ወሎ ሠፈር ማዞሪያ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የግል ማኅበር፣ 60 በመቶ ባለድርሻ የሆኑትን ሼክ መሐመድ ዓሊ አላሙዲንን፣ ከባለድርሻነት እንዲወጡ ወይም ማኅበሩ እንዲፈርስ፣ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ክስ የመሠረቱ ቢሆም፣ ክሱን የመረመረው ፍርድ ቤት እራሳቸው አቶ አብነት ከባለድርሻነት እንዲወጡ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጠ፡፡
የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ችሎት፣ አቶ አብነት ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ያቀረቡትን የክስ አቤቱታ ሲመረምር ቆይቶ በተጠቀሰው ቀን ውሳኔ የሰጠው፣ ስለክሱ አነሳስ፣ በተመሳሳይ ጉዳዮችን ላይ ሰበር ስለሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ውሳኔዎች፣ የንግድ ሕጉንና ሌሎች ተዛማች ሕጎች፣ በስፋት ከመረመረ በኋላ መሆኑን የፍርድ ሀተታው ያሳያል።
ቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተቋቋመው ከ22 ዓመታት በፊት በሼክ መሐመድ 60 በመቶ ባለድርሻነትና በአቶ አብነት 40 በመቶ የባለድርሻነት በአሥር ሚሊዮን ብር በተከፈለ ካፒታል ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. ካፒታሉ ወደ 545 ሚሊዮን እንዲያድግ መደረጉንም የክሱ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
አቶ አብነት በክሳቸው ስለተቋሙ ሲያስረዱ፣ ሁለቱም ባለድርሻዎች እንደ ድርሻቸው መጠን ባሳደጉት ካፒታል መጠን ክፍያ ለመፈጸም በተስማሙት መሠረት፣ እሳቸው ከ1992 እስከ1997 ዓ.ም. ድረስ በሊዝ ይዘውት የቆዩትን የግል ይዞታ ለማኅበሩ በመክፈል (በመስጠት) የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ ነገር ግን ክስ የተመሠረተባቸው ሼክ መሐመድ ወይም ማኅበሩ ግን ምንም ነገር እንዳልከፈሉ ክሱ ያስረዳል፡፡ ማኅበሩ (ቦሌ ታወርስ) በ5,189 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እያስገነባ ባለው ሕንፃ፣ ሼክ መሐመድ ባላቸው የድርሻ መጠንና ሁለቱም ባለድርሻዎች በስምምነት ባሳደጉት ካፒታል (545,000,000 ብር) ለግንባታው እንዲከፍሉ የተስማሙ ቢሆንም፣ ሼክ መሐመድ ሊከፍሏቸው አለመቻላቸውን አቶ አብነት በክሳቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ አብነት የማኅበሩን ሕንፃ ለማስጨረስ ከዳሸን ባንክ 425,000,000 ብር በመበደር የሕንፃውን ቦሌ ኤ እና ቦሌ ቢ ተብለው ከተሰየሙት ውስጥ ቦሌ – ኤ የሚባለውን የተወሰነውን አስገንብተው መጨረሻቸውንና የተወሰነውን ክፍል ለኪራይ እንዲውል መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
ከሳሽ በክሱ እንዳብራሩት እሳቸው (አቶ አብነት) ያላቸውን ልምድ፣ ገንዘብና ዕውቀት ተጠቅመው ሕንፃውን ቢያጠናቅቁም፣ ሼክ መሐመድ በድርሻቸው መጠን ክፍያ እንዲፈጽሙላቸው ሲጠይቋቸው ባለመስማማታቸው፣ ማኅበሩ ከዳሸን ባንክ የተበዳሪውን 425,000,000 ብርና ሌች ወጪዎችን እንዲከፍሏቸው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ምድብ ችሎ ክስ መሥርተው በሒደት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሼክ መሐመድም በተመሳሳይ ሁኔታ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ጉዳዮ ችሎት ክስ መሥርተው፣ ክሱ በሒደት ላይ መሆኑን አቶ አብነት በክሳቸው ጠቁመው፣ ማኅበሩ ቦሌ – ሲ እና ቦሌ – ዲ ተብለው የሚታወቁ 3,383 ካሬ ሜትርና 1,971 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ይዞታዎች ላይ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፣ ለግንባታው 120,000,000 ብር ያወጡ በመሆኑ እንዲከፈላቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመሥረታቸውንም በክሱ አካተዋል፡፡
አቶ አብነት መልካም ስማቸው እየጠፋና ማስፈራራት እየደረሰባቸው መሆኑን፣ ከአገር እንዳይወጡ ዕግድ እንደወጣባቸው፣ ከቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅነት እንዲነሱ መደረጋቸው አግባብ አለመሆኑን፣ ሼክ መሐመድ በእሳቸው ላይ (አቶ አብነት ላይ) በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከስምንት በላይ የክስ ፋይል እንደከፈቱባቸውና በርካታ የማይንቀሳቀሱና የሚንቀሳቀሱ ንብረቶቻቸው ዕግድ በማውጣት እንቅፋት እንደፈጠሩባቸው በዝርዝርና በስፋት በክሳቸው አቅርበዋል፡፡
አቶ አብነት በእሳቸውና በሼክ መሐመድ መካከል በመከባበርና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደነበራቸው አስታውሰው፣ ከጊዜ በኋላ ግን መልካም ግንኙነታቸው እየሻከረና እየከረረ በመምጣቱ፣ ‹‹ብርቱ›› ያለመግባባት በመፈጠሩ የማኅበሩን ዓላማ ከግብ እንዳይደርስ የሚያስደርግ ደረጃ ላይ መድረሳቸውንና ግንኙነታቸው ወደ ጠላትነት ስሜት መሸጋገሩን የሚያሳዩ ስሜቶች መፈጠራቸውን አብራርተዋል፡፡ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲታይ ቢደረግም፣ በሼክ መሐመድ በኩል ፍላጎት ባለመኖሩና ሊሳካ ስላልቻለ፣ ከሼክ መሐመድ ጋር ባለድርሻ ሆኖ ማኅበሩን ማስቀጠል የማይቻል ደረጃ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም አቶ አብነት ማኅበሩን በሥራ አስኪያጅነት በመምራት፣ እንዲሁም የ40 በመቶ ባለድርሻ በመሆን ለረዥም ዓመታት በመሥራት ግዙፍ ሀብት እንዲኖረው ማድረጋቸውን አስረድተው፣ ሼክ መሐመድ ድርሻቸውን ይዘው በማኅበሩ እንዲወጡና እሳቸው በሕጉ መሠረት ማኅበሩን ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አድርገው ማስቀጠል እንዲችሉ ወይም ማኅበሩ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤቱ የክስ አቤቱታ ማቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ አብራርቷል፡፡
ሼክ መሐመድ ለቀረበባቸው ክስ ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት ምላሽ፣ ማኅበሩ ከተቋቋመበትን 10,000 ብር ውስጥ የድርሻቸውን መክፈላቸውን፣ አቶ አብነት ግን አለመክፈላቸውን፣ (ገቢ አለማድረጋቸውን)፣ የማኅበሩ ካፒታል 545,000,000 ብር እንዲሆን ቢወሰንም ለማኅበሩ ገቢ አለማድረጋቸውን፣ የማኅበሩ ሕንፃ የተገነባው በእሳቸው (በሼክ መሐመድ) ሙሉ ወጪ መሆኑን፣ አቶ አብነት ከ1992 እስከ 1997 ዓ.ም. በግል ይዞታነት ይዤዋለሁ የሚሉትና ለማኅበሩ እንደሰጡ የሚናሩት ትክክል እንዳልሆነና በርካታ ቁጥር ጨ0430 በሊዝ የተሸጣቸው 2,000 ካሬ ሜትር ብቻ መሆኑን በመግለጽ፣ ክሱን ክደው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ላይም በግልጽ መቀመጡንም አክለዋል፡፡
አቶ አብነት በመመሥረቻ ጽሑፍ በተቀመጠው መሠረት በተሰጣቸው የሥራ አስኪያጅነት ሥልጣን ግዴታቸውን መወጣት ሲገባቸው፣ ከላይ የተጠቀሰውን ይዞታ የራሳቸው እንደሆነ አድርገው ለማኅበሩ ማስፋፊያ የተሰጠውን 3,189 ካሬ ሜትር ይዞታ ከራሳቸው ይዞታ (2,000 ካሬ ሜትር) ጋር ቀላቅለው የይዞታ ምስክር ወረቀት ማውጣታቸውንም በምላሻቸው አብራርተዋል፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተ 1994 ዓ.ም. ወዲህ የአቶ አብነት ማናቸውም መብትና ግዴታዎች ወደ ቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መተላለፋቸውንና አቶ አብነት ግን ምንም ዓይነት ክፍያ አለመክፈላቸውን አክለዋል፡፡ አቶ አብነት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ በርካታ ጥፋቶች መሥራታቸውንና ያቀረቡት ክስ ሐሰት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ አብነት የማኅበሩን ሕንፃ ለማስጨረስ 425,000,000 ብር ተበድሬያለሁ ቢሉም፣ ሼክ መሐመድ ግን ክደው ተከራክረዋል፡፡ በክርክራቸውም አቶ አብነት በከፍተኛ ዕውቀት ቀርቶ ዕውቀት የሌለው ሰው እንኳን በሚመራው አኳኋን ማኅበሩን እንዳልመሩት፣ በመመሥረቻ ጽሑፍ በተጠቀሰው መሠረት መሥራት ሲገባቸው፣ የንግድ ማኅበሩ በክፍለ ከተማው ማኅደር እንዳይኖረው በማድረግ ይዞታውን ወደ ግላቸው በማዞር እምነት ማጉደላቸውን ሼክ መሐመድ በመልሳቸው ገልጸዋል፡፡
