅንቅ አይልም ሲል አቋም መያዙ የለውጥ ሂደቱን ጡዘት አመላካች ቢሆንም ብዙዎች ልብ ያሉት አይመስልም።

በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ብሮንዊን ብሩቶን ይህ ለብዙዎች ደብዝዞ የሚታያቸውን ጉዳይ ግሩም ትንታኔ በመስጠት Ethiopia and Eritrea Have a Common Enemy በሚል ርዕስ ተሟጋች መጣጥፍ አቅርበዋል። ይህ ማስረጃዎችን በመደርደርና በማጣቀስ በቀረበ ጽሁፍ ላይ ጸሃፊዋ አስረግጠው የሚያቀርቡት ሙግት ህወሃት የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ስጋት መሆኑን ነው። ስጋት የሚሆነበትን ምክንያት በመዘርዘር የቀረበውን ይህንን መነበብ የሚገባውን ትንታኔ ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ወደ አማርኛ መልሶ እንደሚከተለው አቅርቦታል። ትርጉሙ ቀጥተኛና ተዛማጅ የትርጉም ስልትን የተከተለ መሆኑ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን።
ዓቢይ አሕመድና ኢሣያስ አፈወርቂ በፍጥነት ወደ ሰላም እየተጓዙ ነው፤ ምክንያቱም ለሁለቱም የጋራ ስጋት የሆነ ቡድን አለ፤ አክራሪው የህዝባዊ ትግራይ ሓርነት ግምባር (ህወሓት)።
ያለፈው ወር የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ ከኤርትራ ጋር ለሁለት ዐሥርተ ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ወደ ሰላም ለማምጣት መወሰናቸው የዓለምአቀፍን ትኩረት የሳበ ሆኗል። የዛሬ 27ዓመት ኤርትራ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የዛሬ 20ዓመት ሁለቱ አገራት ባካሄዱት ጦርነት ከመቶ ሺህ በላይ ሕዝብ ሞቶበታል። በቀጣይም አቧራማ የሆነችው የባድመ ከተማ በዓለምአቀፉ የድንበር ኮሚሽን ለኤርትራ እንድትሰጥ ከተወሰነ በኋላ ኢትዮጵያ ውሳኔውን አልቀበልም በማለቷ ባድመን ላለማስረከብ ለ20ዓመታት “ሰላም ዓልባ ጦርነት” ውስጥ ቆይታለች። በመጨረሻ የቀደሙት መሪዎች ይከተሉት ከነበረው አካሄድ በማፈንገጥ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ አሕመድ ያለምንም የኢኮኖሚ ቅድመ ሁኔታ ባድመን ለመስጠት ግንቦት 28 ቀን መወሰኑን ባታወቁበት ጊዜ ግጭቱ አበቃ።
በዚህ ውስጥ መራር ጠበኛ መሆን ይገባቸው የነበሩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከዓቢይ አሕመድ አስተዳደር የተላከውን የሰላም ሃሳብ በመቀበል ወደ አዲስ አበባ የሰላም ልዑክ ልከው ነበር። ይህንንም በማድረግ ከዚህ በፊት ፍጹም ሊታሰብ ያልቻለውን የሰላም ሃሳብ ተግባራዊ በማድረግ በአዲስ አበባና በአስመራ አውሮፕላኖቻቸው እስከማብረር ደርሰዋል።
በቀጣይም ዓቢይ አሕመድ ወደ አስመራ ጉዞ በማድረግ በኢሳያስ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን ሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደሚጀምሩ ይፋ አደረጉ። በወቅቱ ጥቂት ዝርዝር ነገሮች የተነገሩ ቢሆኑም ኢሳያስ ግን ከንግግራቸው በአንዱ ዓቢይ አሕመድ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው በገደምዳሜው ገልጸው ነበር። “የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የወሰዱት እርምጃ ቀላል እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም፤ ነገርግን ልናረጋግጥላቸው የምንፈልገው ነገር ቢኖር የወደፊቱን ችግር አብረን የምንጋፈጠው መሆኑን ነው፤ አንድ ሆነን እንሠራለን” ብለው ነበር ኢሳያስ።