ከ300 በላይ የሚሆኑት ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ከኢራን፣ ኢራቅ እና ከየመን ወደ እስራኤል የተተኮሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ተወንጫፊዎች አብዛኞቹ ጉዳት ሳያደርሱ በእስራኤል እና በወዳጆቿ አማካይነት እንዲከሽፉ መደረጋቸው ተነግሯል።
የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ፒተር ለርነር ለቢቢሲ እንደተናገሩት “360 የተለያዩ ተወንጫፊዎች ወደ እስራኤል ተተኩሰው ነበር።”
ከእነዚህም ውስጥ 170 ከዒላማቸው ጋር ተላትመው የሚፈነዱ ድሮኖች፣ 150 የተለያዩ ዓይነት ሚሳኤሎች ወደ አስራኤል መተኮሳቸውን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።
ኢራን ደማስቆ ውስጥ በሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ከሳምንት በፊት ጀምሮ በእስራኤል ላይ ትፈጽመዋለች ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የበቀል ጥቃት ቅዳሜ ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ተግባራዊ አድርጋዋለች።
ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ብታስወነጭፍም 99 በመቶ የሚሆኑት ጉዳት ሳያደርሱ እንዲከሽፉ መደረጋቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
እስራኤል ካሏት የሚሳኤል መከላከያ ጋሻዎቿ በተጨማሪም ወዳጅ አገራት ከኢራን በኩል የተሰነዘረባትን ጥቃት በማክሽፍ በኩል መሳታፋቸው እየተነገረ ነው።
በዚህም ዮርዳኖስ በግዛቷ በኩል የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን መትታ የጣለች ሲሆን፣ የአሜሪካ ሠራዊትም በርካታ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን ከአየር ላይ እንዲከሽፉ ማድረጉን የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን አሳውቀዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይም ከጥቃቱ በፊት የአየር ቅኝት በማድረግ እስራኤልን የመከላከል ተግባር መፈጸማቸውን የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልጸዋል።
- በእስራኤል የአየር ጥቃት ስለተገደሉት የሐማሱ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ ልጆች የሚታወቁ ጉዳዮችከ 6 ሰአት በፊት
- ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ትፈጽማለች በሚል ስጋት አሜሪካ ለዜጎቿ ማስጠንቀቂያ አወጣች12 ሚያዚያ 2024
- የተረሳው ግጭት እና ከአስከፊ የረሃብ ቀውስ አፋፍ ላይ የምትገኘው ሱዳንከ 6 ሰአት በፊት
በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ወደ ከፍተኛ ደረጃ በወሰደው ጥቃት ኢራን ጠላቷ አድርጋ በምትቆጥራት እስራኤል ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ስትፈጽም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ኢራን በጋዛ እስራኤልን እየተዋጋ ያለውን ሐማስን እንዲሁም በቀጠናው የእስራኤል ጠላት የሆኑትን ሄዝቦላህ እና የየመን ሁቲ አማጺያንን በመደገፍ እስራኤል ላይ በእጅ አዙር ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የመክፈቷ ዜና ኢራናውያን ወደ አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን አንዲገልጹ አድርጓቸዋል።
ይህ የኢራን ጥቃት ድንገት የተከሰተ አይደለም። ኢራን ከ11 ቀናት በፊት በሶሪያ ዋና ከተማዋ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤቷ ላይ በተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ቆይታለች።
ቴህራን በቴል አቪቭ ላይ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ይባባሳል በሚል አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን ለኢራን ማሳሰቢያዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል።
ኢራን እራሳቸውን እያጋዩ ዒላማቸውን የሚመቱ ድሮኖችን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን እስራኤል ላይ መተኮሷ ተዘግቧል።
እስራኤል ሚሳኤሎቹን እና ድሮኖቹን የአየር ክልሏ ውስጥ ሳይገቡ መትታ መጣሏን ገልጻለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የኢራንን ጥቃት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካ የጦር መርከብ ድሮን እና ሚሳኤሎቹን መትተው ጥለዋል ብለዋል።
“እስራኤል ሁሉንም ለማለት በሚቻል መልኩ መትታ እንድትጥል አግዘናል” ብለዋል ባይደን።
“ኢራን እና በየመን፣ ሶሪያ እና ኢራቅ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር በመጣመር የእስራኤል ጦር መዕክላትን ዒላማ ያደረገ ከፍተኛ የሆነ የአየር ጥቃት ከፍታለች” ብለዋል ባይደን።
ጥቃቱን ተከተትሎ የኢራን እስላማዊ ብሔራዊ ዘብ የኢራን ዒላማዎች “የተለዩ ቦታዎች ናቸው” ብሏል።
የኢራን ጥቃት እንደተጀመረ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የጦር ካቢኔያቸውን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።
ከዚያም ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል። በንግግራቸው ባይደን አሜሪካ ለእስራኤል “የማይነጥፍ ድጋፍ” እንደምታደርግ አረጋግጠዋል ተብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ ኢራን ያስወነጨፈቻቸው አብዛኛዎቹ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ገና የእስራኤል የአየር ክልል ውስጥ ሳይገቡ መወገዳቸውን ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ እስራኤል የአየር ክልል ውስጥ መግባት የቻሉት በሰው ሕይወት ላይ ያደረሱት ሞት ባይኖርም በወታደራዊ ቦታዎች ላይ አነስተኛ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል።
“ውጥረቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያደርስ የኢራን ጥቃት ተፈጽሞብናል። በአሁኑ ወቅት እስራኤልን እና የእስራኤልን ሕዝብ ለመከላከል ከአጋር አገራት ጋር ሆነን በሙሉ ኃይል እየከላከልን ነው” ብለዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ ኢራን ከሳወነጨፈቻቸው 300 ተተኳሾች መካከል እስራኤል 99 በመቶ የሚሆኑትን አየር ላይ መትታ ጥላለች። ቃል አቀባዩ አንዳንዶቹ የተተኮሱት ከኢራቅ እና ከየመን ነው ብለዋል።
ሁለት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለሲቢኤስ እንደተናገሩ በአካባቢው ያሉ የአሜሪካ ኃይሎች በርካታ የኢራን ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን መትተው ጥለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከአሜሪካ በተጨማሪ በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኝ የዩናይትድ ኪንግደም አየር ኃይል እስራኤል ላይ የተጠቃጣውን የአየር ጥቃት ለማክሸፍ ተሰማርቷል።
የኢራን ጥቃት እንደተጀመረ በእየሩሳሌም ከተማ የአደጋ ጊዜ ደውል ተደውሎ ነበር። በከተማዋ የፍንዳታ ድምጽም ይሰማ ነበር።
በአሁኑ ወቅት እስራኤል፣ ሌባኖስ እና ኢራቅ የአየር ክልላቸውን የዘገቡ ሲሆን የሶሪያ እና ጆርዳን መንግሥታት ደግሞ የአየር ኃይላቸውን በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዋል።
የኢራንን ጥቃት የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እንዲሁም የአሜሪካ እና የዩኬ መሪዎች አውግዘዋል።
ሙሉ ዘገባው የቢቢሲ ነው