ሼክ መሐመድ ከላይ ለጠቀሷቸው ችግሮች ክስ መመሥረታቸውን ጠቁመው፣ አቶ አብነት በማጭበርበር ያወጡት የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰረዝ ከመክሰሳቸውም በተጨማሪ፣ ማኅበሩ ከዳሸን ባንክ 425,000,000 ብር እንዲበደር አድርገው፣ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውንና በማኅበሩ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አብርራተዋል፡፡
በመሆኑም አቶ አብነት ማኅበሩ እንዲፈርስ ወይም እሳቸው (ሼክ መሐመድ) ከባለድርሻነት እንዲወጡ የጠየቁበት ክስ፣ የሕግ መሠረት ወይም የፍሬ ነገር ምክንያት እንደሌለው አስረድተው ክሱን ተቃውመዋል፡፡
አቶ አብነት በክሳቸው እንደገለጹት ሼክ መሐመድ በዝርዝር ባቀረቡት የመቃወሚያ መልሳቸው ላይ፣ አቶ አብነት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ የማኅብሩን ይዞታዎች ወደ ግላቸው በማዛወርና በመሸጥ፣ እንዲሁም ማኅበሩ ከዳሸን ባንክ የተበደረውን 425,000,000 ብር ወደ ራሳቸው፣ ባለቤታቸው፣ ልጃቸው፣ ወንድማቸው፣ ጓደኞቻቸው፣ ዘመዶቻቸውና ጉዳይ ፈጻሚዎቻቸው በማስተላለፍ፣ በማኅበሩ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ማድረሳቸውን በመግለጽ፣ ስምንት የክስ ፋይሎች ከፍተው ክሱ በሒደት ላይ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ አብነት ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም እሳቸው (ሼክ መሐመድ) በየወሩ 25,000 ዶላር ደመወዝ እንደሚከፍሏቸው በመግለጽ 14,000,000 ብር መውሰዳቸውንና አዲስ ፓርክ ከተባለው ድርጅት (ሚሊኒየም አዳራሽና ሌሎች ድርጅቶች) 35 ሚሊዮን ብር በመውሰዳቸው በሁለት ፋይል ክስ ማቅረባቸውንም በምላሻቸው አካተዋል፡፡
አገራዊ ጠቀሜታ ያለውን የንግድ ማኅበር በባለድርሻዎች አለመግባባት እንዲፈርስ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተው፣ አቶ አብነት ከማኅበሩ ጋር መቀጠል ካልፈለጉ ‹‹እሳቸው ባለድርሻነታቸውን ለቀው ወይም በሽያጭ አስተላልፈው›› ከሚወጡ በስተቀር፣ ተከሳሽ (ሼክ መሐመድ) የሚወጡበት ወይም ማኅበሩ የሚፈርስበት የሕግም ሆነ የፍሬ ነገር ምክንያት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
በከሳሽ (አቶ አብነት) በተከሳሽ (ሼክ መሐመድ) በስፋትና በዝርዝር የቀረበውን ክስና ምላሽ የተመለከተው ፍርድ ቤት፣ ‹‹በከሳሽና ተከሳሾች መካከል ብርቱ አለመግባባት አለ ወይስ የለም? አለ የሚባል ቢሆን አለመግባባቱ የማኅበሩ ዓላማ ከግብ እንዳይደርስ የሚያስተጓጉል ነው ወይስ አይደለም?፣ ሼክ መሐመድ ከማኅበሩ የሚወጡበት ሕጋዊ ምክንያት አለ ወይስ የለም?፣ ማኅበሩ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም?፣ በተከሳሽ (ሼክ መሐመድ) ከሳሽ (አቶ አብነት) ክስ ላይ የተገለጹትን ጥፋቶች፣ አቶ አብነት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም? እና ጥፋቶችን ፈጽመዋል የሚባል ቢሆን (አቶ አብነት) ከማኅበሩ አባልነት እንዲወጡ የሚያበቃ ሕጋዊ ምክንያት አለ ወይስ የለም? የሚሉ ጭብጦችን ይዞ ክሱን መመርመሩን የፍርድ ትንታኔው ያሳያል፡፡
ፍርድ ቤቱ የከሳሽ (አቶ አብነት) ሁለት ምስክሮችን በማስቀረብ እንዲመሰክሩ አድርጎ፣ ቦሌ ታወር ‹‹ኤ›› የሚባለው ሕንፃ ግንባታ 75 በመቶ መሠራቱን፣ ሌላው ግንባታ መቆሙን፣ አቶ አብነት ሲከታተሉ እንደነበርና ማሠሪያ ገንዘቡ ከማኅበሩና ከራሳቸው ወጪ ሲያደርጉ እንደነበርና ሌሎች ክፍያዎችንም ሲፈጽሙ እንደነበር ገልጸው፣ በሁለቱ ባለድርሻዎች መካከል አለመግባባት ቢኖርም ምክንያቱን እንደማያውቁ መመስከራቸውን የፍርድ ሰነዱ ያብራራል፡፡
ፍርድ ቤቱ በከሳሽና ተከሳሽ መካከል ‹‹ብርቱ›› አለመግባባት አለ ወይስ የለም? ማኅበሩ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ሲመረምር፣ ያስቀደመው ‹‹በማኅበሩ አባላት መካከል ብርቱ አለመግባባት አለ ወይስ የለም?›› የሚለውን ከንግድ ሕጉ አንቀጽ 181 እና አንቀጽ 531 ድንጋጌ መሠረት፣ እንዲሁም የሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 153981 ላይ ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንፃር ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ብርቱ አለመግባባት አለ›› በማለት አቶ አብነት የጠቀሷቸው ጉዳዮችና ዝርዝር የክርክር ወይም የክስ ሒደቶች፣ በማኅበሩ አባላት መካከል ብርቱ አለመግባባት አለ የማያስብሉ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ እንዳደረሰው ገልጿል፡፡
ክሱ በዋናነት በአቶ አብነትና በሼክ መሐመድ መካከል በመሆኑ፣ የቀረቡትም ክሶችና ክርክሮች በሚያዩዋቸው ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት የሚያገኙ ቢሆን፣ ማኅበሩን የሚጠቅሙ እንጂ የማይጎዱ በመሆኑ፣ ሼክ መሐመድ በአቶ አብነት ላይ ክስ መመሥረታቸው በማኅበሩ አባላት ላይ ብርቱ አለመግባባት አለ የማያስብል መሆኑንም አብራርቷል፡፡ የማኅበሩን ዓላማ ከግብ እንዳይደርስ የሚያስተጓጉል ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን በሚመለከት ደግሞ፣ ፍርድ ቤቱ ብርቱ አለመግባባት እንደሌለ ብይን በመስጠቱ ጭብጡን አልፎታል፡፡
ሼክ መሐመድን ከማኅበሩ አባልነት ማውጣት የሚያስችል የሕግ መሠረት ወይም ፍሬ ነገር መኖር አለመኖሩን ሲመረምር፣ ከላይ በተጠቀሱ ሕጎችና አስገዳጅ የሰበር የሕግ ትርጉሞች አንፃር ‹‹በቂ ምክንያት›› አለመኖሩንና ከላይ ብይን በተሰጠበት ‹‹ብርቱ አለመግባባት›› ስለሌለ፣ አቶ አብነት የጠየቁት ሼክ መሐመድ ከአባልነት ይውጡ ጥያቄን ውድቅ አድርጎታል፡፡
አንዳቸው ሌላኛቸውን ከማኅበሩ እንዲወጡ ወይም ማኅበሩ እንዲፈርስ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 498 ድንጋጌ መሠረት ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበለው በፍርዱ ገልጿል፡፡
ቦሌ ታወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሊፈርስ አይገባም በመባሉ፣ በማኅበሩ አባልነት ሊቀጥል የሚገባው ከሳሽ (አቶ አብነት) ወይስ ተከሳሽ (ሼክ መሐመድ) የሚለውን በሚመለከት፣ ፍርድ ቤቱ ሼክ መሐመድ ባቀረቡት በተከሳሽ (ሼክ መሐመድ) ከሳሽ (አቶ አብነት) ክስ ላይ፣ አቶ አብነት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ፈጽመዋቸዋል በሚል የተገለጹ ጥፋቶች እንዲሁም ከማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ሁኔታ አንፃር፣ ማኅበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ ከተከሳሽ (ሼክ መሐመድ) ይልቅ ከሳሽ (አቶ አብነት) ከአባልነት ቢሰናበቱ እንደሚሻል ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ይኼ ሲባልም ተሰናባቹ (አቶ አብነት) ካለ በቂና ሕጋዊ ምክንያት እንዳይሆን የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አብራርቷል፡፡
አቶ አብነት በተከሳሽ (በሼክ መሐመድ) በቀረበባቸው የተከሳሽ ከሳሽ ክስ ላይ እንደተብራራው፣ ማኅበሩን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ከፈጸሟቸው ጥፋቶች አንፃር፣ ተከሳሽ (ሼክ መሐመድ) ጥፋት ስለመፈጸማቸው በማስረጃ የቀረበባቸው የተረጋገጡ ፍሬ ነገር እንደሌለ ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ተንትኖ አቅርቧል፡፡