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የግጭቱ ድንበር በመርህ ደረጃ የተሰመረ በመሆኑ ሰላምን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያን ሠራዊት ከድንበሩ ላይ ከማንሳት ያለፈ ብዙ የሚያስፈልግ ሥራ የለም። አለመታደል ሆኖ በጣም አስቸጋሪው ተግባር ግን ይኸው ጉዳይ መሆኑ ነው – ይህ ደግሞ ከዓቢይም ሆነ ከኤርትራ ጋር ምንም የሚያገናኘው ጉዳይ የሌለው በመሆኑ ነው። ምናልባት ሁኔታውን ከውጭ ለሚከታተሉ አስደንጋጭ ቢመስልም ሁለቱ መሪዎች በእንደዚህ ዓይነት ፍጥነት ለመተባበር የወሰኑበት ግልጽ የሆነ ምክንያት አላቸው። የኅብረታቸው ዋንኛ ምክንያት ዓቅም ያለው የጋራ ጠላት ስላላቸው ነው – ይህም የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ነው።
ዓቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ሲመጡ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ዓመጽ ስትናወጥ ነበር። አገሪቱን ለ27ዓመታት በመዳፉ ሥር በማድረግ እንደፈለገ ሲገዛ የነበረውን ጥቂቶች የመሠረቱትን ምሥጢራዊ የተገንጣይ ቡድን (ህወሓትን) በመቃወም በርካታዎች ሰልፍ ሲወጡ፣ መንገዶችን ሲዘጉ፣ ሱቆችን ሲያወድሙ፣ ወዘተ የቆዩበት ጊዜ ነበር።
ይህ ቡድን (ህወሓት) የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ አገሪቱን ወደቀጣናው ልዕለኃያል ያሳደገ ቢሆንም ይህንን ተግባራዊ ያደረገው ግን በሌብነት፣ የኢትዮጵያን ሃብት በመዝረፍ እና ሚሊታሪውን አናሳ ጎሣ በሆነው የትግሬዎች ቡድን በመዳፉ ውስጥ በማስገባት ነበር።
ህወሓት በጣም ትንሽ ወይም ጥቃቅን ተብሎ የሚጠራ የአናሳዎች ቡድን ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተገደበ ሥልጣንና ኃይል ሊያዳብር የቻለው የድርጅቶች ጥምረት ብሎ በመሠረተው (ኢህአዴግ) እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ቡድን ሥልጣኑን በመጠቀም የሲቪል ማኅበረሰቦችን፣ ፕሬሱን (ሚዲያውን)፣ የሃይማኖት ነጻነትን እና ማንኛውንም ዓይነት የተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድንን ድምጥማጡን አጥፍቷል።
በያዝነው ዓመት አጋማሽ አካባቢ የኦሮሞና አማራ ማኅበረሰቦች በፈጠሩት ጥምረት የአዲስ አበባን መግቢያዎች በመዝጋትና በየቦታቸው መጠነ ሰፊ ተቃውሞ በማሰማት በህወሃት ጠንካራ ምሽግ ላይ ያሳረፉት ጡጫ ሥርዓቱን ወደ ፍጻሜ አቃረበው። በከተማዋና በአካባቢው የደረሰው የምግብና አቅርቦት ዕጥረት እየጨመረ ሲሄድ በወቅቱ ጠ/ሚ/ር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው ሲለቅቁ ኦሮሞው ዓቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መንበሩ እንዲመጡ በር ከፈተላቸው። በቀጣይም በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ከእስር ተለቀቁ፤ ዓቢይም አዲስ ኃይል በመሆን አዲስ የፖለቲካ አሠራር ለመተግበር በህወሓት ተይዞ ነበረውን ሥልጣን ማፈራረስ ጀመሩ።
