በፀጋ በላቸው ላይ የጠለፋና አስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰው ኮንስታብል የኋላመብራት ወልደማርያም በ16 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

የህግ አማካሪና ጠበቃ እንዲሁም በፆታዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩት አበባየሁ ጌታ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፤ ውሳኔው የከተማውን ገፅታ የሚያበላሽ እንደሆነ ስለታሰበ ነው መፍትሄ ያገኘው ብለዋል።
– ሚዲያ ላይ ባለመውጣታቸው ብዙ ተሸፋፍነው የቀሩ የጠለፋ ወንጀሎች በከተማው አሉ።
– ይህ ውጤት የተገኘው በተለያዩ መንገዶች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ስላገኘ ነው።
– ጉዳዩ አነጋጋሪ የሆነው የከንቲባው የግል ጠባቂ ከመሆኑ፣ የመንግስትን ንብረት ተጠቅሞ በመሆኑ በከተማው ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለነበረው ነው ይህ ጉዳይ እልባት ያገኘው።
– ታህሳስ 04 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተጠርጣሪው በተከሰሰባቸው ሁለት ወንጀሎች ማለትም በጠለፋ እና አስገድዶ መድፈር ጥፋተኛ ተብሏል።
- በመቀጠል ታህሳስ 08 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ላይ ከሁለቱም ወገኖች የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ እንዲያቀርቡ ተደርጎ ነበር።
– በዛሬው እለት ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በ16 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ተሰጥቷል። ሲሉ የህግ አማካሪው ለቲክቫህ ተናግረዋል።
ባለሙያው በአጠቃላይ ፆታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ ምን አሉ ?
- ወደሐዋሳ አካባቢ መሰል ችግሮችን በሽምግልና መፍታት እና ከባህል ጋር የማያያዝ አዝማሚያ አስቸጋሪ ነው። እንደዚህ አይነት ነገሮች በሽምግልና መፈታት የለባቸውም።
- የህግ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ የማይጮኹ ጉዳዮችንም ትኩረት አለመስጠት እና ተባባሪ አለመሆንም መስተካከል ይገባዋል።
- በትምህርት፣ በስልጠና እና በመሰል አስተማሪ ቅጣቶች ለፆታዊ ጥቃቶች ትኩረት መስጠት ይገባል።
የዳሸን ባንክ ሰራተኛ እንዲሁም የአላሙራ ሙሉወንጌል ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆነችው ፀጋ በላቸው ፤ ግንቦት 15 ቀን 2015 ከስራ ስትወጣ በወቅቱ የከተማው ከንቲባ የግል ጠባቂ በነበረው ኮንስታብል የኃላመብራት ወ/ማርያም የተባለ ግለሰብ በመኪና ታግታ መወሰዷና አድራሻዋም ሳይታወቅ ለቀናት መቆየቱ የሚታወስ ነው።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በወቅቱ እንዳስታወቀው ተጠርጣሪው ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ከፀጥታ ሀይል ለማምለጥ ሲል በሻፋሞ ጫካ ለጫካ ሲዘዋወር እንደነበረ እና ተጠርጣሪው ግለሰብ ወንጀሉን ለመፈጸም ሲጠቀምባቸው ከነበሩ አንድ ክላሽንኮቭ የጦር መሳሪያና ሽጉጥ ጋር ህዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. መያዙን የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቆ ነበር።
መረጃው ተዘጋጅቶ የተላከው በአዲስ አበባ የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ነው።