በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦችን ኢላማ ያደረጉ አሉታዊ መረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ ይሰራጫሉ። በተለይም ፓለቲካ እና ሀይማኖትን የመሳሰሉ ስሜት ቀስቃሽ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የሚያደረጉ አካላት የአሉታዊ መረጃዎች ዋነኛ ኢላማዎች ናቸው። ይህ ጥናት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማዕከል አድርገው በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚደረጉ የአሉታዊ መረጃ ዘመቻዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና አንድ በክልል ስልጣን ላይ ያለን ፓርቲን እንደ ማሳያ ጥቅም ላይ ውሏል።
ለዚህ ፅሁፍ በአጠቃላይ ከ2011 እስከ 2013 መጨረሻ ባለው ወቅት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተሰራጩ 880 አሉታዊ መረጃዎችን ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን እነዚህም አሉታዊ መረጃዎች ከ166 ሺህ በላይ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን በአስተያየት፣ በማጋራት፣ እና በስሜት ምላሽ መልክ ያሳተፉ ናቸው። ከዚህ ውስጥ 56% የአማራ ብልፅግና ፓርቲ፣ 23% አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ 10% የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ 7% ያህሉ ባልደራስን የተመለከቱ ሲሆን የተቀረው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጋራ ኢላማ ያደረጉ ናቸው። በተጨማሪም 381 አካውንቶች እነዚህን አሉታዊ መረጃዎችን በመፍጠር እና በማሰራጨት ላይ ተሳትፎ አድረገዋል። ከነዚህ ውስጥ 54% የአማራ ብልፅግናን፣ 34% አብን፤ 19% ኢዜማን፣ 8% ባልደራስን እንዲሁም የተቀሩት አካውንቶች የተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎችን በጣምራ የአሉታዊ መረጃዎች ኢላማ አድረገው አቅርበዋል። በአጠቃላይ እነዚህ አካውንቶች ከ22 ሚሊዬን በላይ ለሚሆን ተጠቃሚ ተደራሽ የሆኑ ናቸው።
ለዚህ ጥናት ጥቅም ላይ ከዋሉ 880 አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 74% የሚሆኑት ሀሰተኛ መረጃዎች፣ 4% የጥላቻ ይዘት ያላቸው መረጃዎች እና 22% ደግሞ ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ናቸው። ከሀሰተኛ መረጃዎች ውስጥ 84% የፈጠራ ይዘት ያላቸው ሲሆን 16% ደግሞ አሳሳች ይዘት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል። ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ካላቸው አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 64% እነዚህ የፓለቲካ ድርጀቶቹ እና አባላቶቹ ላይ አደጋ እንዲደርስ የሚያነሳሳ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ 30% ተቃውሞን እና ሽብርን የሚቀስቀሱ 5% ደግሞ ግጭት እና የሽብር ጥቃቶችን የሚያሞግሱ እና የሚያወድሱ ናቸው። በተጨማሪም የጥላቻ ይዘት ካላቸው አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 48% ማንነት ላይ ያተኮሩ ፀያፍ የጥላቻ ስድቦች ፣ 26% ደግሞ የፓለቲካ ፓርቲ አባላነትን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ፣ 16% የንቀት እና ማንነትን ዝቅ የሚያደረጉ እና 10% ሰብአዊ ማንነትና ክብርን የሚያዋርዱ ይዘት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።
