ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳኖቭ ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው ፈርጀ-ብዙ የሆነውን የሁለቱን ሀገራት ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በኢነርጂ፣ መሰረተ ልማት፣ ግብርና እንዲሁም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በሁለቱ አገራት ትብብር ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚከናወኑ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶችም ተወያይተዋል።
የጋራ ጥቅምን በሚመለከቱ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ሁነቶች ዙሪያም ሃሳብ የተለዋወጡ ሲሆን በዚህም በተመድ እና ሌሎች ባለብዙ ግንኙነት መድረኮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በአፍሪካ የሚያጋጥሙ ግጭቶች እና ቀውሶችን በዓለም አቀፍ ሕግ እና የተመድ ቻርተር አግባብ መፍታት እንደሚገባም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በ2022 ስለሚካሄደው 2ኛው የሩስያ-አፍሪካ ጉባኤ ዝግጅትም አንስተው ተወያይተዋል።
የሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳኖቭ የሩስያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪካ ልዩ ተወካይም ናቸው። EBC