የአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አጋርነት አደጋ ላይ ከመውደቅ ታድጎናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
ዛሬ በተጀመረው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያለፈው አንድ ዓመት ለኢትዮጵያ ከባድ እንደነበር ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ውስጥ መቆየቷን ለጉባኤው የገለፁ ሲሆን ሀገሪቱ ስታከናውነው በነበረው ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን ለመቀነስ የተቻላትን ሁሉ ማድረጓን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር መንግስት የሀገሪቱን ሰላም ለመመለስ ያስችል ዘንድ ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር ይገኙ የነበሩ ግለሰቦችን ክስ ማቋረጡን እና አካታች የሆነ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
አለም አቀፍ ሚዲዎች አፍሪካን በጎ ባልሆነ መልኩ የረሀብ፣ እርስ በእርስ ጦርነት፣ ሙስና፣ በሽታ እና ድህነት መገለጫ አድርገው በዓለም አቀፉ መድረክ ላይ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አለም አቀፍ ሚዲያዎች አፍሪካውያን እራሳችንን የምናይበትን መንገድ ጨምር እያነፁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን የሚቀለብስ የሚዲያ አማራጭ በህብረቱ አማካኝነት እንዲመሰረት ለጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህም አህጉሪቱ ላይ የሚሰነዘሩ የተዛቡ መረጃዎችን መዋጋት፣ የራሳችን አጀንዳ ማቅረብ እና የፓን አፍሪካኒዝም ድምፅን ማሰማት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የመስኖ ልማት እንቅሰስቃሴዎችን በማከናወን ለአርሶ አደሮቿ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቷን እና ለሀገሪቱ ቀዳሚ የምግብ ዋስትና ስጋት የሆነው የደን መመናመንን በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አማካኝነት ስትመክት መቆየቷን በጉባኤው አውስተዋል፡፡
በዚህም በመጪው ክረምት አራተኛ አመቱን በሚይዘው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአጠቃላይ 25 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላ እንደምታጠናቅቅ ገልፀዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ተገልላ እንደምትገኝ በመጥቀስም አህጉሪቱ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቢያንስ 2 ቋሚ እና 5 ቋሚ ያልሆነ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡ EBC NEWS