“የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ከ30 በላይ ምዕመናንን ገድለውብናል፤ ምዕመናን በጾመ ፍስለታ ስጋ እንዲበሉና ወተት እንዲጠጡ በማስገደድ ህብረተሰቡ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ውርደት እንዲደርስበት አድርገዋል”

- መላእከ ሠላም መርጌታ ሙሴ ህሩይ የጋሳኝ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ
የአሸበሪው ህወሓት ታጣቂዎች በፋርጣ ወረዳ የጋሳኝ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አጥቢያ ተገልጋይ የሆኑ ከ30 በላይ ምእመናን መግደሉ ሳያንሰው ምዕመናኑን በጾመ ፍልሰታ አስገድዶ ወተት እንዲጠጡና ስጋ እንዲበሉ በማድረግ ሀይማኖታዊ በደል ፈጽሞብናል ሲሉ የጋሳኝ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ነግረውናል።
በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የጋሳኝ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መላእከ ሠላም መርጌታ ሙሴ ህሩይ በስፍራው ለሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎቹ ከ30 በላይ የጋሳኝ ዙሪያ የደብሩ አጥቢያ ምዕመናንን ገድለዋል። ቅዳሴ ላይ የነበሩ ሶስት የደብሩ አገልጋዮችም ቆስለው የተወሰኑት በህክምና ላይ ናቸው። ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በታጣቂዎች በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ግድግዳና መስኮቶቹ ላይ ጉዳት ደርሶበታል።
በደብሩ አጥቢያ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ ከ30 በላይ ምዕመናን በአሸባሪው ህወሓት በመገደላቸው የፍልሰታ የሱበዔ አገልግሎት በቤተክርስቲያኑ ተቋርጦ እንደነበር አስታውቀዋል።
ታጣቂዎቹ በጾም ወቅት ክርስቲያኖችን እያስገደዱ ሲያስገድፋቸው እንደነበርና የጠቀሱት አስተዳዳሪው፤ በዚህም ምዕመናኑን ወተት እንዲጠጡ፤ ስጋም እንዲበሉ ያስገድዱ ነበር፤ ይህም ከሁሉም በደል የከፋ ሀይማኖታዊ በደል ነው ያሉት የደብሩ አስተዳዳሪ ምእመኑ ከእምነቱ እንዲጣላ፡ አንገቱን እንዲደፋና ማህበራዊና ሃይማኒታዊ ውርደት ለማድረስ አቅደው የሰሩት ነው ብለዋል።
በቅዳሴ ወቅት አሸባሪው ህወሓት በደብሩ ግቢ ውስጥ በጣለው የከባድ ጦር መሳረ ምክንያት የመቁሰል አደጋ የደረሰበት ዲያቆን ሳሙኤል ኢያሱ እንደሚለው፤ በወቅቱ እሱን ጨምሮ ሶስት አገልጋዮች የቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ እንደነበሩና በወደቀው የከባድ መሳሪያ ፍንጥርጣሪ እርሱ ጉልበቱ ላይ ሌሎች ደግሞ እጃቸውና ትከሻቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ህክምና እየተከተተሉ እንዳሉ ዲያቆን ሳሙኤል ተናግሯል፡፡
አሸባሪው ቤተ ክርስቲያንን እንዲህ መዳፈሩ ጸረ ሀይማኖት፣ ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝብ እንደሆነና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ሊያጠፋው እንደሚገባ አመላክቷል፡፡
በአሸባሪው ከተገደሉት ምዕመናን ውስጥ የደብሩ አስተዳዳሪ እናት አንዷ ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡
በአዲሱ ገረመው (ጋይንት)
(ኢ ፕ ድ)