ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ለአንድ ሳምንት በብድር ጉዳይ ውይይት ካደረጉ በሁዋላ ስምምነት መፈረሙ ይፋ ሆነ። ውይይቱ ሙሉ በሙሉ ስምምነት የተደረሰበት ባይሆንም “ከሽፏል” ሊባል የሚችል እንዳልሆነ ተመልክቷል። “ድርድሩ ከሽፏል” በሚል በቅብብል ያስታወቁት ሚዲያዎች የ1.7 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ስለመደረጉ ያሉት ነገር የለም።
ቢቢሲ ሮይተርስን ምንጭ አድርጎ በአፕሪል 3 “አይኤምኤፍ የጉብኝቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በድርጅቱ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አልቫሮ ፒሪስ የተመራ ቡድን ከመጋቢት 10 አስከ 24/2016 ዓ.ም. ለሁለት ሳምንታት ያደረገውን ቆይታ ማጠናቀቁን አስታውቋል” ሲል ዜናውን ይጀምራል።
ቢቢሲ ሲያክል ፒሪስ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ አይኤምኤፍ የአገሪቱን የምጣኔ ሃብት ፕሮግራሞች መደገፍ በሚችልበት ሁኔታ አዎንታዊ ንግግሮች ማድረጋቸውን እና ውይይቱ በቀጣይ ሳምንታት በዋሺንግተን እንደሚቀጥል ማስታወቃቸውን አመልክቶ ሮይተርስን ዋቢ በማድረግ “… አይኤምኤፍ የብድር ስምምነት ሳይደርስ የኢትዮጵያ ቆይታውን ማጠናቀቁ አገሪቱ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎቿ የሚጠበቅባትን እንዳትወጣ እክል ይሆናባታል” ብሏል።
የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ባለሙያ ሲል ጠርቶ ቢቢሲ ያናገራቸው አብዱልመናን መሐመድ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ብድር የማታገኝ ከሆነ ለአገሪቱ መንግሥት ትልቅ ራስ ምታት ይሆናል” ማለታቸውንም አመልክቷል።
ይህ ዜና ከተሰራጨ አንድ ቀን በሁዋላ የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መንግስት መገናኛዎች ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የ1 ነጥብ 72 ቢሊየን ዶላር የፍይናንስ ድጋፍና የብድር ስምምነት መፈራረማቸውን ይፋ አድርገዋል።

የብድርና የድጋፍ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትንና እድገትን ለማምጣት ለታቀዱ ስድስት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር እንደሚውል ፕሮጀክቶቹን በመዘርዘር አመልክተዋል።
ድጋፍና የብድር ስምምነቱ ለምግብ ዋስትና መርሐግብርን ለመደገፍ፤ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ለማጠናከር፤ በቆላማ አካባቢዎች ለሚገኙ አርብቶ አደርና አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ኑሮንና የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ፤ ለሀይል አቅርቦት ማሻሻያ፣ ለሁለተኛው የከተማ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት እንደሚውል ተገልጿል።
ከባንኩ ከተገኘው ብድር 523 ሚሊዮን ዶላር የሚደርሰው በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማስፋፋት እና የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን አቅም ለማጎልበት እንደሚውል የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።
ተጨማሪ 500 ሚልዮን ዶላር ደግሞ በገጠራማ አካባቢዎች የትራንስፖርት መንገዶችን ግንባታ ጨምሮ የምግብ ገበያ ተደራሽነትን ለማሻሻል ለታቀዱ ሁለት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።
ብድሩ በዝቅተኛ ወለድ ወይም ከወለድ ነጻ እስከመሆን የሚዘልቅ እንዲሁም የመክፈያ ጊዜውም ከ30 እስከ 40 እንደሆነ ተመልክቷል። ሁለቱ አካላት ውይይታቸውን በአሜሪካ እንደሚቀጥሉ ተመልክቷል።
በውይይቱ ልዩነት የፈጠረውና መግባባት ላይ መድረስ ያልተቻለው ባንኩ መንግስት የብርን የምናዛሬ መጠን ዝቅ እንዲያደርግ ወይም ዲቫሉዌት እንዲያደርግ የቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ እንደሆነ ውይይቱን የተከታተሉ አመልክተዋል። ቀታይ ውይይቱም እዚህ ላይ እንደሚሆን እነዚሁ ወገኖች አስታውቀዋል። መንግስት የጠየቀው 3.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም ታውቋል።