የሀሰተኛ፣ ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ይዘት ካላቸው 880 መረጃዎች ውስጥ 59% የአማራ ብልፅግና ፓርቲን የተመለከቱ ሲሆን የተቀሩት 41% መረጃዎች የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ኢላማ ያደረጉ ከእነዚህ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ኢላማ ካደረጉ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 20% አብንን፣ 10% ኢዜማን፣ 5% ባልደራስን ኢላማ ያደረጉ አሉታዊ መረጃዎች ሲሆኑ 2% ደግሞ እናት ፓርቲ እና ኦፌኮ እንዲሁም የተቀረው 4% መረጃዎች የተለያዩ ፓርቲዎችን በጋራ ኢላማ ያደረጉ መረጃዎችን የያዙ ናቸው።
የአማራ ብልፅግና ፓርቲን ከተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 67% ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሆኑ 30% ግጭት ቀስቃሽ እንዲሁም የተቀረው 3% መረጃ ደግሞ የጥላቻ ይዘት ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ናቸው። ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ካላቸው መረጃዎች ውስጥ 95% የቡድኑ አባላት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ጥሪ የሚያደርጉ እና ብጥብጥ ቀስቃሽ መረጃዎች ሲሆኑ የተቀረው ደግሞ ብጥብጥና ግጭትን የሚያወድሱ መረጃዎችን የያዙ ናቸው።
የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ኢላማ አድርገው ከተሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ 84% ሀሰተኛ መረጃዎች፣ 10% ግጭት ቀስቃሽ እና 6% ያህሉ ደግሞ የጥላቻ ይዘት ያላቸው ልጥፎች ሆነው ተገኝተዋል። ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ካላቸው መረጃዎች ውስጥ 87% የድርጀቶቹ አባላት እና ቤተሰቦች ላይ ጉዳት እንዲደርስ የሚቀሰቅሱ እና በአጠቃላይ ብጥበጥን የሚያበረታቱ መረጃዎች ናቸው።
በተጨማሪም የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የተመለከቱ የጥላቻ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ሙሉ በሙሉ በፓለቲካ ፓርቲዎች አባላት ማንነትን ማዕከል ያደረጉ የፀያፍ ቃላትን፣የንቀት ቋንቋን የሚጠቀሙ እና ሰብዓዊነትን የሚያሳንሱ የጥላቻ ንግግር አይነቶች ናቸው። (ምስል 2)

አሉታዊ መረጃዎቹ ከይዘት አንፃር በዋነኝነት እነዚህን አሉታዊ መረጃዎች የሚያሰራጩ አካላት ያላቸውን አላማ ለማሳካት ወቅታዊ ሁኔታዎችን እየተከተሉ ስሜት ቀስቃሽ ይዘት ያላቸውን አሉታዊ መረጃዎችን በመፍጠር እና በማሰራጨት ላይ ሲሰሩ ይስተዋላል። በተጨማሪም ተመሳሳይ አጀንዳን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የሚያሰራጩ አካላት በብዛት እንዳሉ መታዘብ ተችሏል። በዚህ ጥናት ላይ ከተስትዋሉ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ ከመረጃዎቹ ብዛት እና የተሳትፎ ምጣኔ አንፃር በዋነኝነት 6 የፓለቲካ ፓርቲዎችን ኢላማ ያደረጉ ሲሆን እነዚህም አብፓ፣ አብን፣ ኢዜማ፣ እናት ፓርቲ፣ ባልደራስ እና ኦፌኮ (የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ) ሆነው ተገኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ፓርቲዎችን በጣምራ በማካተት ኢላማ አድርገው የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በብዛት እንዳሉ ለመታዘብ ተችሏል።
