“የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር” በሚል ራሱን የሚጠራውና ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ ጋር ግንባር የፈጠረው ሸኔ ተፈረካክሶ እየታደነ መሆኑንን የመከላከያ ከፍተኛ መኮንን አስታወቁ። የሸኔ የውጭ አገር ቃል አቀባይም ሆኑ ጃል መሮ በቀጥታ በትህነግም ሆነ የትህነግ ደጋፊ ሚዲያዎች ማስተባበያም አልሰጡም።
የአገሪቱ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ” በኦሮሚያ ክልል ሸኔን ለመደምሰስ የሚያስችሉ የሸዋ፣ የወለጋ፣ የጉጂ ኮማንድ ፖስቶች የተደራጁ ሲሆን፤ መከላከያ፣ የክልሉ አመራርና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በጋራ የተቀናጀ ሥምሪት እያካሄዱ ይገኛሉ። በዚህም 3180 የሸኔ ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን እጃቸውን ላለመስጠት አሻፈረኝ ያሉት ተደምስሰዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአባ ቶርቤ፣ የአልሸባብና የጁንታው ሴሎችና ተባባሪዎች ተይዘዋል” ሲል ዝርዝር መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎ ማጽዳቱ መቀጠሉን ያስታወቁት የምዕራብ ወለጋ ዞን ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ከበደ ገላው ከሕዝብ ጋር በቅንጅት የተከናወነ ባለ ዘመቻ የሸኔ ሃይል ተፈረካክሶ ተበትኗል። የመከላከያ ሰራዊትም እግር በግር እየተከተለ እያጸዳ ሲሆን የተዘረፉ የቀንድ ከብቶችና ንብረት በየጫካው በመጣል እየሸሸ መሆኑ ተመክቷል። በአሸባሪው ቡድን የተዘረፉት የቀንድ ከብቶችና ንብረት ለህብረተሰቡ ንብረቶች እየተመለሰ መሆኑም ተገልጿል።
በዞኑ በግምቢ ወረዳ ሶጌ ከተባለው አካባቢ፣ በቦጂ ጨቆርሳና ግምቢ አካባቢዎች ተዘርፈው የነበሩ 105 የቀንድ ከብቶችና 10 በጎች እንዲሁም ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ በቆሎ ለየባለቤቶቹ እንዲመለስ መደረጉን እንደማሳያ ተጠቁሟል። ይህ ቡድኑ አርዶ ከበላውና ከሸጠው የድሃ ንብረት የተረፈ መሆኑ ታውቋል።
በተጨማሪም 10 ሞተር ብስክለት፣ 200 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ 108 የዲሽቃ ጥይቶች፣ ድምጽ አልባ የጦር መሳሪያዎችና አንድ ጀኔሬተር ከመንግስት መስሪያ ቤቶች የተዘረፈ መያዙም ተገልጿል። መከላከያ አካባቢውን እያጸዳ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት የዞኑ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅቱ ያለምንም ስጋት በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የየዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ነዋሪዎች አስታውቀዋል። አያይዘውም መከላከያ ሠራዊት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚያበረታታ መሆኑንም የዞኑ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ በተወሰደው ጠንካራ እርምጃ፥ በርካታ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ሲደመሰሱ አመራሮቻቸውን ጨምሮ አምስት ታጣቂዎች መማረካቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ለጥፋት ይጠቀምባቸው የነበሩ 5 ሙሉ ትጥቅ፣ 310 የክላሽ ጥይት፣ 2 የጭስ ቦንብ፣ 15 የጥይት መጋዘን እና የተለያዩ ወታደራዊ ንብረቶች መማረካቸው ተገልጿል። የአሰሳ ዘመቻው ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡
በለሌላ ተመሳሳይ ዜና በምስራቅ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን በቀጠናው የሚገኘው የክፍለ ጦር ዋና አዛዥ አመልክተዋል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና፣ ኪረሙ፣ በኢበንቱ፣ በሀሮሊው እና በሊሙ ወረዳዎች ዙሪያና አካባቢው በአሸባሪው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ እየተወሰደበት እንዳለ ተገልጿል።
በግዳጅ ቀጠናው የሚገኘው የክፍለ ጦር ዋና አዛዥ እንዳሉት÷ በአሸባሪው የህወሃት ሳንባ በሚተነፍሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ላይ በተወሠደው የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ 49 የሸኔ ታጣቂ ቡድን አባላት ሲማረኩ፣ አምስቱ እርምጃ ተውስዶባቸዋል 50 የሚሆኑት ጀሌዎች ደግሞ ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲያቀብሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በዚህ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ አሸባሪው ሸኔ ከሕዝብና ከመንግሥት ተቋማት ዘርፎ ሲጠቀምባቸው የነበሩ 18 ሞተር ሳይክሎች፣ 44 ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ 26 ልዩ ልዩ መሳሪያዎች፣ 25 በርሜል ነዳጅን ጨምሮ 74 ሺህ 795 ብር መያዙን ተናግረዋል።
ዋና አዛዡ አክለውም÷ ክፍለ ጦሩ በስፍራው ከመድረሱ በፊት የአሸባሪው ሸኔ ቡድን በአካባቢው ማህበረሠብ ላይ ከፍተኛ የሆነ ስቃይና እንግልት ያደርስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ሠራዊቱ ይህን የጥፋት ቡድን የመደምሰስ ግዳጅ ተቀብሎ ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ግዳጅ መፈፀም ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በአምስት ወረዳዎች ጠላትን በመደምሠስ የአካባቢውን ሠላም መመለስ መቻሉ ተገልጿል።
የአሸባሪው የወያኔ ተላላኪ ክንፍ የሆነውን የሸኔ ቡድንን ለመደምሰስ በተደረገው የተጠናከረ ዘመቻ በምስራቅ ወለጋ ዞን በጋቲራ ቀበሌ ከህዝቡ ተዘርፈው የተወሰዱትን 40 የቀንድ ከብቶች ለባለቤቶቻቸው መመለሳቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነውን መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
የአገሪቱ ብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በዝርዝር ቁጥርና ቦታ ጠቅሶ ላቀረበው ሪፖርትም ሆነ አሁን ላይ የሸኔ ሃይል መፈረካከሱን አስመልክቶ ቡድኑ ያለው ነገር የለም። ለወትሮ ቪኦኤን፣ ቢቢሲን፣ የትግራይ ሚዲያ ሃውስ፣ ርዕዮትና መስለ ሚዲያዎችን በመጠቀም፣ ማስተባበያና የራሱን ድል የሚገልጸው ሸኔ በዚህ ደረጃ እየከሰመ መሆኑ ሲገለጽ ምንም ምላሽ አልሰጠም። ከትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር በገሃድ ግንባር ፈጥሮ እንደሚሰራ ካስታወቀ በሁዋላ ሰፊዎ ኦሮሞ ጀርባውን እንደሰጠው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ተሰሚነት ያላቸው የኦሮሞ አንጋፋ ፖለቲከኞች ” ሸኔ ብረት ይዞ ጫካ በመግባት ንጹሃንን የሚገልበት ምድራዊ ምክንያት የለውም፣ ከትህነግ ጋር አብሮ ለመስራት መወሰኑ የፖለቲካ ሞት ይሆንበታል” ብለው ነበር። እነዚህ ክፍሎች ቀደም ባለው ጊዜ ከአርባ ሺህ በላይ ኦሮሞ እስር ቤት በታጎረበትና ሊተኩ የማይችሉ የኦሮሞ ልጆች ደብዛቸው እንዲጠፋ ካደረግ ድርጅት ጋር አብሮ ምስራት ኦሮሞ ላይ ክህደት እንደመፈጸም እንደሚቆጠርም ገልጸው ነበር።