በኢራን የጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒን 4ኛ የሙት አመት እያከበሩ በነበሩ ሰዎች ላይ በደረሰ ሁለት የቦንብ ፍንዳታ ሰዎች የሟቾች ቁጥር ከ103 በላይ ደረሰ። አልጀዚራ በየደቂቃው መረጃ በሚሰጥበት አውዱ ላይ እንዳለው የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨመር ይችላል። የሀገሪቱ ሚዲያ ባለስልጣናቱን ጠቅሶ እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል።
አንዳንድ ሚዲያዎች ሶስት ያደረሱት ተከታታይ ፍንዳታ በደቡባዊ ኢራን በምትገኘው ካርማን ከተማ ሳሄብ አል-ዛማን በተባለው መስጊድ አቅራቢያ ነው የደረሰው። በፍንዳታው ከ180 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ተመልክቷል።
በአሜሪካ ከተገደሉ አራተኛ ዓመት የሆናቸው የኢራኑ ጀኔራል ቃሲም ሱሌማኒ አራተኛ ሙት ዓመት በመቃብራቸው አካባቢ በፈነዱ ቦምቦች የደረስውን ጉዳት ተከትሎ የከተማዋ ምክትል አስተዳዳሪ የቦንብ ፍንዳታው የሽብር ጥቃት ብለውታል።

ከአያቶላህ አሊ ሃሚኒ በመቀጠል በኢራን ወታደራዊ ሀይል ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ጄኔራል ቃሲም ሱሊይማኒ በ2020 በኢራቅ ባግዳድ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡
እኚህኑ የኢራን የፀረ ሽብር ዘመቻ አዛዥ ቃሲም ሱሊይማኒ 4ኛ የሙት ዓመት ለማስታወስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመቃብሩ ስፍራ በመገኘት ጄኔራሉን ሲያስታውሱ እንደነበር የሚያሳይ ምስል የአገሪቱ ሚዲያዎች አሳይተዋል።
በሌላ ዜና የሃማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን በቤይሩት በደረሰ ፍንዳታ መገደሉ ተሰምቷል። አል አሮሪ የተባለው የአንድ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሥራች እና የቡድኑ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል መሪ የተገደለው በእስራኤል እንደሆነም አንዳንድ መገናኛዎች እየገለጹ ነው። አል አሮሪ በዌስት ባንክ ሃማስን ማገልገሉም ነው የተነገረው፡፡
የሊባኖስ መንግሥት ብሔራዊ የዜና አገልግሎት እንደገለጸው በፍንዳታው የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ፤ በድሮን እንደተመታም አያይዞ ጠቁሟል፡፡ሃማስ በከፍተኛ አመራሩ ላይ ለተፈጸመውን ግድያ እስራዔልን ተጠያቂ አድርጓል።