የአማራ ብልፅግና ፓርቲን የተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎች አብዛኛው ይዘት የሚያጠነጥነው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ እና የፌድራል መንግስቱን ከሚመራው የብልፅግና ፓርቲ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተገናኙ ሴራ ተኮር መረጃዎች ላይ ነው። እነዚህም በዋነኝነት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አባል የሆነበት እና የፌድራል መንግስቱን እየመራ ያለው የብልፅግና ፓርቲ በተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ ለተፈረጀው አነግ ሸኔ የቁስቁስ፣ የገንዘብ እና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን እንደሚያደርግ የሚጠቅሱ እና የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ለዚህ ተግባር በማወቅም ይሁን በአቅም ማነስ የተነሳ የተባባሪነትን ሚና ይጫወታል የሚል ይዘት ያላቸው አሉታዊ መረጃዎች ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያየዘ የፌድራል መንግስት የአማራ ክልል የተለያዩ አመራሮችን እያስወገደ ነው የሚል እና የፌድራል መንግስት ከህዋሃት ጋር በትብብር በመሆን የአማራ ማህበረሰብ ላይ እስከ ዘር ማጥፋት የደረሰ ጉዳቶች እንዲደርስበት እያደረገ ነው የሚል ይዘት ያላቸው ሀሰተኛ መረጃዎችን ያካትታሉ። በተጨማሪም በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አባላት መካከል ውስጣዊ ግጭት ተከስቷል፤ በድርጅቱ እና በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ መካከል ውዝግብ አለ፤ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ በህቡዕ ለህዋሃት ትብበር ያደርጋል እንዲሁም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አንድ ክንፍ ነው የሚል ይዘት ያላቸው ልጥፎችን በማህበራዊ ሚዲያው ሲሰራጩ በዚህ ጥናት ላይ ማስተዋል ተችሏል።
ሌላው የአሉታዊ መረጃዎችን የጭብጥ ሀሳብ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ እና በሚያስተዳድረው ክልል ነዋሪ መካከል እምነት እንዳይኖር የማድረግ አላማን ያነገቡ ሀይሎች የሚጠቀሙባቸው መልከ ብዙ የሆነ ይዘት ያላቸው አሉታዊ መረጃዎችን ሲሆኑ ይህንን መሰል ልጥፎች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በአብዛኛው በአማራ ብልፅግና ፓርቲ ላይ ያለ ምንም እንዲሁም በቂ ማስረጃ የክስ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ናቸው። በዚህ ጥናት ላይ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የሚወክለውን የአማራ ክልል ማህበረሰብ ሰላም እና ፀጥታ ለማስከበር ፋላጎት የለውም፤ በቅማንት፣ አገው፣ ቤንሻንጉል፣ ኦሮሞ ብሄረሰቦች እና በመስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እያደረሰ ነው፤ በአማራ ማህበረሰብ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚደረሱ ጥቃቶች በቀጥታ እና በተባባሪነት ተሳትፎን እያደረገ ነው፤ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የስልጣን እርከን የተቆጣጠሩት የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አካለት ላይ በተለይም የአብን እና ፋኖ አባላትን በማሰር፣ በማንጋላታት እና በመገደል ላይ ተሳትፎን ያደርጋል ከዚሁ ጋር ተያይዞ የክልሉ ልዩ ሀይል ላይ የተለያዩ ህቡዕ ሴራዎችን እና ቀጥተኛ ጉዳቶችን እንዲደርሱበት በተለያየ መንገድ ይሞክራል የሚሉ ውንጅላዎችን በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲሰራጩ ለመታዘብ ተችሏል። በመጨረሻም የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ጥቃት እንዲደርስ የሚቀሰቀሱ ብጥብጥ ቀስቃሽ መረጃዎችም በከፍተኛ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲሰራጩ ይስተዋላል።