በተመሳሳይ ጊዜ ኢሳያስም ወደ አዲስ አበባ የሰላም ልዑካን ቡድናቸውን ስለመላክ ሲናገሩ በህወሓት ላይ ያላቸውን ስጋት አልሸሽጉም። እኤአ ሰኔ 20 (ሰኔ 13) ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ እየተከሰተ ስላለው ለውጥ አንድና ሁለት መልካም ቃላት ከመናገራቸው ሌላ በዋንኛነት የንግግራቸው ትኩረት የነበረው “መርዘኛ፣ በጣም አደገኛ፣ (ተንኮለኛና ምቀኛ) ስለሆነው የህወሓት ሌጋሲ” ነበር። ሲቀጥሉም የህወሓት “ጥምብ አንሣዎች” ሥልጣናቸውን እንዳጡ ሲያውቁ በመደናገጥ “አዎንታዊውን ለውጥ ለማጨናገፍ” ይህም በሁለቱ አገራትና በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሠሩ ነበር ኢሳያስ በንግግራቸው ያስታወቁት።
ከትግራይ የሚወለዱት ኢሳያስና ህወሓቶች በጣምራነት አገር ለመገንጠል የሓርነት ትግል አድርገዋል። ሆኖም በኤርትራ ድንበር ላይ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነትና የኢትዮጵያ ሠራዊት በድንበሩ አካባቢ ሠፍሮ መቆየቱ በሁለቱ መካከል የነበረውን ኅብረትና ትብብር አውድሞታል። በህወሃት ሐሳበ ግትርነት ምክንያት ላለፉት 20ዓመታት ኤርትራ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ቆይታለች። ይህም ዜጎች ከአገራቸው እንዲሰደዱ በማድረግ በርካታ ወጣቶች ጉዟቸውን ወደ አውሮጳ እንዲያቀኑ አስገድዷቸዋል።
ዓቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን ያመጣውና በህወሃት ላይ ተጽዕኖ ሳደረው በኢትዮጵያ የተካሄደው ተቃውሞ መሆኑን በማመን የኢሳያስ ንግግር ዋና ዓላማ ኤርትራን (በህወሓት የተጎዳች አገር በመሆኗ) ከኢትዮጵያ ጋር አጋር ማድረግ ነው። ይህ የኢሳያስ ንግግርና የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ መወሰናቸውን ማብሰራቸው በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት ዘንድ “ደፋር አመራር” በሚል ተበረታትቷል። በተለይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በኩል ያገኘችውን አዲስ የትግል አጋርነት በደስታ ነው የተቀበለችው፤ ምክንያቱም ይህ አጋርነት ገና ማሸነፍ በሚጠበቅባት የቀድሞ ጠላቷ – ህወሓት – ላይ የሚከፈት ጦርነት በመሆኑ ነው።
ከኢሳያስ በላቀ ሁኔታ ዓቢይ አሕመድ የህወሓትን አካሄድ የሚፈሩበት ብዙ ምክንያት አለው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የፖለቲካ ተሃድሶ እነዚህ የህወሓት አካሄዶች ወሳኝ ዕንቅፋት ፈጣሪዎች በመሆናቸው ነው። ለዚህ ነው በፍጥነት አፋኙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳት (ህወሓቶችን) ከወታደራዊ ሥልጣናቸው የገፈፋቸው። በመቀጠልም ተቃዋሚዎችን ሁሉ አሸባሪ በማለት የሚኮንኗቸው ህግጋት ላይ ዕገዳ በመጣልና ለውጡን በማፋጠን ስለላና ደኅንነቱን እንዲሁም የሚሊታሪውን (አመራር) ከትግሬዎች በማላቀቅ ኃላፊዎቹን ከሥራ አንስቷቸዋል።
