60ኛ ልጁን “ኩሻል” ወይንም “ደስታው” የሚል ስም የሰጠው ክሂልጂ፥ የልጆቹ ቁጥር ስድስት አስርትን እንዲሻገር ይፈልጋል።
ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ተጨማሪ ሚስት እና ልጆችን እንደሚፈልግ ነው የተናገረው።
“ጓደኞቼ አራተኛ ሚስት በመፈለግ እንዲያግዙኝ ነግሬያቸዋለሁ” የሚለው ጎልማሳው “ዶክተር”፥ በቀጣይ ከሚያገባትም ሆነ ከሶስቱ ሚስቶቹ ተጨማሪ ልጆችን በመውለድ የቤተሰቡን ቁጥር ማሳደግ እንደሚፈልግ ከተናገረ በኋላም በማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
ክሂልጂ በፈረንጆቹ 2016 35ኛ ልጁን ሲያገኝ ነበር የአለም መገናኛ ብዙሃን ቀልብን የሳበው።
ከዚያ በኋላም ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፥ 100 ልጆች እንዲኖሩት እንደሚፈልግ ማሳወቁን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
አነስተኛ ክሊኒክ ከፍቶ እንደ ራስ ምታት ያሉ ህመሞችን የሚያክመው “ዶክተር”፥ በ50ዎቹ መጀመሪያ መገኘቱ ምኞቱን የማሳካት እድሉን ሰፊ ሳያደርጉለት አልቀረም።
ጥያቄው ግዙፉን ቤተሰብ የማስተዳደር አቅሙ ምን ያህል ነው የሚለው ነው።
“ባለፉት ሶስት አመታት የዱቄትም ሆነ የስኳር ዋጋ በሶስት እጥፍ አድጓል” የሚለው ክሂልጂ፥ ልጆች እና ሚስቶቹን ለማስተዳደር እንደተፈተነ አልሸሸገም፤ የኑሮ ውድነቱ ግን ተጨማሪ ሚስት እና ልጆችን ከመመኘት አላገደውም።
ፓኪስታናዊው የልምድ ሃኪም የሰሞኑ መነጋገሪያ ይሁን እንጂ በልጆች ብዛት አሁን ላይ ስማቸው በጉልህ የሚነሳው ኡጋንዳዊው አርሶ አደር ሙሳ ሃሳይሃ ናቸው።
የ68 አመቱ ሃሳይሃ ከ12 ሚስቶች 102 ልጆችን የወለዱ ሲሆን፥ የኑሮ ውድነቱ ባይከብደኝ ተጨማሪ ልጆችን መውለድ እፈልግ ነበር ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል።
via Al ain