- አማራ በየቀኑ ዐቢይ አሕመድ ባስታጠቀው የኦነግ ጦር በመቶዎች እየተጨፈጨፈ ያለው ብአዴን ከሰው በታች እንደ ውሻ እንዲታይ ስላደረገው ነው! ከ160 በላይ የአማራ ተወላጅነት ያላቸው ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞች፣ አልጋ ላይ የዋሉ ሕሙማንና የሃይማኖት አባቶች ዐቢይ አሕመድ ባስታጠቀው የኦነግ ጦር በምዕራብ ወለጋ ዞን በባቡ ወረዳ ሰደቃ ቀበሌ ውስጥ ተጨፍጭፈው አድረዋል። ሽመልስ አብዲሳ “አማርኛንና አማራን አጥፍተን ኦሮሞኛን በአማርኛ ላይ የበላይ በማድረግ አማርኛ የማይነገርባትን አገር እየገነባን ነው” በማለት በአማራ ላይ እልቂትና የሞት ድግስ ካወጀ ወዲህ በተለይም በሻሸመኔ፣ በሐረርጌ፣ በዝዋይ፣ በወለጋ፣ ወዘተ በየቀኑ በመቶዎች በሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እየተካሄደ ያለው የግፍ ጭፍጨፋ የአማራ ሕዝብ በአማራነቱ የበደል ሀሞት ከተጎነጨባቸዉ ዘመናት ሁሉ በላይ እጅግ የተዋረደበትና ከሰው በታች እንደ ውሻ የታየበት ብቸኛው ጥቁር ጊዜ ነው። የአማራ ሕዝብ ከሰው በታች እንደ ውሻ ከታየበት ጥቁር ጊዜ መውጣት የሚችለው ከሰው በታች እንደውሻ እንዲቆጠር ያደረገውን፤ በልቶ ማደርን ብቻ የሕይዎት መመሪያቸው ያደረጉ የአማራ ርግማኖችና አማራ መቃብሩን ፈንቅሎ እንዳይወጣ መቃብር ጠባቂ እንዲሆኑ የተፈጠሩ የአማራ ባንዶች ድርጅት የሆነውን ብአዴንን በቅድሚያ ሲነቅል ብቻ ነው። ብአዴን የሚባለው የአማራ ርግማን በአማራ ሕዝብ ላይ ተጭኖ እስከቀጠለ ድረስ አማራ ከሰው በታች እንደውሻ መታየቱና በየዕለቱ በመቶዎች መጨፍጨፉ ይቀጥላል። ባጭሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ሕጻናትን፣ ሴቶችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አልጋ ላይ የዋሉ ሕሙማንና የሃይማኖት አባቶችን ዐቢይ አሕመድ ካስታጠቀው የኦነግ ጦር ጭፍጨፋ መታደግ የሚቻለው አማራን ከሰው በታች እንደውሻ እንዲታይ ያደረገውን ብአዴን የሚባል የአማራ ርግማን ከሰንኮፉ ደም በሚያስተፋ ቁጣና ንዴት ማስወገድ ሲቻልና አዲስና ሊቀለበስ የማይች ሕዝባዊ እምቢተኝነት መቀስቀስና ሕዝባዊ ማእበል በማስነሳት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ መታረጃ ቄራው የሆነችበት አማራ ብአዴን እስካለ ድረስ አማራን መታደግ እንደማይቻል ተስፋውን ቆርጦ መተማመን በመፍጠር በቃኝ ብሎ እስካልተነሳ ድረስ በየዕለቱ የሚደርስበትን ብሔራዊ ሐዘን ሳይጨርስ አማራን ከሰው በታች እንደውሻ ቆጥረው የግፍ ሁሉ መሞከሪያ ያደረጉት ጠላቶቹ ተጨማሪ ውርደት በዕየለቱ ይዘውለት እየመጡ ሲጫወቱበት መኖራቸው አይቀሬ ነው።
- ብአዴን ለሁለት ከተሰነጠቀ ቆይቷል፣ ከአዲስ አበባ ደመቀ መኮንንና ላቀ አያሌው የተካተተበት፣ ወርቁ አይተነው ስፖንሰር እያደረገው አበረ አዳሙ የሚመራው አንደኛው ፍንካች ነው፣ ሌላኛው ርዕሰ መስተዳድሩ አገኝሁ ተሻገር የሚገኝበት “ቀሪው” ብአዴን ብላችሁ ልትይዙት ትችላላችሁ፣ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ፍጥጫ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፣ አበረ አዳሙ ወታደሩንና ፀጥታውን እንደያዘው ነው፣ ያሻውን ማድረግ ይችላል፣ አንድም በገንዘብ ካልሆነም በመሳሪያ በርከት ያሉ ሰዋችን ከጀርባው ሊያሰልፍ ይችላል፣ ወደ ፌደራል አቤት አይባል ነገር ምክትል ጠ/ሚ ተብሎ የተቀመጠው ደመቀ መኮንን የጎጃሙ ቡድን አባል ነው፣ በዚህ ምክንያት አገኝሁ አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ይሰማኛል። …
- ብአዴንን ቀድሞ ማስወገድ የመጨረሻም የመጀመሪያም የአማራን ህልውና መታደጊያ የትግል መስመር ነው።ፋሽስት ወያኔም ሆነ ወራሪ ተስፋፊው ኦሮሙማ ብልፅግና አማራን የሚጨፈጭፉት ብአዴንን ተጠቅመው ነው።ይሄ መረዳት የማይችል አማራ የብአዴን ዲቃላ ወይም ተከፋይ ባንዳ ነህ።ዋና ጠላትን ብአዴንን አዝሎ በታዛዥ ግለሰቦች ታየ ሽመልስ አሻድሊ ወዘተ እያሉ እዚህም እዛም መጮህ ደንቆሮነት አይገልፀውም!!!!አማራ እራሱን ከብአዴን ነፃ ካወጣ ከፊለፊቱ ማነው የሚቆመው መልስ ያለው ደንቆሮ ካለ????
- #የአዴፓ_ፀረ_አማራ_ቫይረሶች አማራ በፀረ አማራ ቫይረስ የተሞላውን ብአዴንን ነቅሎ ሳይቀብር ሰላም ክብርና እድገትን አያይም። …. በፀረ አማራ ቫይረስ የተያዘው ብአዴንን አማራው ከስሩ ነቅሎ ወደ መካነ መቃብር መላክ ይገበዋል-!!!!
በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚሰራጩትን የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎች ስንመለከት ደግሞ በዋነኝነት ሁለት አይነት ባህሪ አላቸው። አንደኛው አንድ ፓርቲ ላይ ብቻ በማተኮር ፓርቲውን በተመለከተ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ በተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለ ወይም ይኖራል ተብሎ በሚታሰበው ርዕዮተ አለማዊ እንዲሁም ፓለቲካዊ እና ማህበራዊ አንድነት እና የአቋም ስምምነት ላይ በመመርኮዝ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎችን በጣምራ በመጠቀስ በእነሱ ዙሪያ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ናቸው። የመጀመሪያውን አይነት ማለትም በተናጠል አንድ ፓርቲ ላይ በማተኮር የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ስናይ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በዋነኝነት ትኩረት የተሰጣቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቅደም ተከተል አብን (178) ፣ ኢዜማ፣ ባልደራስ፣ እናት ፓርቲ እና ኦፌኮ ናቸው። ሁለተኛው አይነት ማለትም በፓርቲዎቹ መካከል የአቋም ስምምነት/አንድነት አላቸው ተብሎ በጋራ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ በጣምራ በብዛት የምናገኛቸውን ፓርቲዎችን ስናይ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚጠቅሱ አሉታዊ መረጃዎች ላይ በዋነኝነት የአብን/ባልደራስ (13) ፤ ኢዜማ/ባልደራስ (6) ፤ አብን/ኢዜማ (6) እና አብን/እናት ፓርቲ (1) ጥምረት በብዛት ይገኛል። ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚጠቅሱ አሉታዊ መረጃዎች ላይ ደግሞ የአብን/ኢዜማ/ባልደራስ (7) ጥምረት በብዛት ይገኛል፤ በተጨማሪም አራት እና ከዚያ በላይ የተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲዎችን በሚያሰራጩት አሉታዊ መረጃዎች ላይ የሚጠቅሱ የአብን/ኢዜማ/ባልደራስ/እናት (2) እና አብን/ኢዜማ/ባልደራስ/ኦፌኮ ጥምረት (2) በብዛት ይገኛል። ይህም አብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ የአሉታዊ መረጃዎች ትኩረት በከፍተኛ ደረጃ አብን ላይ ሲሆን በመቀጠል ኢዜማ እና ባልደራስ ተከታይ ቦታዎችን እንደያዙ የሚያሳይ ነው።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ አብዛኛው አብን የተመለከቱ ሲሆን በይዘት ደረጃ በቀዳሚነት የሚሰራጨው አብን ላይ ክስን የሚያቀርቡ አሉታዊ መረጃዎች ሆነው አግኝተናቸዋል። ከሀሰተኛ መረጃዎች ውስጥ አብንን በተለያዩ ክልሎች በተለይም በቤንሻንጉል፣ አማራ እና ኦሮሚያ በሚደርሱ ግጭቶች ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን እና በተናጠል ቀጥተኛ ተሳታፎ እያደረገ ነው የሚል ይዘት ያላቸው እና ከዚሁ ጋር ተያይዞም አብን በአማራ ክልል በሚኖሩ ሙስሊሞች ላይ ጥቃት እያደረሱ እና እንዲደርስ እየቀሰቀሱ ነው የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎች በቀደሚነት ሲቀመጡ በተጨማሪም የአብንን ፓለቲካ የሚዘውሩት የአንድ አካባቢ ፖለቲከኞች ስለሆኑ ሁሉንም አማራ የሚወከል ድርጅት አይደለም የሚል ይዘት ያላቸው አሉታዊ መረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ ሲሰራጩ ለማየት ተችሏል።
- #አብን የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን የጥፋት ተልዕኮን ለማስፈጸም የእጅ ዙር ተልዕኮው ያነገበ ቡድን ነው! ➜➜➜➜➜➜➜➜➜➜➜➜➜➜ #አብን በራሱ የፖለቲካ ዓላማ ያለው ፓርቲ ሳይሆን እስራኤል በሚኖሩ ደርበው ብርቁ፣ ታደሰ ቸኮል፣ ካሳሁን መስፍን የተባሉ ባለሃብቶች ኢትዮጵያን የማተራመስ ዓላማ ለማስፈጸም ያቋቋሙት የግል ድርጅታቸው ነው። በቀድሞ የወያኔ ተላላኪዎች ክርስቲያን ታደለ እና በለጠ ሞላን የመሳሰሉ ሰዎች የተሰባሰቡበት አብን ተላላኪ ነው። በተለይ ብልጽግና ውስጥ ያሉ ጠንካራ የአማራ አመራሮችን በመምታት አማራን ከኦሮሞ እና ከሌሎች ብሄሮች ጋር በማላተም የአማራ ጽንፈኝነትን ለማስፈን ከብልጽግና አመራሮች ውስጥ ሰዎችን ይገዛሉ። አሳምነው ጽጌ በአብን ደላላነት ተገዝቶ የነበረ እስራኤል የሚኖሩ ባለሃብቶች ንብረት ነበር። የአማራ ህዝብ ላይ ትልቅ ጠባሳ ትቶ ያለፈውን በአሳምነው ጽጌ አቀናባሪነት በየክልሉ አመራሮች ላይ የተፈጠመው ግድያ እስራኤል የሚኖሩት ባለሃብቶች በአብን በኩል ያስፈጸሙት ነው።
