የህወሓት የጥፋት ቡድን ከጤና ተቋማት ዘርፎ የደበቀው አራት ባለተሳቢ የጭነት ተሽከርካሪ ሙሉ መድሃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ በቁጥጥር ስር መዋሉን የመከላከያ ጤና መመሪያ አስታወቀ።
በቁጥጥር ስር የዋለው መድሃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ከሰሜን ዕዝ ሆስፒታልና ከዕዙ ሜዲካል ሎጂስቲክስ የተዘረፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡
መድሃኒቶቹና የሕክምና ቁሳቁሱ ቆላ ተምቤን ልዩ ቦታው ጉሮሮ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው የተያዘው፡፡

የምዕራብ ዕዝ ጤና መመሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ ከፍያለው እንደገለጹት ጁንታው ከሰሜን ዕዝ ሆስፒታል ዘርፎ የደበቀው መድሃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ የተያዘው በመከላከያ ሰራዊት አሰሳ ነው፡፡
መድሃኒቶቹ በውጊያ ጊዜ የሚያገለግሉ ግላቮች፣ የህመምተኛ መታከሚያ አልጋዎችና የተለያዩ አይነት መድሃኒቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
መድሃኒቶቹ ለሰሜን ዕዝ ሆስፒታልና ለዕዞች ይከፋፈላሉ ያሉት ኮሎኔሉ ግዳጆችን በብቃት ለመፈጸም እንደሚያግዙ አስረድተዋል፡፡
ከተያዙት መድሃኒቶች በርካቶቹ ከውጭ አገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የተገዙ በመሆናቸው በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
የህወሓት የጥፋት ቡድን በሰሜን ዕዝ ሆስፒታል ላይ በፈፀመው ዘረፋ ምክንያት እንደ አዲስ ተደራጅቶ ስራ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡ https://www.ena.et/?p=117403
Via ENA