ባለፉት ሁለት የጦርነት ዓመታት ኢትዮጵያ ላይ የሚያሴሩ፣ ራሳቸውን ሸጠው ኢትዮጵያን የሚያደሙና የቀጠራቸውን አገር ፍላጎት ለማሳካት ውል ገብተው በጋዜጠኛነት ስም ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጩ “ልጆቿን” በገሃድ አይታለች። ዓለም “ታላላቅ” በሚባሉ መሪዎችና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት፣ ሚዲያዎች፣ አገራትና ህብረት ስም ኢትዮጵያን ለማወላለቅ ተባብሮ ሲዘምት እነዚሁ ወገኖች አብረው ተሰልፈው ሲያሸረግዱና ለገቡት ውል አፈንድደው የኢትዮጵያን ውድቀት ሲያሳልጡ ስለመክረማቸው ማንም ማስተባበያ ሊያቀርብ አይችልም።
ጭልጥ ባለ ወገንተኝነት ሰዋዊና ዜግነት የሚያዘውን ሚዛናቸውን በገቡት ውል መሰረት ሰብረው የአፋርና አማራ ህዝብን ወረራ እስከመካድ የደረሱ “ዜጎች” ጉዳይ አሁን ድረስ እያሰገረመ ሳለ ነው የአንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጀግና ዜና የተሰማው። ለትግራይ ህዝብም ቢሆን ሊጠቅመው ባማይችል ጭፍን አካሄድ ኢትዮጵያ እንድትነድ እየተከፈላቸው ሲቀሰቅሱና ነብሰገዳይ ቃለ ምልልስ እያደረጉ ማስታወቂያ ሲሰሩ የነበሩትን ያህል እንዲህ ያለ ኢትዮጵያዊ መገኘቱ ” ኢትዮጵያ መካን አይደለችም” ለሚሉት ልጆቿ የተስፋቸው መጽኛ ሆኖላቸዋል።
በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ከትህነግ የትጥቅ ትግል ጀምሮ በውጭ አገራት የሬዲዮ ጣቢያዎች ሲሰሩ የነበሩ የአሁኖቹን ጨምሮ ጥብቅ ጥናት እንዲደረግና ግብራቸው ተለይቶ ለትውልድና ለታሪክ እንዲቀመጥ ” እዛው ውስጥ የነበሩና ያሉ ለህሊናቸው የቀረቡ” አሰራሩን ይፋ ሊያወጡት እንደሚገባ በተደጋጋሚ አስተያየት ሲሰጥ እንደነበር ያሚታወስ ነው። ” ሚዲያና ባንዳነት” እጅግ የተቆራኙ የኢትዮጵያ ችግር ሆነው ሳለ ” በስመ ጋዜጠኛ ስም እንኳን ደህና መጡ በሚል ካባ መደረብና ዕድሜ ብቻ እየቆጠሩ ለደት ማክበር ሙያውን በወጉ ተጠቅመውበት ያለፉትን ዳግም ከመቃብር ቀስቀሶ የመቅበር ያህል ነው” እስከማለት የደረሰ ጥብቅ አስተያየት የተሰጠበት ይህ ጉዳይ እስከመቼ በእከክልኝ ልከክልህ ተሸፍኖ እንደሚዘልቅ የብዙዎች ጥያቄ ነው። ጉዳዩ ገሃድ የሚታወቅ ቢሆንም የሚደፈር ጉዳይ አለመሆኑ ደግሞ ሌላው ግርምት ነው። ይህ ሲባል ግን በሚችሉት ሁሉ ስልታዊ በሆነ መንገድ ሚዛናቸውን የጠበቁና ለመጠበቅ የሚሞክሩ የሉም ማለት አይደለም።
በሌላ አውዱ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ እና ለአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ የሚሰራ የአሜሪካ ዜጋ የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አብርሃም ተክሉ ለማ ጥብቅ ምስጢራዊ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፎ በመስጠት ክስ እንደተመሰረተበት ሲሰማ ” ማን ነው ይህ ጀግና” በሚል ከላይ የተገለጹትን ጥቂት ሚዛን አልባዎች ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል። የአሜሪካንን ጥብቅ መረጃ በተየም ከህልውናው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሳተላይት መረጃ ሳይቀር ለመንግስት ሲሰጥ የነበረው ኢትዮጵያዊ እንዴት ሊፈታ እንደሚችልም መወያየት የጀመሩ አሉ።
