በምስራቅ ሸዋ ዞን 569 የሽብር ቡድኑ ሸኔ አባላት መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እጃቸውን መስጠታቸውን የመከላከያና የመንግስት ሚዲያዎች አስታወቁ። ከዚህ በተጨማሪ ሰሞኑንን በተከታታይ የሰላም ጥሪን ተቀብለው በተለያዩ ግንባሮች እጃቸውን ለመንግስት መስጠታቸው ሲነገር ቆይቷል።
በምዕራብ ወለጋ ቤጊ ወረዳ፣ በሆሮ ጉድሩ፣ በምዕራብ ሸዋ በተከታታይ እጃቸውን ከሰጡትና ከተማረኩት በተጨማሪ ዛሬ ይፋ እንደሆነው ፓርላማ “አሸባሪ” ብሎ የሰየመው 569 የሸኔ ታጣቂዎች እጅ ሰጥተዋል።
“የሽብር ቡድኑ አባላት በሕዝብ ላይ ሲያደርሱት በነበረው ዘርፈ ብዙ በደል ተጸጽተው በሰላም እጃቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል” ሲል ፋና ዘግቧል። ባደረሱት በደል ህዝብ እና መንግስትን ይቅርታ የጠየቁት አባላቱ ፣ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል፡፡ ሌሎችም መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል እጃቸውን እንዲሰጡ መምከራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
እጃቸውን የሰጡትን ተጣቂዎች የተረከበውና በስፍራው የተቀናጀ ኦፕሬሽን እያካሄደ መሆኑን ያመልከተው የአገር መከላከያ በበኩሉ፣ ሸኔ የደረሰበትን ምት መቋቋምና ቆሞ የመዋጋት አቅሙ መዛሉን አመልክቷል።
“በምስራቅ ሸዋ ዞን የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው የሸኔ ቡድን ኮሩ በወሰደው የማያዳግም እርምጃ እየተደመሰሰም እጅ እየሠጠም ይገኛል” ያለው የመከላከያ ዜና አውታር፣ “በተሳሳተ መንገድ የሽብር ቡድኑን በመቀላቀል ለሽብር ቡድኑ በሎጀስቲክስ ፣ በተተኳሽ አቅርቦት፣ በሶሻል ሚዲያዎች የአሸባሪው ክንፍ በመሆን የህዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ የሸኔ አባላት የነበሩበት ሁኔታ የተሳሳተ እንደነበር ተናግረዋል” ብሏል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ የሽብር ቡድኑ በዞኑ ቦሰት ወረዳ፣ ሊበን ወረዳ፣ቦራ ወረዳ እና ፈንታሌ ወረዳዎችን በመያዝ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ በማድረግ በመሰረተ ልማቶች ላይ አደጋ ሲፈጥሩ እንደቆዩም ተናግረዋል።
የሸኔ ቡድን ተደጋጋሚ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበል በደል ሲፈፅሙ የቆየ ቢሆንም መከላከያና የክልሉ የፀጥታ ሃይል በወሰደው እርምጃ እጃቸውን መሥጠታቸውንም ገልጸዋል።
የኮሩ ምክትል አዛዥ ለኦኘሬሽናል ኮሎኔል ብርሃኑ አዱኛ “ኮሩ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ባደረገው ዘመቻ አብዛኛው የሽብር ቡድኑ ሃይል ሲደመሰሰ ቀሪው በሰላማዊ መንገድ እጁን ለመሥጠት ተገዷል” ማለታቸውን መከላከያ ጽፏል።

“ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር 01ብሬን፣ 01ስናይፐር ፣ 50 ክላሽ ፣ኋላቀር መሳሪያ ፣ 29ቦንብ ፣ የክላሽ ጥይት 2892፣የክላሽ ካዝና 72፣ የብሬን ጥይት 350 ገቢ ሆኗል” ሲል ዜናውን የቋጨው የመከላከያ ገጽ፣ ዘመቻው በሁሉም አቅጣጫ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።