- ሰበር….ሞጣ ? አሁን ያገኘሁት መረጃ ትላንት ሞጣ የአብን ደጋፊወች የድጋፍ ሰልፍ ሲያደርጉ ነበር ሙስሊሞች ድጋፍ ሰልፉ ላይ አልተገኙም በዚህ የተበሳጩ ክርሲትያኖች ለምን ድጋፍ ሰልፉ ላይ አልተገኛችሁም ብለው ሲዝቱብን ዋሉ ሌሊት መስጊዱ አጠገብ ያለውን መድረሳ አቃጥለውት አደሩ መስጊዱ ተርፏል ።
- #ከሚሴ_ከተፈጠረው_ግጭት_ጀርባ_ማን_አለ? አብን የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት ትልቁ ጠላት ነው፡፡ አብን ከአባቱ ወያኔ የወሰደውን ተልዕኮ ለማሳካት ሃገራችን እንዳትረጋጋ ለማድረግ የተለያዩ የብብጥ አጀንዳዎችን ቀርፆ በተለያዩ ቦታዎች ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ግጭት በማሰነሳት ወድ የዜጎች ህይወት እንድጠፋ፣ንብረት እንወድም በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በኦሮሞ ልዩ ዞን አስተዳደር ከሚሴ በተፈጠረው ግጭት ጀርባ አብን መኖሩን ብዙ ማስረጃ አለን፡፡ የአብን አካሄድና ዓላማም የአማራ የበላይነት አቀንቃኝና የነፍጠኛ ስርዓት ናፋቂ አሰተሳሰብ ያለው የኢትዮጵያንውያን ብሔር ብሔረሰቦች ጠላት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አንዱ ብሔር የበላይ ሌላኛው ብሔር የበታች ተደርጎ የሚቆጠርበት ኢትዮጵያ አትኖሪም፣ሊትኖሪም አትችልም፡፡ የአብን ምኞትና ፍላጎት አንድ ሃገር፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት የሚል የፀረ ኢትዮጵያውያን አመለካከት አራማጅ ቀንደኛ ጠላታችን ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሃገር አፍራሽ ፅንፈኛ ብሔርተኛ አክራሪዎችን በፅናት ታግለን ለሁላችን ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን እንገነባለን፡
- #ሰበር!! አሸባሪው አብን እና አባቱ አዴፓ ቻግኒ ላይ ያለውን ለተፈናቃዬች የተዘገጀ እህል መጋዘን በእሳት እያወደመ ነው
በመቀጠል የአሉታዊ መረጃዎች ኢላማ የነበረው የተፎካካሪ ፓርቲ ደግሞ ኢዜማ ሲሆን ኢዜማን የተመለከቱ አሉታዊ መረጃዎችን ስናይ በዋነኝነት በኢዜማ ፓርቲ እና በመንግስት መካከል ከመጋረጃ ጀርባ ስምምነት እንዳለ አድርገው የሚያቀርቡ ሀሰተኛ መረጃዎች ቀዳሚ ሲሆኑ በመቀጠል የኢዜማ ፓርቲ የኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲ የአማራ ክልል እንዲፈርስ እና የብሄሩ ተወላጆች እንዲጠፉ በተናጠል እንዲሁም ከሌሎች ጋር በትብብር እየሰራ ነው የሚሉ አሉታዊ መረጃዎች በከፍተኛ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲሰራጩ ተስተውሏል።
- አብዛኞቻችሁ ኢዜማ ተሸነፈ ብላችሁ ጮቤ እየረገጣችሁ ነው; ሞኝ ናችሁ ልበል? ሲጀመር ኢዜማ የተመሰረተው በአብይ እና ብርሃኑ ነጋ ኤርትራ ሄደው ባደረጉት ምክክር ነው ሲቀጥል ብሬ ይሄን ምርጫ ተወዳድሮ ለመሸነፍ 160 ሚልዮን ብር ተቀብሏል:: ኢዜማ እና ብልፅግና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው:: ኢዜማ ምርጫውን የተወዳደረው ለማሸነፍ ሳይሆን ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመሸነፍ እና የምርጫውን ተዓማኝነት ለመጨመር ነው:: በእነ ብርሃኑ ነጋ እና ግርማ ሰይፉ ፓርላማ አለመግባት አትደሰቱ ምክንያቱም ቤተ መንግስት ውስጥ ቋሚ ስፍራ አላቸው እና:: ከሰሞኑ ብርሃኑ በሚድያ ወቶ “እንኳን ደስ አለህ ወንድሜ ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ምርጫውም ከዚህ ቀደሞቹ በጣም የተሻለ ነበር” ማለቱ አይቀርም:: ስለዚህ ወዳጆቼ ምንም ጮቤ የሚያስረግጥ ነገር የለም:: ለኢዜማ ከማዘን ለራሳችን እንዘን በየ ቀኑ ለሚያልቀው ለወገናችን እንዘን መፍትሄው ላይም እናተኩር!!