ከሰማኒያ አምስት በላይ ጥብቅ መረጃዎችን እንደወሰደ ተጠቅሶ ክስ የተመሰረተበት አብረሃም ይህን ሲያደርግ በነበረበት ወቅት ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያ መመላለሱ ተመልክቷል። በይፋ መረጃውን ለኢትዮጵያ መንግስት ሰጠ የሚል ጉዳይ ባይነሳም ጥርጣሬው ብዙ ነው። በሁለት ዓመት ውስጥ ማለትም ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚደገፈውን ትህነግን አከርካሬውን ለመስበር እየተዋደቀችበት ባለበት ወቅት ነው ይህ ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባ ሁለቴ የመጣው።
አሜሪካ በስም ጠቅሳ ኢትዮጵያ መረጃውን ስትቀበል እንደነበር ባትገልጽም፣ ዜናውን ያሰራጩ የአሜሪካ የዜና አውታሮች ተጠርጣሪው ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ መረጃ ሲሰጥና ሲያቀብል የነበረው ለኢትዮጵያ እንደሆነ አስታውቀዋል። ከኢትዮጵያ ባለሥልጣን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበረውም ገልጸዋል። ቢቢሲ በስፋት የዘገበውን ከስር ያንብቡ
ምንም እንኳን የአሜሪካ መንግሥት ባይፋ ባይገልጸውም ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዜጋዋ አብረሃም ተክሉ ለማ የመከላከያ እና የደኅንነት ምስጢራዊ መረጃዎችን ወደ ኢትዮጵያ ያስተላልፍ ነበር መባሉ መነጋገሪያ ሆኗል።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መንግሥትን የስደነገጡ ምስጢራዊ መረጃዎች ሾልከው ሲወጡ የነበሩት ወደ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ወደ ተቀናቃኞቿ ኃያላን አገራት መሆኑ የአሁኑን ክስተት የተለየ አድርጎታል።
በተለያዩ ጊዜያት ከአሜሪካ የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የቴክኖሎጂ ምስጢራዊ መረጃዎች መሹለካቸው ወይም ለማሹለክ የተደረጉ ሙከራዎች መኖራቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ከዚህ አንጻርም የአሜሪካ ተቀናቃኞች ሩሲያ እና ቻይና በዋናነት በተደጋጋሚ ስማቸው የሚነሳ ሲሆን፣ የአውሮፓ ወዳጆቿም በዚህ ድርጊት ውስጥ እጃቸው እንዳለበት ሲጠቀስ ነበር።
ለዚህም ነው ከአብረሃም ተክሉ በቁጥጥር ስር መዋል ጋር ተያይዞ የአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ምስጢራዊ መረጃዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲተላለፉ ነበር ማለታቸው አነጋጋሪ የሆነው።
የአሜሪካ መንግሥት በተጠርጣሪው ላይ ባቀረበው ባለ 16 ገጽ ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመለከተው፣ አብረሃም ከታኅሣሥ 2014 እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የደኅንነት መረጃዎችን ኮፒ በማድረግ፣ የሰነዶቹን ምስጢራዊነትን የሚያመለክቱ መለያዎችን ሠርዟል ተብሏል።
የክስ መዝገቡ ተከሳሹ ሰነዶቹን ለየትኛው አገር እንዳስተላለፈ ያላመለከተ ሲሆን፣ ነገር ግን አንድ አገር እና አንድ አካባቢ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው እንዲሁም ምስጢራዊ የመከላከያ መረጃዎችን ለሌላ አገር የደኅንነት ተቋም ባለሥልጣን አሳልፎ መስጠቱ ተገልጿል።
በአብረሃም ተክሉ ላይ የቀረቡበት የተለያዩ ክሶች ከተደረጋገጡ በሞት ወይም ከ10 ዓመት አስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊያስቀጡ የሚችሉ መሆናቸው ተነግሯል።
