የአፋር ክልል ምክር ቤት የአፋር እና የኢትዮጵያ ሕዝብን ክደው ከሕወሓት የሽብር ቡድን ጋር ያበሩ ጥቂት የቀድሞ የክልሉ አመራሮችን በአሸባሪነት ፈርጇል።
በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ፣ አሁን ላይ ከሽብር ቡድኑ ጋር የተቀላቀሉ ጥቂት ቁጥር ያላቸውን የአፋር ክልል የቀድሞ አመራሮችን ነው ምክር ቤቱ አሸባሪ ሲል የፈረጃቸው።
እነዚህ ቀድሞ ከሕወሓት ጋር የጥቅም ትሥሥር የነበራቸው ጥቂት የቀድሞ የክልሉ አመራሮች ሀገራዊ ለውጡ አስኮርፏቸው ከሽብር ቡድኑ ጋር ማበራቸውን ምክር ቤቱ ገልጿል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የቀረባቸውን ግላዊ ጥቅም ከሕዝብ አስበልጠው ከሕወሓት ጋር ያበሩት እነዚህ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ባንዳዎች የአፋር ሕዝብ ጠላት መሆናቸውን በይፋ አሳይተዋል ብሏል ምክር ቤቱ።
በዚህም እነዚህ ሕዝብ እና ሀገርን የካዱ ባንዳዎች በአፋር እና በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በፈፀሙት ክህደት የደረሰውን ጉዳት ታሳቢ በማድረግም በአፋር ክልል ያለ ሀብት እና ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ሲል ወስኗል።
የአፋር ሕዝብ የአሸባሪ ቡድን ተላላኪዎቹን ባንዳዎችንም ሆነ አሸባሪው ሕወሓትን ከአፋር ምድር ጠራርጎ የሚገባቸውን ቅጣት ለመስጠት እያደረገ ያለውን ርብርብ እንዲያጠናክር፣ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ኢትዮጵያ እና ለሕዝቡ ሲል እንዲዘምትም የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ በሦስተኛው ቀን የምክር ቤቱ ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
በተመስገን ሽፈራው -walata