ከዚህ በማስቀጠል በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩት ድርጅቶች በተወሰነ መጠን ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ሒደት የህወሃትን የባንክ ሒሳብ እንዲቀዘቅዝ ሆን ተብሎ የታሰበበት ነው። ምክንያቱም ህወሓቶች (እንደ ሚቴክ ባሉ) ድርጅቶች አማካኝነት ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በሞኖፖል በመቆጣጠር ትርፋማ የሆኑ የመንግሥት ኮንትራቶችን በመውሰድ ራሳቸውን በበርካታ ትርፍ ሲያደልቡ ኖረዋል። በመሆኑን እነዚህና ሌሎች ጥቅማቸው የተነካባቸው የህወሓት አመራሮች ራሳቸውን እንደገና በማሰባሰብ የተቀናጀ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት ዓቢይ ጠንካራና ፈጣን እርምጃ ሊወስድባቸው የግድ ነው። ምክንቱም ላለፉት ሁለት ዓመታት ጌታቸው አሰፋ፣ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ሳሞራ ዩኑስ እና ስብሃት ነጋ ወደ ከፍተኛው የሥልጣን እርካብ ለመውጣት ያደረጉት ሽኩቻ በህወሓት ውስጥ የአመራር ክፍተት እንዲኖር ምክንያት ፈጥሮ ሰንብቷል። እነዚህ አክራሪ የህወሓት ሰዎች ማንኛውንም የተሃድሶ ጥያቄ ሚሊታሪውን በመጠቀም ሲደመስሱ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ለእስር ሲዳርጉ ሁልጊዜ የኖሩ ናቸው። በአንጻሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገነነ በመጣውና ትግራዮችን ፍርሃት ላይ በጣለው የአብላጫው ኢትዮጵያዊ ሊበቀለን ይችላል የሚል ፍርሃቻ እነዚህ ሰዎች የፈለጉትን እንዳይፈጽሙ ገድቦ የያዛቸው ሆኗል።
ለጠ/ሚ/ሩ መጥፎ ዜና የሚሆነው የሚያደርጓቸው ጥረቶች የሚያመጡት ውጤት አናሳ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ምክንቱም ህወሓት 6ሚሊዮንና አናሳ የሆነውን የትግራይ ተወላጅ የሚወክል ድርጅት ቢሆንም ለ27 ዓመታት በሥልጣን ላይ በቆየባቸው አምባገነናዊ ዓመታት ከሌሎች ክልሎች ጋር የፈጠረውና ሥር የሰደደ ጥቅማዊ ወዳጅነት እንዲሁም ከ61 ጄኔራሎች መካከል 57ቱ የትግራይ ተወላጅ መሆናቸው የኢትዮጵያ ድንበር ጠባቂ ኦፊሰሮች ሁለት ሦስተኛው እንዲሁ ትግሬዎች ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ የዓቢይን ሥራ ቀላል እንዳይሆን ከሚያደርጉት ዋንኞቹ ናቸው።
ይህም ቢሆን ዓቢይ አሕመድ የህወሓትን የበላይነት ማሳሳቱን ቀጥሎበታል። እንደ ሳሞራና ጌታቸው ያሉትን አደገኛና ጨካኝ ሰዎችን ከሥራ እንዲለቁ በማድረግ የሚደረገው ተሃድሶ በቀላሉ ሰዎቹ እንዲተኑ አያደርጋቸውም። ከዚህ ሌላ 95በመቶ ትግሬ የሆኑትን ጄኔራሎች በሙሉ ማባረር ለዓቢይ አዋጭ አይደለም። ስለዚህ የሥልጣኑን መንበር ለማጠናከር አደገኛና ጨካኝ የተባሉትን ማባረር፤ አብረውት ለመሥራት የሚፈልጉትን በማስተባበር ዓመታትን መዝለቅ የግድ ይሆንበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀላል የሚባለውን የመጀመሪያ ተግባር በብቃት ተወጥተውታል። ይህም የህወሓት ተምሳሌት የሆኑትን ዓባይ ፀሐዬ፣ ቴድሮስ ሐጎስ፣ ጌታቸው አምባዬ፣ ስብሃት ነጋ፣ ወዘተ እንዲሰናበቱ መደረጉ በጣም ተደጋፊ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች ጠብ መጫራቸው አይቀሬ ነው። ከሥልጣኑ እንዲለቅቅ የተደረገው የቀድሞው ኢንሳ ዳይሬክተር ተክለብርሃን ወልደአረጋይ አዲሱን አስተዳደር “ጠላት” ብሎ በመፈረጅ “ለሕዝቡ የማይጠቅም፣ ለፌዴራል አስተዳደሩ ስጋት” የፈጠረ በመሆኑ በመፈንቅለ መንግሥት መወገድ አለበት በማለት በትግርኛ ቃለምልልስ መስጠቱ ይታወቃል።
