የኢትዮጵያን መንግስት ለማዛልና ለማንኮታኮት በግብጽ አቀናባሪነት ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ ጋር አብራ ስትሰራ የነበችው ሱዳን ከሱዳን አቋሟን መቀየሯና ተግባብታ ለመስራት ከስምምነት መድረሷ ይፋ ሆነ። በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን መስራት እንደሚገባን መግባባት ላይ መደረሱን ያስታወቁት የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ናቸው። እሳቸው ይፋ ባያወጡትም የሱዳን መንግስት ሲያከናውን የነበረውን ጸረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ለማቆም እንደተስማማ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አስታውቀዋል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አከናውነው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የመንግስት የዜና ምንጮች ጽፈዋል። ጄነራሉን ከሸኙ በሁዋላ “ኢትዮጵያና በሱዳን የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል። አብረንና ተቀራርበን መስራት እንደሚገባን ተግባብተናል” ሲሉ ዶክተር አብርሃም አስታውቀዋል።
ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩና ከኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር መወያየታቸው መገለጹ አይዘነጋም።
ለመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቅርብ የሆኑ እንዳሉት ሱዳን አማጺ ማስታጠቅ፣ ለአማጺ ከለላና መደራጃ መስጠት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን እያደፈጡ እንዲያጠቁ ስታከናውን የነበረውን የውክልና ዘመቻ ለማቆም ተስማምታለች። ዝርዝሩን መናገር ቢያስቸግርም ኢትዮጵያ ቅር የተሰነችባቸውንና የሁለቱን አገራት የቆየ ወዳጅነት ያበላሹትን ጉዳዮች ለማቃናት ጀነራሉ እንደሚቀርፉ ቃል ገብተዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በድንበር አካባቢ የኢትዮጵያና የሱዳን የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ገንቢ ውይይት ማድረጋቸው፣ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ያለ ስጋት እንዲገቡ ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
ከዚህም በተጨማሪ በሱዳን የተነሳውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ የትህነግ ሃይሎች አሉበት የሚባለውን ካምፕ ሱዳናዊያን ገብተው ማውደማቸውና መንግስታቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚያካሂደውን አፍራሽ ድርጊት እንዲያቆም መተየቃቸውን ከሱዳን የአካባቢው ምንጮች ዘግበው ነበር።
በውስጥ የፖለቲካ ቀውስ የተናተችውና በቅርቡ የአሜሪካ፣ እንዲሁም የእስራኤል ባለስልጣናት ለፖለቲካ ስራ የጎበኟት ሱዳን፣ ከጉብኝቱ በሁዋላ በመሪ ደረጃ ሁለተኛ የሚባሉትን ጀነራል መላኳ ለትህነግ አመራሮች ስጋት እንደሆነ ተሰምቷል። ከውይይቱ መካከል አንዱ የሆነው የትህነግ በሱዳን ያከማቸው ሃይል እንደሆነ ያመለከቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጧት ጠይቃላች። አንዱ በሌላው ፋላጎት ላይ እጁን እንደሚያነሳ ስምምነት ከተደረሰ የመጀመሪያው ተግባር የሚሆነው የአማጺያንን የሱዳን መቀመጫ መዝጋትና አሳልፎ ማስረከብ ነው።
በዚህ መነሻ፣ ዘወትር የሱዳን ኮሪዶር እንዲከፈት ለሚወተውቱት የትህነግ አመራሮችና ደጋፊዎች ” በወንድማማችነት አብሮ በጋራ ጉዳዮችና ፍላጎቶች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማምተናል” የሚለው የሁለቱ አገራት የውይይት መቋጫ ዜና፣ ነገ ምን ዜና ይወጣል የሚለውን ጉዳይ አጓጊ አድርጎታል። በኢትዮጵያ ይካሄዳል በተባለው የፖለቲካ እርቅ ምክክር ጉብኤ በምንም መልኩ እንደማይሳተፍ የተገለጸለት ትህነግ ጦሩን እንዲበትንና እንደማንኛውም ክልል ከተራ ፖሊስ የዘለለውን ትጥቅና ሃይል እንዲያሟሟ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ አሜሪካ በመቀበሏ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ በፍጥነት ከስምምነት ላይ ይደረሰ ግንኙነት ይህንኑ የሚያሳልጥ እንደሆነም እየተሰማ ነው።
ትህነግ ተተኳሽና የሰው ሃይሉ ስለላቀ በሱዳን ድንበር ተከፍቶ ተጨማሪ መሳሪያ የሚያገኝበትን መንገድ እያሰላ ባለበት ወቅት የተሰማው የስምምነት ዜና ጸሃይ ለትህነግ ማሞቋን እያቆመች እንደሆነ አመላካች መሆኑም እየተሰማ ነው።
ፎቶ ፋይል