በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ሠላም እንዳይረጋጋጥ እየሠራ ላለው የጥፋት ቡድን መረጃ የሚያቀብሉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የወረዳው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የህዝቦችን ሠላምና አብሮነት የማይልጉ የጥፋት ሽፍታዎች ሰሞኑን በድባጤ ወረዳ ድባጤ ከተማና አካባቢው ወጊያ በመክፈት በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
በድባጤ ወረዳ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ የመከላከያ ሠራዊት የኮማንድ ፖስት አመራሮች፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የወረዳው አመራሮች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የውይይት ተሳታፊዎችም፣ መንግስት በዞኑ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በሽፍታው የጥፋት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን የበላይነት የማረጋገጥ ሥራ በማጠናከር የማያዳግም ርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በአካባው ሠላም እንዳይረጋጋጥ እና ሕዝቡ ተረጋግቶ መደበኛ ሥራውን እንዳያከናውን ለሚያደርገው የጥፋት ቡድን በተለያዩ መንገዶች መረጃ የሚያቀብሉና የጦር መሣሪያ ጥይት አሳልፈው የሚሰጡት አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ መንግሥት ጥብቅ እርምጃ እንዲወድም ጠይቀዋል።
በተጨማሪም፣ መንግሥት የአካባቢውን ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ በቅድሚያ ሽፍታ ቡድኑ እና ተላላኪዎቹ የታጠቁትን የጦር-መሣሪያ ሊያስፈታ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የድባጤ ወረዳ ኮማንድ ፓስት ሰብሳቢ ሻለቃ ዮሐንስ እውነቱ፣ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በጥፋት ቡድኑ ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው፣ ማህበረሰቡ በወሬና አሉባልታ ሳይሸበር ውስጣዊ አንድነትና አብሮነቱን በማጠናከር ለጸጥታ ኃይሉ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከጉሙዝ ማህበረሰብ ወጥተው የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ የሚያስፈጽሙ አካላት በወጡበት ንጹኃን ማህበረሰብ ጭምር ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የገለጹት ሻለቃ የሐንስ፣ ሠላም የሚረጋገጠው በሁሉም ጥረት በመሆኑ ህብረተሰቡ እነዚህን አካላት ከማውገዝ ባለፈ ሊታገላቸው እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
ሻለቃ ዮሐንስ አክለውም፣ የአካባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ሚና እየተጫመተ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ማሳሰባውን የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
Communication office