ስለ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አብረሃም የምናውቀው
አብረሃም ተክሉ ለማ ትውልዱ ኢትዮጵያ ሲሆን የአሜሪካ ዜጋ ነው። የ50 ዓመቱ ጎልማሳ አብረሃም ነዋሪነቱ ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሜሪላንድ ሲሆን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ነው።
አብረሃም ከአውሮፓውያኑ 2013 አስከ 2016 ድረስ እዚያው አሜሪካ ውስጥ ባልቲሞር በተባለው ዩኒቨርስቲ ውስጥ የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርትን ተከታትሏል።
ይህ ሙያው ነው እንግዲህ በተለያዩ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምስጢራዊ መረጃዎችን እንዲያገኝ እና እንዲመለከት ቅርበትን የፈጠረለት።
ለአብረሃም እነዚህ አጋጣሚዎች የተፈጠሩለት በመጀመሪያ ከአምስት ዓመት በፊት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የመረጃ እና የጥናት ክፍል ውስጥ በቴክኒሻንነት ተመድቦ ሲሠራ ነው። ከዚያም ተከትሎ በዚያው መሥሪያ ቤት ስር የዋሽንግተን ቢሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተዳደር ሠራተኛ ሆነ።
በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ደግሞ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከምስጢራዊ መረጃዎች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችለውን ፈቃድ አገኘ።
በግንቦት 2014 ዓ.ም. ደግሞ ወደ አሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ተዘዋውሮ መሥራት ጀመረ። በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ወደ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተመልሶ ለፍትሕ መሥሪያ ቤቱም መሥራቱን ቀጠለ።
በዚህ አጋጣሚም በታኅሣሥ 10/2015 እና በነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ቢያንስ 85 የደኅንነት መረጃዎችን በተለያየ መልኩ በመገልበጥ ወስዷል ተብሎ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
አብረሃም የተጠረጠረባቸውን ድርጊቶች ፈጽሟል በተባለባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ ትውልድ አገሩ ኢትዮጵያ ተጉዞ እንደነበርም ተገልጿል።
እዚያም በክሱ ላይ የተጠቀሱ ጉዳዮችን መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የግለሰቡ የመረጃ ልውውጥ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን እንደማይቀር አመልክቷል።
አብረሃም ተክሉ በየካቲት 02/2014 ዓ.ም. እንዲሁም ባለፈው ዓመት ከፋሲካ በዓል በፊት ሚያዚያ 04/2015 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ እንደነበር ተነግሯል።
ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም. በኤፍቢአይ ወኪሎች በቁጥጥር ስር የዋለው አብረሃም፣ የብሔራዊ መከላከያ መረጃን ሌላ አገርን ለመደገፍ ለማስተላለፍ በማሴር እንዲሁም ሆን ብሎ የመከላከያ መረጃን በግል መያዝ የሚሉ ክሶች ተመስርተውበታል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ግለሰቡ ላይ በይፋ ክስ የተመሠረተበት ሲሆን፣ ፈጸማቸው የተባሉ የስለላ ድርጊቶች በዝርዝር ቀርበዋል። ግለሰቡ ምስጢራዊ መረጃዎችን አሳልፎ መስጠቱ እንዲሁም ከውጭ አገር ባለሥልጣን ጋር መረጃ መለዋወጡ እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ገንዘብ ማግኘቱም ተገልጿል።
ነገር ግን ቀደም ብሎም ሆነ አሁን ክሱ ይፋ ሲደረግ አብረሃም ተክሉ ለማ ከአሜሪካ መንግሥት የመረጃ ቋት በሥራው አጋጣሚ ያገኛቸውን ምስጢራዊ መረጃዎችን ለየትኛው አገር አሳልፎ እንደሰጠ ይፋ አልሆነም።
ነገር ግን የአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ተጠርጣሪው መረጃዎችን ሲያስተላልፍ እና ግንኙነት ሲያደርግ የነበረው ወደ ኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ባለሥልጣን ጋር እንደሆነ አመልክተዋል።
በክስ ሰነዱ ላይም አብረሃም ተክሉ ለማ ወደ ትውልድ አገሩ በተደጋጋሚ መጓዙን እና እዚያም ከባለሥልጣን ጋር መገናኘቱ ተገልጿል።
ይህም ቢሆን አስካሁን ስለተጠርጣሪው እና ግንኙነት ያደርጋል ስለተባለው አገር የአሜሪካ መንግሥት ዝርዝር መረጃ ያልሰጠ ሲሆን፣ በመገናኛ ብዙኃን ስሟ የተነሳው ኢትዮጵያም በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት የሰጠችው ምላሽ የለም።

አብረሃም ስላደረጋቸው ግንኙነቶች የምናውቀው
የአሜሪካ መንግሥት ባቀረበው ዝርዝር ክስ ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ተቋማት “ምስጢር” ተብለው የተለዩ ሰነዶችን፣ ፎቶግራፎችን፣ ማስታወሻዎችን፣ ካርታዎችን፣ የሳተላይት ምስሎችን እና ሌሎች “ከሚመለከተው አገር እና ከጎረቤት አገሮች ጋር የተያያዙ” የመከላከያ መረጃዎችን በተለያዩ ቀናት አሳልፎ መስጠቱ ተገልጿል።
አብረሃም ተክሉ በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ አማካይነት መረጃውን ያጋራል ከተባለው አገር ባለሥልጣን ጋር፣ በአገሪቱ ውስጥ መንግሥትን የሚቃወሙ የአማጺያን ወታደራዊ እንቅስቃሴን በተመለከተ ውይይት ማድረጉ ተመልክቷል።
በአንድ ግንኙነት ወቅትም በተባለው አገር ውስጥ ያለ ክስተትን አስመልክቶ ባለሥልጣኑን “ቡድንህ ይህንን በመተንተን አንዳች ነገር ይውሰድ” በማለት መምከሩም ተገልጿል።
በሌላ የመልዕክት ልውውጥ ላይ ደግሞ ባለሥልጣኑ “ይህንን በመቀልበስ በኩል . . . በድጋሚ እንዳይከሰት . . . ጉልህ ለውጥ አግኝተናል. . . በጥቂት ቀናት ውስጥ ወሳኝ ደረጃ ላይ እንደርሳለን። . . . አጣርተህ ምን ማድረግ እንደምንችል ብታሳወቀኝ ጥሩ ይሆናል” እንዳለው በክሱ ላይ ሰፍሯል።
በተመሳሳይም ባለሥልጣኑን “ወደፊት የተሰማራ የዕዝ እና የአቅርቦት ማዕከልን ማወቅ ጠቃሚ ነው” በማለት ጥያቄ ያቀረበለት ሲሆን፣ ለማም በተጠቃሹ አገር ውስጥ ያሉ ቦታዎችን በተመለከተ ውይይት አድርጓል።
በሌላ ውይይት ላይ ባለሥልጣኑ የአማጺያንን የአቅርቦት ማዕከላትን በመሳሰሉ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ከለማ መረጃን እንደሚፈልግ እንደገለጸለት እና በምላሹም “አዎ፣ ይህንን ሳምንት በሙሉ በእዚያ ላይ አተኩሬ ነው የቆየሁት. . .” ማለቱ ተጠቅሷል።
