የመጀመሪያው ፈተና ታሪክ ካሸከመን ዕዳዎች የሚመነጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አያሌ አኩሪ ታሪኮችና በታሪክ ውስጥ ያገኘናቸው ዕድሎች አሉን፡፡ በእነዚህ እንኮራለን፤ ለኢትዮጵያ ብልጽግናም እንደ አንጡራ ሀብት እንጠቀምባቸዋለን።
በተቃራኒው ደግሞ በታሪካችን ውስጥ ያልፈታናቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገን የጨመርናቸውና ያልተግባባንባቸው ዕዳዎችም አሉን፡፡ እነዚህ ዕዳዎቻችን የእኛ ብቻ አይደሉም፡፡ በዓለም ላይ ሀገር የመሠረቱ ሕዝቦች ሁሉ የሚገጥሟቸው ናቸው፡፡
- Growing relations between Israel and Ethiopia: between military deals, intelligence influence, and an eye on Egypt
- የመጨረሻው መጀመሪያ የማሪያም መንገድ – ራስ ዱሜራ
- “ ንስሃ ገብቻለሁ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል ፤ ሲያፈገፍጉ የተረሸኑ ታጋዮች አሉ ” አቶ ጌታቸው ረዳ
እነዚህ ዕዳዎች የመነታረኪያ፣ የመጋጫና የመከፋፈያ ምክንያቶች ሊሆኑብን አይገባም፡፡ ዕዳዎቹን ወረስናቸው እንጂ አልፈጠርናቸውም፡፡ መጡብን እንጂ አልሄድንባቸውም፡፡ የተሻለው የመጀመሪያ መፍትሔ ለዕድሉም ለዕዳውም ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዕድሉን ለመጠቀም፣ ዕዳውን ደግሞ ለማራገፍ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሠለጠነና የሰከነ አካኼድ አዋጪ መሆኑን የዓለም ታሪክ አሳይቶናል፡፡
ያለፉ ዕዳዎቻቸውን በጠብ፣ በግጭትና በመከፋፈል ለመፍታት የሄዱ ሀገሮች ተጨማሪ ዕዳ አመጡ እንጂ መፍትሔ አላገኙም፡፡ ያለፉ ዕዳዎቻቸውን በሠለጠነና በሰከነ መንገድ በምክክርና በውይይት፣ በይቅርታና በዕርቅ ለመፍታት የሞከሩ ሀገሮች ግን ወደተሻለ መግባባትና ወደላቀ አንድነት ለመምጣት ችለዋል፡፡ እኛም የሚያዋጣን ይሄ ነው፡፡ የጀመርነው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ እናድርግ፡፡ ለስኬቱም ከሁላችን የሚጠበቀውን ድርሻ እንወጣ፡፡ ዕዳዎቻችንን በምክክር፣ በይቅርታና በዕርቅ እናርማቸው፡፡ ያለፉ ነገሮቻችን ትምህርት እንጂ እሥር ቤት እንዳይሆኑን አድርገን እንሻገራቸው፡፡
የፓርቲያችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ሕዝባችን ያለፉ ታሪካዊ ዕዳዎቻችንን እንደ ግጭት መሣሪያ ለመጠቀም የሚሹ ኃይሎችን በመታገል፣ ለሀገራዊ ምክክሩ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 8 ቀን 2015 ካስተላለፈዉ መግለጫ የተወሰደ