- ኢዜማ በመንግስት መኪና (ያውም በፖሊስ) የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርግ ከማየት በላይ ምን ያስደምማል። ብርሀኑ ነጋ “የኦሮሞ ትግል መነቃቃት ኢትዮጵያን ያጠፋል በማለት ስጋት ስለ ገባኝ ነው ዳግም ወደ ትግሉ የተመለስኩት” ነበር ያለው። አው አብይ አህመድ እና ብርሀኑ ነጋ መካከል አንዳች ልዩነት የለም ሁለቱም የጋራ ጠላት አድርገውን እየሰሩ ያሉት።
- ኢዜማዎች ባልደራስ አማራ ስለሆነ አትምረጡት በማለት ለአማራ ያላቸውን የቆየ ጥላቻ ገሃድ እያወጡት ነው:: ኢዜማ በአማራ ክልል አንድ ድምፅ ካገኘ ይገርመኛል:: የአማራ ህዝብ ኢዜማን መምረጥ ማለት ኦህዴድን መምረጥ መሆኑን ይዘነጋዋል ብዬ አላስብም::
የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎችን በአንድነት ኢላማ ካደረጉት አሉታዊ መረጃዎች ውስጥ በአብዛኛው የተለያዩ የመንግስት አካላት እና ተቋማት በእነዚህ ፓርቲዎች ላይ በተለይም የአብን፣ ኢዜማ፣ ባልደራስ እና ኦፌኮ ፓርቲ አባላትን እና አመራሮችን እያንገላቱ፣ እያሰሩ እና እየገደሉ ነው የሚል ይዘት ያላቸው ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የተለያዩ የክልል አስተዳደሮች ለተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሞራል ፣ የመሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚያተቱ መረጃዎችም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሲሰራጩ በዚህ ዳሰሳ ላይ ለማየት ተችሏል። በተጨማሪም የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ማስረጃ የለሽ ክስን የሚያቀርቡ አሉታዊ መረጃዎችም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በስፋት ሲሰራጩ ለማየት ተችሏል። በተለይም የባልደራስ፣ ኢዜማ እና አብን የፓለቲካ ፓርቲዎች የአንድ ብሄር እና ሀይማኖት የበላይነት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ናቸው የሚል ይዘት ያላቸው ሀሰተኛ መረጃዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው።
- 3ቱ ፀረ ሙስሊም የፖለቲካ ድርጂቶች ~~~ “የሙስሊም ባንክ መከፈት የለበትም” ብረሀኑ ነጋ/ኢዜማ “ኢትዮጲያ ውስጥ የሚኖሩ ሙስሉሞች” እስክንድር ነጋ/ባልደራስ “ኢትዮጲያ የክርስትያን አማራ ደሴት ናት” አብን ሙስሊሞች ከነዝህ ፀረ እስልምና ድርጂቶች መራቅ አለባችሁ።
- #የኦሮሚያ ብልጽግና ጉድ… በሽመልስ አብዲሳ እና አዲሱ አረጋ የሚመራው የድሮው ኦህዴድ የአሁኑ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ለከፍተኛ አመራሩ ባሰራጨው ‘ስትራቴጂክ ሰነድ’ ላይ እንዲህ ብሏል!! “ኦነግ ፣ ኦፌኮ ፣ አብን እና ባልደራስ ከግብጽ ጋር የሚሰሩ ሀገር አፍራሾች ናቸው ብለን በህዝብ እንዲጠሉ ማድረግ አለብን” ብሏል!! ባለፈው ጊዜ ኦሮሚያ ላይ በነበረው ሰልፍ “በኦነግ ሻኔ እና አብን ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚል የድንቁርና ሰልፍ ያካሄዱት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በሰጠው አቅጣጫ መሆኑን ልብ ይላሉ!! እንግዲህ እኒህ ናቸው ሀገር ይመራሉ ተብለው አራት ኪሎ የተዘፈዘፉት ፣ የሀገር ሸክሞች!!!