ክሱ ጨምሮም አብረሃም “የወታደራዊ ሰፈር” ፎቶዎችን ለባለሥልጣኑ መላኩን፣ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር አካባቢ ደግሞ ባለሥልጣኑ “ድጋፍህን የምትቀጥልበት ጊዜ ነው” በማለት መልዕክት እንደላከለት ገልጿል።
አብረሃምም በምላሹ “ተቀብያለሁ!” ማለቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሌላ ውይይታቸውም ባለሥልጣኑ “ይህች ውብ አገር ሁሌም አኩሪ ታሪኳን ለመጠበቅ ሕይወታቸውን የሚሰዉ ልዩ ሰዎች አሏት። ውጤቱ ምንም ሆነ ምን፣ ሁሌም ትታወሳለህ” በማለት አድናቆቱን እንደገለጸለት በክስ መዝገቡ ላይ ሰፍሯል።
ሊጣልበት ስለሚችለው ቅጣት የምናውቀው
የአሜሪካ መንግሥት በተጠርጣሪው ላይ ባቀረበው ባለ 16 ገጽ ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመለከተው፣ አብረሃም ከታኅሣሥ 2014 እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የደኅንነት ሪፖርቶችን ኮፒ በማድረግ፣ የሰነዶቹን ምስጢራዊነትን የሚያመለክቱ መለያዎችን ሰርዟል ተብሏል።
የክስ መዝገቡ ተከሳሹ ሰነዶቹን ለየትኛው አገር እንዳስተላለፈ ያላመለከተ ሲሆን፣ ነገር ግን አንድ አገር እና አንድ አካባቢ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው እና ምስጢራዊ የመከላከያ መረጃዎችን ለሌላ አገር የደኅንነት ተቋም ባለሥልጣን አሳልፎ መስጠቱ ተገልጿል።
ተጠርጣሪውን የሚመለከቱ የባንክ ሰነዶችን የሰበሰቡት መርማሪዎች እንደሚሉት፣ አብረሃም ምስጢራዊ ሰነዶቹን ከአሜሪካ መንግሥት የመረጃ ቋት ካወጣ እና ወደ ኢትዮጵያ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ አስገብቷል።
በአብረሃም ተክሉ ላይ የቀረቡበት የተለያዩ ክሶች ከተደረጋገጡ በሞት ወይም ከ10 ዓመት አስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊያስቀጡ የሚችሉ መሆናቸው ተነግሯል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ግለሰቡ ምስጢራዊ መረጃዎችን ወደ ሌላ አገር እያሾለከ መሆኑን የደረሰበት፣ ተለይተው የተቀመጡ ብርቱ ወይም በጥንቃቄ መያዝ ያለባቸው ሰነዶች አያያዝን በተመለከተ ለሁለት ወራት ባደረገው አጠቃላይ ምርመራ አማካይነት መሆኑን የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ማት ሚለር ገልጸዋል።
ይህ አጠቃላይ ምርመራ እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው ጃክ ቴሼራ የተባለው የ21 ዓመት የአሜሪካ አየር ኃይል አባል ምስጢራዊ የመረጃ እና የመከላከያ ሰነዶችን አሾልኮ አውጥቷል ተብሎ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ ነው።

ስለሾለኩ የአሜሪካ ምስጢራት የምናውቀው
በአሜሪካ የምስጢራዊ መረጃዎች ሾልኮ የመውጣት ታሪክ ውስጥ ዋነኛ የሚባሉት አምስቱን የሚከተሉት ናቸው።
የዩክሬን ጦርነት ምስጢሮች
ከአሜሪካ የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ምስጢራዊ መረጃዎች ሾልከው ሲወጡ ቆይተዋል። ከሳምንታት በፊትም ከአገሪቱ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታጎን ያፈተለኩ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ምስጢራዊ ሰነዶች ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሰነዶቹ በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ የኔቶ ወታደራዊ መረጃዎች ሲሆኑ፣ ይህንንም ተከትሎ ምዕራባውያን የመከላከያ ባለሥልጣናት ምስጢሮቹን አሽሉኮ ያወጣውን ወገን ለማወቅ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