ተክለብርሃንና መሰሎቹ ሚሊታሪውን አሳምነው ዓመጽ የማካሄዳቸው ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም ህወሓት በእጅ አዙር ሌሎችን የአካባቢ ኃላፊዎችን፣ የአጋዚ ኃይሎችን እና ሌሎች ብረት ያነሱ ቡድኖችን በመጠቀም ግድያና በብሔሮች መካከል ግጭቶች እንዲነሱ እንደሚተጉ የሚጠረጠር አይደለም። በሰኔ 16ቱ ሰልፍ ወቅት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩን ጨምሮ 30 ተባባሪዎች ተብለው ለእስር መዳረጋቸው አንዱ ተጠቃሽ መሆን የሚችል ነው።
በአሁኑ ወቅት አክራሪ ህወሃቶች በቁጥር እየተበለጡ መሆናቸው እየተሰማቸው ነው ያለው። ቁጥራቸው ገና ጥቂት ቢሆንም የዓቢይን አካሄድ የተቀበሉ የትግራይ ተወላጆች እየመጡ መሆናቸውና አንዳንድ የፓርቲ ሰዎች ስለ ተሃድሶው በግልጽ ድጋፍ በመስጠት መናገራቸው በገሃድ እየታየ የመጣ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አሸባሪ የተባሉት ድርጅቶች ውንጀላው መነሳቱ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታቱ ብቻ ሳይሆን ከዓቢይ ጋር ለመነጋገር መቻሉ እንዲሁም በኦሮሞና ሶማሊ ክልሎ ከሚገኙት ሸማቂዎች ጋር ወደ ሰላም የሚወስዱ ተጠቃሽ ተግባራት መፈጸሙ ዓቢይን ሥልጣኑን እያጠናከረ እንዲሄድ ከሚረዱት ዋንኞቹ ናቸው።
በጠቅላዩ የተወሰዱት እርምጃዎች ከኤርትራ ጋር ስምምነት መፈጸሙም ሆነ ቁልፍ የሆኑትን ጄኔራሎች ማባረሩ ህወሃትን መልሶ የማጥቃት ወይም አጸፋ የመመለስ ተግባር ውስጥ ሊያስገባው ይችላል። ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለይ አሜሪካ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሄዱ በቅርብ መከታተል የሚገባት ተግባር ነው። ምክንያቱም አክራሪ ህወሓቶች በሚሊታሪው ላይ ተጽዕኖ በማሳደር በግድያ (በአሳሲኔሽን)፣ የብሔር ግጭት በመፍጠር፣ ወይም በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የሚቆጣጠሩ ከሆነ ኢትዮጵያ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ መግባቷ አይቀሬ ይሆናል።
ሁኔታው ይህንን ቢመስልም አሜሪካም ሆነች አውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ሁኔታ ብዙም ትኩረት የሰጡት አይመስሉም። የትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪካ በስተቀር በበርካታ ጉዳዮች የተወጠረ ነው። የዓቢይ አስተዳደር የሚያደርገውን ተሃድሶ በለስላሳው ከመመልከት ባለፈ የዋሽንግተንም ሆነ የብራስልስ መሪዎች በውስጥ የሚካሄደውን የሞት ሽረት ትግል እምብዛም ትኩረት የሰጡት አይመስልም። ነገርግን ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች የአውሮጳ ማኅበር ህወሓት ኃይል በመጠቀም ወይም በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚያደርገው ሙከራ በቸልታ እንደማይታይ – የዕርዳታ ድጎማ፣ የሚሊታሪ ትብብርና የፖለቲካ ድጋፍ እንደማይሰጡ በማያሻማ መልኩ ግልጽ አድርገው ለሕዝቡም ሆነ ለህወሓት መልዕክታቸውን ማድረስ አለባቸው። እንዲህ ዓይነቱ የጠነከረ መልዕክት አክራሪ ህወሓቶቹን አደብ እንዲገዙ የሚያደርጋቸው ብቻ ሳይሆን በፀጋ እንዲለቁ መደረጋቸውን አመስግነው እንዲቀበሉ የሚያደርጋቸው ብቸኛ አማራጭ ይሆናል።