- ከዛሬው የኬሎ ሚዲያ ቪዲዮ የተመለከትኩት ዋናው ቁልፍ ንግግር “ምርጫውን ተገን አድርገው ብጥብጥ ሊያስነሱ የሚሞክሩ ሀይሎችን የማጨፈጭፍ ግብረ ሀይል ቀድመን አዘጋጅተናል”የሚለው ነው። ማናቸው እነዚህ አካላት ? በኦሮሚያ ክልል ምርጫ የለም ተወዳዳሪዎች በጊዜ ከሜዳው ተወግደዋል ። ስለዚህ እነዚህ ብጥብጥ ሊቀሰቅሱ የሚያስቡ ሀይላት በፊንፊኔ፦ ባልደራስ ኢዜማና አብን በአማራ ክልል፦ አብን በደቡብ በተይም በጉራጌ እና ጋሞ ዞኖች ፦ ኢዜማ ናቸው ። ስለዚህ አብይ አስቀድሞ ሊያፍናቸው የተዘጋጀላቸው ፓርቲዎች ኢዜማ አብንና ባልደራስ ናቸው ማለት ነው። ዞሮ ዞሮ አብይ አህመድ የደነፋው በከላይ በተጠቀሱት የነፍጠኛ ፓርቲዎች ላይ ስለሆነ የእኛ የኦሮሞች ድርሻ ትግላችንን አጠናክረን እየቀጠለን የነፍጠኞችን የክሽክሽ ፊልም መመልከት ይሆናል ። የእኛ የትግል መስመር already ቀድሞ ስለታወቀ ስለ ቀጣዩ የውሸት ምርጫና ድራማ አይመለከተንም️ ይህንን ቪዲዮ ከተመለከቱ በኋላ እነዚህ ፓርቲዎች ብልፅግናን ማጀባቸውን ይቀጥላሉ ወይስ boycott ያደርጋሉ?
ማጠቃለያ
በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ምህዳር ውስጥ የተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በዚህ ትንተና ላይ ለመዳሰሰ የተሞከረ ሲሆን በዚህ ዳሰሳ ላይ የተለያዩ አዝማሚያዎችን ለመታዘብ ተችሏል። በቀዳሚነት የታዘብነው በፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የበለጠ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከፍተኛ የአሉታዊ መረጃዎች ኢላማ ሆኖ እንደሚቀርብ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የብሄር ፓለቲካን የሚያራምዱ ድርጅቶች ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ከፍተኛ የአሉታዊ መረጃዎች አላማ ናቸው። ሁለተኛ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሀገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት እና ህጋዊ ፍቃድ ካላቸው ፓርቲዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ትኩረት እንደሚያገኙ እና በማህበራዊ ሚዲያው ላይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ለመታዘብ ተችሏል። ሶስተኛ ትኩረት ያገኙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትኩረት ያገኙበት ምክንያት በፓለቲካ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳቸው ሳይሆን አሉታዊ በሆኑና ሴራ ተኮር እንዲሁም በብዛት እርስ በእርስ በሚቃረኑ የመረጃ ስርጭቶች ላይ ነው። አራተኛ አብዛኛው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የተመለከቱ የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሆኑ በተጨማሪም የፓለቲካ ስልጣን የያዘ አካል ዙሪያ ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎች በብዛት ሲሰራጩ ይስተዋላል። በመጨረሻም የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በብዛት ጊዜና ሁኔታዎችን እየተከተሉ የሚለዋወጡ ሳይሆኑ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ አንድ አጀንዳ ላይ ብቻ የማተኮር አዝማሚያ ያላቸው ናቸው።
ምንጭ – Factify Ethiopia