ሰነዱ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚሰጡትን ወታደራዊ ድጋፍ የሚዘረዝር ሲሆን፣ በተጨማሪም አሜሪካ በሩሲያ እና በዩክሬን መሪዎች ላይ ስለላ እንደምታካሂድ። እንዲሁም አሜሪካ የሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴን በሳተላይት እንዴት እንደመትከታተል ይፋ ማድረጉ ተዘግቧል።
የኤድዋርድ ስኖውደን መረጃዎች
የደኅንነት ሠራተኛ የነበረው ኤድዋርድ ስኖውደን ይፋ ያወጣቸው ምስጢራዊ መረጃዎች በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ አስለከትሎ ነበር።
የአሜሪካ ብሔራዊ የመረጃ ተቋም ሠራተና የነበረው ስኖውደን ባሾለካቸው ሰነዶች ላይ የአሜሪካ መንግሥት በተራ ዜጎቹ ላይ ከሕግ ውጪ የሚካሂደውን ክትትል፣ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በአገራት እና በኤምባሲዎች ላይ ስለምታካሂደው ስለላ አጋልጧል።
ስኖውደን ምስጢሩን ይፋ ካደረገ በኋላ ከአሜሪካ ወደ ሆንግ ኮንግ የሸሸ ሲሆን ቀጥሎም የአሜሪካ ባላንጣ ወደሆነችው ሩሲያ ገብቷል። አሜሪካም መንግሥታዊ ንብረት የሆኑ መረጃዎችን በመዝረፍ እና በሌሎች ጥፋቶች ክስ ተመስርቶበታል።

የፔንታጎን ሰነዶች
አሜሪካንን ከባድ ፈተና ውስጥ ከትቷት የነበረውን የቬትናም ጦርነትን በተመለከተ የተደረገ ወታደራዊ ጥናት ብርቱ ምስጢር ከ50 ዓመታት በፊት ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሾልኮ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር። ይህም በአሜሪካ መንግሥት ላይ ከባድ ተቃውሞ እና ትችትን አስከትሎ ነበር።
እንዲሁም ይህ የመከላከያ ምስጢር በጋዜጣ ለሕዝብ ይፋ ከመደረጉ ቀደም ብሎ የአሜሪካ መንግሥት በፍርድ ቤት እንዲታገድ ቢያደርግም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዕግዱ ተነስቶ ታትሟል። ይህም በመንግሥት እና በአገሪቱ ጋዜጦች መካከል ከባድ ፍጥጫ እና ግጭትን ፈጥሮ ነበር።
የኢራቅ ጦርነት ሰነዶች
በጁሊያን አሳንጅ የሚመራው ዊኪሊክስ የአሜሪካ እና የአጋሮቿ ሠራዊት ኢራቅ ውስጥ ስለፈጸሟቸው ድርጊቶች የሚዘረዝሩ በምስጢር የተያዙ ወታደራዊ ሰነዶችን ይፋ አደረገ። መረጃዎቹ በኢራቅ ውስጥ ስለተፈጸሙ ግፎች እና የመብት ጥሰቶች ያጋለጡ ናቸው።
ሾልከው የወጡት ሰነዶች 400 ሺህ የሚደርሱ ወታደራዊ ሪፖርቶች ሲሆን፣ ከ60 ሺህ በላይ ሰላማዊ ኢራቃውያን በአሜሪካ በሚመሩት ጥምር ኃይሎች መገደላቸውን እና በእስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ግፎችን ጨምሮ በርካታ ምስጢራዊ መረጃዎችን ይፋ አድርገዋል።
ይህ መረጃም አሜሪካ በኢራቅ ውስጥ ባካሄደችው ጦርነት ዙሪያ የነበረው እየቀነሰ የመጣውን የሕዝብ ድጋፍ የበለጠ እንዲኣሽቆለቁል አድርጎታል። ኦባማ ጦራቸውን ለማስወጣት እንዳሰቡ ባሳወቁበት ጊዜ ከፍተኛ ድጋፍን አግኝተዋል።
የሮበርት ሃንሰን ስለላ