የታሪክን አካሄድ ለሚከታተሉ አሜሪካ ሁለቱንም ኃይላት በመደገፍ ኪሣራዋን ለመከላከል እንደምትሞክር የሚካድ አይሆንም። እጅግ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ የደኅንነት ማሽን አሜሪካ ራሷ የፈጠረችው አውሬ ነው። ህወሓት አሸባሪዎችን እንዲዋጋ በሚል ሊቆጠር የማይችል ሚሊዮን ዶላር ፈሶበታል። ህወሓትም ይህንን የሶማሊያ አሸባሪዎችን ለመቆጣጠር የተጠቀመበት ሳይሆን የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪዎችን “አሸባሪ” ብሎ ለመሸበብ የተላከለትን ዕርዳታ ተጠቅሞበታል። ለስቴት ዲፓርትመንት ሰዎች እንደ ዓቢይ አሕመድ ዓይነቱ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅና ለፎቶግራፍ ገጣሚ የሆነ የሰው ፊት ያለው በአዲስ አበባ ሥልጣኑን ቢቆጣጠርላቸው ይመርጣሉ። ነገር ግን የኤርትራን ድንበር ለረጅም ጊዜ ይዛ የቆየችውን፣ ሶማሊያን የወረረችውን እና አስደንጋጭ ሰብዓዊ መብቶችን የጣሰችው ኢትዮጵያ ቸል ሲል ለኖረው ፔንታጎን (መከላከያ ሚ/ር መ/ቤቱ) በአፍሪቃ ቀንድ የፀረአሸባሪነት አጋር የሆነውን (ህወሓትን))ቶሎ ይተዋል ማለት አጠራጣሪ ነው። ይህ ማለት በአንድ በኩል ዓቢይን መደገፍ፣ በሌላ ደግሞ ከህወሓት በተለይም ከአጋዚ ልዩ ጦር ጋር ያለውን ግንኙነት አብሮ በማስኬድ በሶማሊያ ውስጥ የአሸባሪ ዒላማዎችን ማጥቃት ሌላው ተግባር ይሆናል። ስለዚህ ዋሽንግተን ሶማሊያንን አስመልክቶ በአጋዚና ህወሓት ላይ ያለው መመኪያነት ፔንታጎንን በቋፍ ላይ ያስቀምጠዋል።
ኤርትራም በበኩሏ አንዳንድ አደጋዎች ተጋርጠውባታል። ህወሓት ሚሊታሪውንና የዕዝ ሠንሠለቱን የመቆጣጠሩ ሁኔታ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ በግላቸው የኢትዮጵያን ጦር ከድንበር ላይ ለማንሳት ይችሉ ይሆን የሚለውን ገና ግልጽ እንዳይሆን ያደርገዋል። ኢሳያስና ዓቢይ ሙሉ ኅብረት ለማድረግ ተስማምተዋል፤ በዚህ ድርጊት ኤርትራ ራሷን በአጣብቂኝ ውስጥ የከተተች ይመስላል፤ ይኸውም በአንድ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ስታደርግ በሌላ በኩል ግን ድንበሯን ከህወሓት ጥቃት የመጠበቅ ሥራ ላይ እንድትጠመድ አድርጓታል። ምናልባት ይህ ጥቃት ከህወሓት በቀጥታ ባይመጣ እንኳን፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ስምምነት በመፈጸማቸው በርካታ የንግድና የወደብ ገቢ ከምታጣውና ህወሓት ሊጠቀምባት ከሚችለው ጂቡቲ በኩል በእጅ አዙር ሊሆን ይችላል።
ከዚህ ሌላ ኤርትራ የምትከተለውን አስገዳጅ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት በፍጥነት እንድታቆም የማያደርግ የሰላም ስምምነት ለኢሳያስ በአገሩ ውስጥ ትልቅ ችግር እንዲፈጠርበት ሊያደርግ ይችላል። ላለፉት 20ዓመታት በጦርነት ዓውድ ውስጥ የቆየችው የኤርትራ ሕዝብ ለፖለቲካዊ ስምምነትና ለሰላም ታላቅ ናፍቆት ስላለው ብሔራዊ ውትድርናውን አስመልክቶ ፈጣን ለውጥ ጠብቃል። ከዚህ ውጪ ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ በኩል ጥቃት ሊሰነዘርብኝ ይችላል የሚለው አካሄድ በራሷ ላይ ችግር የሚፈጥር ይሆናል።
