የአዲስ አበባ ፖሊስ በጥናት ላይ ተመስርቶ ባደረገው ኦፕሬሽን በተለያዩ ጊዜያት የተሰረቁ 22 ተሽከርካሪዎችን እና 33 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ በጥናት ላይ በመመስረት የምርመራ እና የክትትል ቡድን አቋቁሞ ባካሄደው ኦፕሬሽን በተለያዩ ጊዜያት የተሰረቁ 22 ተሽከርካሪዎችን ማስመለሱን በወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ ገልፀዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ እየተሰረቁ አብዛኞቹ ወደ ሃዋሳ ከተማ እንደሚወሰዱ በምርመራ ማረጋገጥ እንደተቻለ የጠቀሱት ኮማንደር አለማየሁ ከተሰረቁት ተሽከርካሪዎች መካከል ሰባቱ በአዲስ አበባ የተገኙ ሲሆን የተቀሩት 15 ተሽከርካሪዎች ደግሞ በሀዋሳ ከተማ እና ከሀዋሳ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ተይዘው ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ተሽከርካሪ በመስረቅ ፣ የተሰረቀውን ተሽከርካሪ በመግዛት እና በመደለል ተሳትፎ ያደረጉ ከአዲስ አበባ 19 ከሃዋሳ ደግሞ 14 በአጠቃላይ 33 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራው በስፋት መቀጠሉን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ተሽከርካሪዎቹን ለጥበቃ ምቹ በሆነ ቦታ ባለማቆም በሚፈጠር ክፍተት እና ቁልፍ ተሽከርካሪ ላይ ጥለው ሲወርዱ እና የተሽከርካሪውን ቁልፍ በልዩ ልዩ አጋጣሚ በማስቀረፅ ወንጀል ፈፃሚዎቹ የስርቆት ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር በምርመራ መረጋገጡን ከኮማንደር አለማየሁ ገለፃ መረዳት ተችሏል፡፡