“የሚሊሻ ኀይሉን በተመለከተ የሚዘዋወረው መረጃ ፍጹም መሠረተ ቢስ ነው” ሲሉ ኮሎኔል ግርማ ገሰሰ አስታወቁ። “ቅጥፈት ነው” ያሉትና በፕሬዚዳንቱ ስምና ፊርማ የተሰራጨው ደብዳቤ የሚሊሻ ሃይሉ ጸጥታ በማስከበሩ ስራ መውጪያ መግቢያ እየለየ ውጋት ስለሆነባቸው ተላቶች ሆን ብለው ከቅዠት የተነሳ ያሰራጩት እንደሆነም አመልክተዋል።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አማካኝነት እንደተጻፈ እና ለሁሉም ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች እንዲደርስ በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወር ደብዳቤ ቅንብሩ ከዚህ የሚከተለው ነው
ይህ ሐሰተኛ ደብዳቤ “የአማራ ክልል ሚሊሻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ቢኾንም ከጽንፈኛ ኀይሎች ዛቻ እና ማስፈራሪያ በቤተሰቡ እና በንብረቱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በመስጋት ከትግሉ ሜዳ የመሸሽ አዝማሚያ እና በጽንፈኛ ፕሮፓጋንዳ በመጠለፍ የጸጥታ አካላት የሚያደርጉትን ተጋድሎ ወደፊት እንዳይራመድ እና በድል እንዳይገሰግስ እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለኾነም በየዞኑ የሚገኙ የሚሊሻ አባላት ለሥልጠና በሚል ወደ አንድ ማዕከል እንድታስገቧቸው እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድታግባቧቸው ካልኾነም በአስገዳጅ ሁኔታ ትጥቅ አውርደው በካምፕ እንዲቀመጡ እና ሌላ ትዕዛዝ እስኪመጣ በመከላከያ እንዲጠበቁ እንድታደርጉ ለማሳሰብ እወዳለሁ” ይላል፡፡
የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮሎኔል ግርማ ገሰሰ የአማራ ክልል የሚሊሻ ኀይልን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወረውን መረጃ በተመለከተ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም በክልሉ መንግሥት እንዲህ አይነት ውሳኔም እርምጃም የለም፤ መረጃው ፍጹም መሠረተ ቢስ ነው ብለዋል፡፡
ጠላት መንግሥትን እና የሚሊሻ ኀይሉን ግጭት ውስጥ ለመክተት እና የሚፈልገውን ነገር ለማሳካት አስቦ የነዛው ሐሰተኛ መረጃ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ መረጃው ባልበላውም ጭሬ ላፍስሰው አይነት ብሒል ያዘለ ነውም ብለዋል፡፡ በሚሊሻ ኀይሉ እንዲህ አይነት ውሳኔ ለመወሰን የሚያስገድድ ሁኔታ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡
የሚሊሻ ኀይሉ ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመኾን ችግሮችን እየተጋፈጠ፣ እየተዋጋ ያለ ነው ያሉት ኀላፊው መንግሥት በሚሊሻ ኀይሉ ላይ ምንም አይነት ጥርጣሬም ስጋትም የለበትም ብለዋል፡፡ ደብዳቤው ተራ አጭበርባሪዎች የጻፉት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ጠላት አተኩሮ የሚሠራው የበለጠ ጥቃት በሚያደርስበት ኀይል ላይ ነው ያሉት ኀላፊው በሚሊሻ ኀይሉ ላይ የተነዛው ሐሰተኛ ወሬ ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
የሚሊሻ ኀይሉን ወደ ዞን አሠባሥቡ የሚለው አገላለጽ በራሱ ክልሉ ያለውን የሚሊሻ ኀይል ያልተረዳ እንደኾነ የሚያመላክት መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በሚሊሻው ላይ የተነዛው ሐሰተኛ ወሬ የጽንፈኞች የቀን ቅዥት ካልኾነ በስተቀር ምንም ነገር የለም ብለዋል፡፡ የሚሊሻው ሥራ መሬት ላይ በተግባር የሚገለጽ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በሐሰተኛ ወሬው ማኅበረሰቡ እንደማይደናገርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የሚሊሻ ኀይሉም ስጋት ይገባዋል የሚል ጥርጣሬ የለንም ነው ያሉት፡፡ በክልሉ በእያንዳንዱ የጸጥታ ስምሪት ውስጥ የሚሊሻ ኀይሉ መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ የጠላት መሪዎች እና አባላት ሚሊሻው መመታት አለበት እያሉ በተደጋጋሚ እንደሚናገሩ የገለጹት ኀላፊው ሚሊሻው ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸውን ያውቃል፤ የሚሊሻ ኀይሉ መሠረታቸውን የሚነቅል በመኾኑ ስለሚሊሻው ብዙ ነገር ይላሉ ብለዋል፡፡
ሚሊሻው የጠላትን መውጫ እና መግቢያ ጠንቅቆ የሚያውቅ እና እረፍት የሚነሳ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ የሚሊሻ ኀይሉ ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመኾን የክልሉን አካባቢዎች ከጽንፈኞች እያጸዳ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሚሊሻ ኀይሉ ግንባሩን ሳያጥፍ ለክልሉ ሰላም እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ የሚሊሻው የማድረግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በተሳሰተ መረጃ እንዳይደናገርም አሳስበዋል፡፡