በኢትዮጵያ የሚደረገው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከከሸፈ ወደ እርስበርስ ጦርነት የሚያመራበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ ኤርትራ ያላት አማራጭ ሁሉንም ነገር ከዓቢይ ጀርባ በመጣል አደጋውን ለመቋቋም መቀበል ብቻ ነው – በተሃድሶ ላይ የሚደረገው ጊዜ እየቆጠረ ነው፤ ከዚህ ሁሉ ዓመታት ቀውስ በኋላ የኤርትራ መንግሥት ምን ያህል እንደተዘጋጀ ለማወቅ ግልጽ አይደለም።
በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል መስፈን የነበረበት ሰላም እስካሁን በጣም ዘግይቷል። ነገርግን አሁን ወደ ሰላም የሚደረገው ጥድፊያ የታክቲክ ጉዳይ መሆኑ ፖሊሲ አውጪዎች ሊረዱት የሚገባ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ዓቢይና ኢሳያስ ኅልውናቸው በህወሓት አማካኝነት አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑ እስከታወቀ ድረስ ልዩነታቸውን ሸፋፍነው በፍጥነት መጓዝ አለባቸው (በጋራ ጠላታቸው ላይ መዝመት ይገባቸዋል)። ዓቢይ የአገር ውስጡን የሥልጣን ሽኩቻ መፍትሔ ላይ ካደረሱና ኤርትራም የፖለቲካ ጉዳዮቿን ካስተካከለችና ኢኮኖሚዋን ወደ ማሳደግ ሥርዓት ውስጥ ከገባች የከዚህ በፊቱ ዓይነት የኢኮኖሚ ቁርሾና ተፎካካሪነት ምናልባት እንደገና ሊያገረሽ ይችል ይሆናል።
በቀጣይ ባሉት አጭር ጊዜያት ወጥመዶችና ዕንቅፋቶች አሉ። ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ፈጣን የሰላም ስምምነትና ጉዞ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሠራዊቱ አባላትን ከድንበሩ እንዲለቅቁ በማድረግ ነጻ ያወጣቸዋል። የእነዚህ ወታደሮች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ግን ምንም የታወቀ ነገር የለም። ከድንበሩ እንዲለቅቁ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ አንቀበልም ይሉ ይሆናል፤ ወይም እንታዘዛለን ብለው ለቅቀው ከወጡ ደግሞ ቀጣዩ ጥያቄ ምን ይሆናሉ የሚለው ነው። ከኤርትራ ጋር የሚፈጸም ሰላም ከሚፈለገው በላይ የተረፈ የሚሊታሪ ብቃትና መጠን እንዲኖር ያደርጋል። ይህ ሚሊታሪ ለኢትዮጵያ የዕዝ ሠንሠለት ይታዘዛል ማለት አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ሚሊታሪውን ወደ ሕዝቡ በሰላም እንዲቀላቀል የመበተኑ ሥራ እኤአ በ2003ዓም በነኢራቅ የባት ፓርቲ አባላት ወታደሮችን ሲበትኑ እንደተከሰተው ዓመጽ ሊነሳሳ ይችላል።
ለጊዜው አክራሪ ህወሓቶችን አሁን ባለው የሕዝብ ቁጣ እየተቆጣጠሩ ማቆየት ይቻላል። ነገርግን ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ ምክንያት ዓልባ ተግባራትን መውሰድ ሊጀምሩ ይችላሉ። ላሁኑ ግን በህወሓት ጓሮ በሚገኘውና በሁሉም መስክ ኃይለኛ የሆነው ጦር ሠራዊት እና አደብ የገዛችው ኤርትራ ለአክራሪዎቹ ህወሓቶች ስንት ጠላት እንዳላቸው በማስታወስ የኃይል ሚዛኑን በመጠበቅ ዕገዛ ያደርጋሉ።