በአሜሪካ የአገር ውስጥ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኤፍቢአይ ለ25 ዓመታት የሠራው ሮበርት ሃንሰን ለሶቪየት ኅብረት እና ለሩሲያ የመረጃ መሥሪያ ቤቶች አሜሪካንን ሲሰልል እንደነበረ መታወቁ ሌላኛው አነጋጋሪ ክስተት ነበር።
ግለሰቡ አስኪታወቅበት ድረስ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ሠራዊት ምስጢራዊ ዕቅዶችን እና የጦር መሣሪያ ቴክኖሎጂዎችን ለሶቪየቶች እና ለሩሲያ የስለላ ተቋማት አሳልፎ ሰጥቷል።
ሃንሰን ምስጢራዊ የደኅንነት እና ወታደራዊ መረጃዎችን አሳልፎ በመስጠት 1.4 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ መጠን ያለው ሃብትን በገንዘብ እና በአልማዝ ማግኘቱ ተደርሶበታል።
- የመጨረሻው መጀመሪያ የማሪያም መንገድ – ራስ ዱሜራኢትዮጵያ ከጅቡቲ ማግኘት የነበረባትን የባህር በር ሳታገኝ እንዲሁም በተመሳሳይ ኤርትራ ስትሄድ ለመውጪያም ሆነ ለመግቢያ ይጠቅማት የነበረን የባህር በር ሳታገኝ መቅረቷ ልብ ያደማል። የፖለቲካ ሳይንስን በቅጡ የሚገነዘቡ ምሁራን… Read more: የመጨረሻው መጀመሪያ የማሪያም መንገድ – ራስ ዱሜራ
- “ ንስሃ ገብቻለሁ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል ፤ ሲያፈገፍጉ የተረሸኑ ታጋዮች አሉ ” አቶ ጌታቸው ረዳየትህነግ ቃል አቀባይ በመሆን ጦርነቱን በፕሮፓጋንዳ ሲያቀጣጥሉት የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ላይ የሆነው ሁሉ እረፍት እየነሳቸው ያሉ ይመስላል፡፡ በጦርነቱ ወቅት ሲነገሩ የነበሩ ቁልፍ ሚስጢሮችን ሲከላከሉና ሲያመክኑ… Read more: “ ንስሃ ገብቻለሁ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል ፤ ሲያፈገፍጉ የተረሸኑ ታጋዮች አሉ ” አቶ ጌታቸው ረዳ
- ለምህላቸው ከሚኖሩት መካከል – ሰርጉን ጥሎ ነብስ የታደገው ሐኪምሰሞኑን ከሚሰማው የሐኪሞች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጎን ለጎን የተሰማው ዜና ሰፊ አድናቆት እየተቸረው ነው። ዶክተር ብሩክ ወይሻ ሙሽራነቱን አቋርጦ ነብስ ታድጓል፡፡ ” ለሆስፒታሉ ብቻ ሳይሆን ለአከባቢውም ብቸኛ… Read more: ለምህላቸው ከሚኖሩት መካከል – ሰርጉን ጥሎ ነብስ የታደገው ሐኪም
- ፕሮፌሰር ክንድያ የደብረፅዮንን ቡድን “ካለፈ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ” አሉት፤ ፋኖ የደቦ አመራር ሰየመበጦርነቱ ወቅት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ፕሮፌሰር ክንድያ ገብረህይወት “የደብረፅዮን ቡድን ከተደጋጋሚ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ነው” ሲሉ አጣጣሉት። ፋኖ አስራ ሶስት አመራሮችን መርጦ ድርጅት መመሰረቱ ተገለጸ። መሪ አለመሰየሙ… Read more: ፕሮፌሰር ክንድያ የደብረፅዮንን ቡድን “ካለፈ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ” አሉት፤ ፋኖ የደቦ አመራር ሰየመ
- The Wars We Still Can StopCameron Hudson (New York TimesMay Opinion Mr. Hudson is a senior fellow in the Africa program at the Center for Strategic and International Studies in Washington. Conflict,… Read more: The Wars We Still Can Stop