በዩክሬን ድንበር አካባቢ ከ100 ሺህ በላይ ወታደሮቿን ማስፈሯ የሚነገረው ሩስያ ላይ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ኅብረት ጠንከር ያሉ ማዕቀቦችን ጥለዋል። የሞስኮን እንቅስቃሴ ዩክሬንን የመወረር የመጀመሪያው እርምጃ ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሁለት ትላላቅ የሩስያ የፋይናንስ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ እንደሚያግዱና በሩስያ እዳ ላይ አጠቃላይ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።
ይህም ሩስያን ከምዕራቡ ዓለም ፋይናንስ መነጠል ነው ያሉት ባይደን ፑቲን ተጨማሪ እርምጃዎችን መዉስሰድ ከቀጠሉ ደግሞ ተጨማሪ ማዕቀቦች ይጣልባታል ብለዋል። የአውሮጳ ኅብረት ደግሞ ራሳቸውን ከዩክሬን ለገነጠሉት የዶኔትስካና ሉሃንስክ ግዛቶች እውቅና በሰጡት 351 የሩስያ ምክር ቤት ዱማ አባላትና በሌሎች 27 የሩስያ ባለስልጣናት እንዲሁም በመከላከያና በባንኩ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ጥሏል። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ማዕቀቡ «ኬሬምሊን ጥቃትዋን እንዳትቀጥል በተቻለ መጠን አስቸጋሪ ያደርግባታል ብለዋል።
ሞስኮ የሚገኙ አምባሳደሯን የጠራችው ዩክሬን ከሩስያ ጋር ያሏትን ግንኙነቶች ለማቋረጥ እያሰበች ነው ተብሏል። የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዩክሬን ዜጎች ወደሩስያ እንዳይሄዱና ሩስያም የሚገኙ 3 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ሀገራቸው በአስቸኳይ እንዲገቡ መክራለች። ሩስያም አምባሰr/ን ከክየቭ ጠርታለች። የዩክሬን ብሔራዊ የፀጥታና የመከላከያ ምክር ቤት በመላ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነግ ሃሳብ አቅርቧል። ሩስያ ክየቭ ወደ 50 ሺህ የሚጠጋ ተጠባቂ ጦሯን ጠርታለች።
የተባባሰው የዩክሬን ሩስያ ቀውስ
የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ራሳቸውን ከዩክሬን ለገነጠሉትና ሪፐብሊኮች ነን ለሚሉት ሁለት ግዛቶች የሰጡትን እውቅና የሩስያ ምክር ቤት ዱማ ካጸደቀና ሩስያም ከሀገርዋ ውጭ ወታደራዊ ኃይሎቿን እንድታስገባ ከፈቀደ በኋላ የሩስያና ዩክሬን ቀውስ ተባብሶ ቀጥሏል።ውጥረቱን ለማብረድ ከዚህ ቀደም ሲሞከር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አሁን ተስፋ ያለው አልመሰለም።
ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት የሩስያን እርምጃዎች ወራራ ማለት ከጀመሩ በኋላ ሁኔታዎች ተቀይረዋል።ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን ከሩስያ አቻቸው ጋር ሊያካሂዱት የነበረው ውይይት መሰረዙን አሶስየትድ ፕሬስ ዘግቧል። የአውሮጳ ኅብረትም የሩስያ ምክር ቤትን ውሳኔዎች በእጅጉ ተቃውሟል። የኅብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ውሳኔዎቹን ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሱ ብለዋቸዋል። «የዩክሬን ግዛት ለሆኑት ለዶኔትስክና ሉሃንስክ ሩስያ እውቅና ለመስጠት መወሰንዋ ሕገ ወጥ እና ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው። ወደነዚህ ግዛቶች ወታደሮችዋን ለመላክ መወሰኗም እንዲሁ። ውሳኔው የዩክሬንን አንድነት እና ሉዓላዊነት ይጻረራል።
ሩስያም ዓለም አቀፍ ግዴታዎቿ ካለማክበርዋም በተጨማሪ የዓለም አቀፍ ሕግጋትን ቁልፍ መርሆች የጣሰ ነው።» የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተሬም ሩስያ ለሁለቱ የምስራቅ ዩክሬን ግዛቶች እውቅና መስጠቷን የግዛት ሉዓላዊነትን የሚጥስ ሲሉ አውግዘዋል።ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጨማሪ ደም ሳይፈስ የዩክሬንን ህዝብ ለመታደግ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል። ሩስያ በበኩልዋ ጉተሬሽን ስለ ዩክሬንና ሩስያ ቀውስ የሰጡትን አስተያየት ደረጃቸውን የማይመጥን ሲሉ የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ነቅፈዋል።
«በሚያሳዝን ሁኔታ የተመድን የሚወክሉት ዋና ፀሀፊው በምዕራባውያን ተጽእኖ ስር ወድቀው ምስራቅ ዩክሬን ውስጥ ስለሚሆነው የሰጧቸው መግለጫዎች በተመ ድርጅት የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት ደረጃቸውንና ስልጣናቸውን የማይመጥን ነው።» ላቭሮስ ጉተሬሽ ገልለተኛነታቸውን ጠብቀው ሊጓዙ ይገባል ሲሉም ማሳሰባቸውን ዶቼቬሌ ዘግቧል።
ጃፓንና አውስትራሊያ በሩሲያ ላይ መዓቀብ ጣሉ

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለወሰደችው እርምጃ አጸፋ የሚሆን መዓቀብ ጃፓን እና አውስትራሊያ እንደጣሉ ታውቋል። ሁለቱ ሀገራት ቀደም ብለው ውሳኔዎችን ያስተላለፉትን ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ካናዳ እና ጀርመንን ተቀላቅለዋል። አውስትራሊያ ምንጊዜም በጉልበታቸው ከሚመኩት በተቃራኒ እንደምትቆም የተናገሩት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስር ስካት ሞሪሰን
“ከሁሉም አጋሮቻችን ጋር በመሆን ሩሲያን እንጋፈጣለን!” ብለዋል። ተከታታይ ማዕቀቦች እንደሚጠበቁ እና ይሄም የሂደቱ ጅማሬ መሆኑን ተናግረዋል።
የአውስትራሊያ መዓቀብ በሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት አባላት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ጃፓን በበኩሏ የተመረጡ የሩሲያ ዜጎች ሀብት እንዳይንቀሳቀስ፣ እና የሩሲያ ቦንድ ሽያጭ በግዛቷ እንዳይካሄድ ወስናለች።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ፕሬዚደንት ዲሜትሮ ኩልባ፣ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚርን ተጨማሪ ቅጣት ለማስቆም ከዚህም ከረረ ያለ ማዕቀብ በአስቸኳይ እንዲጣል አሳስበዋል። በትናንትናው ዕለት ለተወሰዱት እርምጃዎች ምስጋናቸውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ላይ ፑቲንን ለማስቆም ጫናው መጠናከር አለበት። ዛሬውኑ ኢኮኖሚው እና አጋሮቹ በብርቱ ሊመቱ ይገባል” ብለዋል።
የዩክሬን ጦር ዛሬ ረቡዕ ዕለት በሩሲያ በሚደገፉ በሉሃንስክ ቀጠና በሚገኙ ተገንጣዮች በተሰነዘረ ጥቃት አንድ የዩክሬን ወታደር እንደተገደለ እና ተጨማሪ ስድስት ሰዎች እንደተጎዱ የዘገበው ቪኦኤ ነው።