ፑንትላንድ ሞቃዲሾ ለሚገኘው ለሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የሰጠችውን ዕውቅና ማንሳቷን በይፋ አስታወቀች፡፡ ውሳኔው የተወሰነው የራስገዟ ፑንትላንድ መንግሥት ካቢኔ ቅዳሜ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ባሳለፍውው ውሳኔ ነው፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ በተሰራጨው መግለጫ ፑንትላንድ በሶማሌ የፌደራል መንግሥቱ ተቋማት ላይ የነበራትን መተማመን በማጣቷ ሳቢያ ትሰጥ የነበረውን ዕውቅና ለማንሳት መወሰኑ ተመልክቷል፡፡ ዜናው ለፕሬዚዳንት ሃሰን ሼኽ አስደንጋጭ እንደሆነም የተለያዩ መገናኛዎች አመልክተዋል፡፡ የሶማሊያ መንግስትም ፑንት ላንድን ለዚህ ውሳኔ ያደረሳትን የህግ ማሻሻያ ስለማንሳቱ ወይም ዳግም እንደሚመለከተው ያለው ነገር የለም።
የሶማሊያ መንግሥት ፓርላማ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ውሳኔ ሰጥቷል። የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ካካተታቸው ጉዳዮች መካከል ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የማሰናበትን ሙሉ ሥልጣን የሚሰጥ ሲሆን አንድ ሰው አንድ ድምጽ የሚለውን ዓለም አቀፍ የምርጫ መርህ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያዘው ይገኝበታል።
ይህ የፑንትላንድ አስተዳደር ውሳኔ የተሰማው የሶማሊያ መንግሥት ፓርላማ ብዙ ባወዛገበ ሂደት በአገሪቱ ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ባለፈው ቅዳሜ ከላይ በተገለጸው አሳብ ይሁንታ መስጠቱን ተከትሎ ነው።
ይህ ለበርካታ ሳምንታት ብዙ ሲያነታርክ የቆየው የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ጊዜ ተወስዶ ሰፊ ውይይት እንዲደረግበት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሲጠይቁ መኖራቸው ይታወሳል።
ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ውሳኔን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የማሻሻሉ ሂደት የተከናወነው የአገሪቱን “የፌደራል ሥርዓት እና ብሔራዊ አንድነትን አደጋ ላይ በጣለ መልኩ በመሆኑ ውሳኔውን አጥብቆ እንደሚቃወመው አሳውቋል።
ውስብስብ የሆነውን እና በጎሳ መሠረት የሚደረገውን ምርጫ ከ50 ዓመታት በላይ ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ አሁን ‘ አንድ ሰው አንድ ድምፅ ‘ የሚለው ማሻሻያ በፑንትላንድ ባለልስጣናት ተቃውሞ ገጥሞታል። የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በፑንትላንድ በኩል ውድቅም ተደርጓል።
በዚሁም ሳቢያ ፑንትላንድ ” በጋራ መግባባት ላይ የሚደረስበት ሕገ መንግስታዊ ሂደት እስከሚፈጠር ድረስ የፑንትላንድ አስተዳደር ለፌዴራል ተቋማት እውቅና አይሰጥም፣ ተቋማቱ ላይም እምነት የለውም ” ስትል አቋሟን ይፋ አድርጋለች። ሕዝበ ውሳኔ ሪፈረንደም የሚደረግበት ሕገ መንግስት እስከሚወጣ ድረስ፣ ፑንትላንድ የራሷ የሆነ መንግስታዊ ስልጣን እንደሚኖራትም አስታውቃለች፡፡ እንደ አገር ፍላጎቷን ለማስጠቅ ከማዕከላዊ የሶማሊያ መንግሥት እውቅና ውጪ በራሷ አማካይነት የውጭ ግንኙነቶችን እንደምታደርግ ገልጻለች።
ይህ የፑንትላንድ ውሳኔ ከሶማሊያ ተነጥሎ ነጻ አገርነትን ከማወጅ ጋር ሊስተካከል እንደሚችል በመጥቀስ ከሶማሊላንድ ቀጥሎ ለፌደራል መንግሥቱ ሌላ ራስ ምታት እንደሚሆን ተንታኞች እየገለጹ ነው።
ፑንትለንድ በተፈጥሮ ሃብቶችና በቦሳሶ ወደቧ በመተማመን እ.አ.አ 1998 ነው ከፊል ራስ ገዝ መሆኗን ማወጇ ይታወሳል። አቅም አልባው የሃሰን ሼክ መንግስት ከዞማሊ ላንድና ከፑንት ላንድ ጋር ያለውን ችግር በየትኛውም የሃይል አግባብ ማስተካከል ወይ ጫና ማሳደር አለመቻሉ እየታወቀ በዚህ ደረጃ የበላይ ለመሆን መዳዳቱ ችግሩን እንዳሰፋው በርካቶች ይስማማሉ።
ሶማሊያ ስድሳ ከመቶ የሚሆነው ክልሏ በኢትዮጵያ ጦር የሚጠበቅ ሲሆን የተቀረው ደግሞ በሰላም አስባሪ ሃይልና በሶማሊያ ጦር በጋራ የሚጠበቅ መሆኑ ይታወሳል። በተመሳሳይ ፑንት ላንድና ሶማሊላንድ አንድም የሽብር ስጋት የሌላቸው፣ ራሳቸውን ችለው ሰላማቸውን የሚያስጠብቁ ናቸው።