በዓመት 10ሺ ትራክተሮችን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት በሞጆ ከተማ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።
በየክልሉ የሰርቪስ ማዕከላት ለመገንባትና በቀጣይ መገጣጠሚያ ለማድረግም ታቅዷል፡፡
በሞጆ ከተማ ሊገነባ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የትራክተር ፋብሪካ በዓመት 10ሺ ትራክተሮችን ያመርታል። ፋብሪካውን የሚገነባው በቻይና ቁጥር አንድ የትራክተር አምራች YTO-CAMACO ሲሆን በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ግንባታውን አጠናቆ ስራ ይጀምራል ተብሏል።
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚው አምባሳደር ምስጋና አረጋ የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ ዘመኑ የደረሰበት የግብርና ማምረቻ ፋብሪካ መገንባት አስፈልጓል ብለዋል።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የYTO ማዕከል የሚሆነው ፋብሪካው በቀን 50 ትራክተሮችንና በዓመት ከ10ሺ በላይ ትራክተሮችን የሚያመርት በመሆኑ ለሀገራችን ግብርና የጀርባ አጥንት መሆኑንም አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል።
የYTO ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ሚስተር ሊዩ ፒ በበኩላቸው ኩባንያው የቻይናን ግብርና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዘመናዊ የቀየረ በመሆኑ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር ለመስራት እዚህ ተገኝተናል ብለዋል።
ፋብሪካው ለብዙዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ሊዩ ፒ በአጭር ጊዜ ገንብተን እናስረክባለን ብለዋል።
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አብረሃም በላይ ባደረጉት ንግግር የለውጡ መንግስት የመጀመሪያ ትኩረት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን በአዲስ አስተሳሰብ እንዲመራ ማድረግ እንደሆነ አስታውሰዋል። ከግዥና ችርቻሮ ወጥቶ በአምራችነት እንዲሠማራ ማድረግ በመሆኑ የዛሬው ፕሮጀክትም የዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የፌደራል ተቋማት አመራሮች፣የግሩፑ የቦርድ አመራሮችና የማኔጅመንት አባላት የሞጆ ከተማ አመራሮች መገኘታቸውን ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።(ኢ ፕ ድ)