ያለፈውን ግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ሥነ መንግሥት ታሪክ በጥሞና የተከታተለ ኢትዮጵያዊ የግዛት አንድነቷን እና የፖለቲካ ነጻነቷን በአንጻሩ ጠብቃ የኖረች ሀገር፤ ከአሁን በኋላ በዜጎቿ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሃቀኛ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስርታ ሁሉንም ዜጎቿን በእኩልነት ማቀፍ ካልቻለች እንደ ሀገር በጋራ የመቀጠል እጣ ፋንታዋ የመነመነ መኾኑ ይገለጥለታል፡፡
በርካቶች የሚስማሙበት አንድ ሃቅ ቢኖር ኢትዮጵያ ውስጥ እዛም እዚህም የሚደረጉት ግጭቶችና ግጭት ጠንሳሾቹን ለመደገፍ የሚደረገው ርብርብ ባጭሩ አገር አልባ ለመሆን የመጎምጀት ያህል ነው። አፈር አላባ ሆኖ ለበተን የሚደረግ ጥድፊያ ነው። በጎበዝ አለቃዎች መካከል በሚደረግ ማብቂያ የሌለው የጦርነት ማጥ ውስጥ ለመግባት የሚደረግ መንደርደር ነው። ባጭሩ ጥቂቶች እጅግ ተንቀዥቅዠዋል። ይህ ሲባል ችግር የለም ለማለት ሳይሆን “አለ” የሚባለውን ችግር ለመፍታት ትግል ጀመረናል የሚሉት አካላት አካሄድ ችግር የሚፈታ አለመሆኑ እንጂ።
የክልልነት ጥያቄ ቢዝነስ በሆነበት፣ ብሄር ውስጥ የተሸሸገ የነጻ አውጪነት ትግል ታላቅ ኢንቨትመንት በሆነባት ኢትዮጵያ ማስተዋል ካልተቻለና አብዛኞች ተስማምተው እንደሚያደርጉትና እያደረጉ እንዳለው ተባብሮ አጉል አካሄዶችን ማረቅ ካልተቻለ፣ ሌሎች የደረሳቸው ዕጣ ቀኑንን ቆጥሮ መድረሱ ጥርጥር የለውም።
ሊቢያን የውጭ ሃይሎች አፍርሰው ለጎበዝ አለቆች አስረከቧት። የምድራቸውን ስብ እየዛቁ በቅንጦት ይኖር የነበረ ህዝብ አገር አልባ ሆነ። ሲሪያና የመን እንዲሁም ሶማሊያ በተመሳሳይ ምሳሌ ናቸው። ደጋግሞ ዳር ዳር እያለን፣ ሲብስም አገሪቱን እሳት በሳት አድርጎ የተፋው እሳት አሁንም እያግፈገመገ ነው። የቅርቡ ጥቁር ዲዜ ተረስቶ ጸብ ያለሽ በዳቦ እየተባለ ነው። “አንተ አይገባህም” የሚሉ “እኔ ካልገዛሁ” ብለው ሰክረው ህዝብን በጥላቻ እያሰከሩት ነው። በየደቂቃው ኢትዮጵያ ላይ የሚወርደው የጥፋት ቅስቀሳ መዓት ልቡና ላላቸው ” ምን ተፈጎ ነው” ይሰኛል። መልስ ግን የለውም።
ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሌት ተቀን የሚተጉትን የታከኩ በገሃድ ” በእኔ ዕድሜ ኢትዮጵያ ፈርሳ ከማየት በላይ የሚያረካኝ ነገር የለም” ሲሉ ከመስማት በላይ ምን ማስረጃ ተፈልጎ ይሆን ዳግም ከዚህ ምላስና ዕሳቤ አራማጆች ” አንድ ነን” የሚል የክተት ጥሪ የምናስተናግደው? ማን የምትባል አገር አስቀምጠን ነው እንዲህ በአገራችን ልንቀልድ የወሰንነው? ምን ነክቶን ሴራና ትግል መለየት ተስኖን ኪሳችንን ገልብተን በላየ ሰቦችን የምንደግፈው? ዛሬ ኢትዮጵያ የተሰራችበትን ህገመንግስት የሚባል በላ በጥበብ አሽቀንጥረን ስለምንጥልበት አጋባብ ከመምከር ይልቅ ቡድን ለይተን የአገሪቱን ሆድ እቃ የምንዘነጣጥለው ምን ለማግኘት ነው? የማንንስ አጀንዳ ለማስፈጸም ነው? ጉድ ያሰኛል….
አዋቂዎቹና ፖለቲከኞቹ የራሳቸው ጉዳይ ቢባል፣ ሕጻናቱ ምን አደረጉ? ምንም የማያውቁ ህጻናትን አገር አልባ ማድረግ ምን የሚሉት ጀግንነት ነው? ህግና መንግስት ሳይፈርስ ሌበነቱ፣ እገታው፣ ማጅራት መቺነቱ ሙያ፣ ሰፈር፣ ዝና፣ ዕድሜ፣ ጾታ፣ የንብረት ዓይነት ፣ ወዘተ ሳይመርጥ በምን ያህል ደረጃ ህዝቡን በቁሙ እየገደለው እንደሆነ እያየን ነው። ” ይፍረስ” የሚባለው መከላከያ ባይኖር ምን ሊኮን ነው? ግራ ያጋባል። ሰዎች እንዴት ፈልገውና መርተው በአገራቸው ይቀልዳሉ። ደግነቱ እጅግ ጥቂቶቹ ናቸውና አይሆንም።
አሚኮ ላይ የቀረበው ይህ አስተያየት መነሻውን ያጠነክራልና ያንብቡት።
ምን ያህል ተዘጋጅተናል?
የጥንታዊው እና መካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ማጣቃሻ የሚታሰሰው ሀገሪቷን ከጎበኙ የፖርቱጋል፣ የየመን፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ እና የመሳሰሉት አሳሾች የጉዞ ማስታዎሻ መካከል ነው፡፡ እናም ሁሉም በሚባል መልኩ የሚነግሩን የኢትዮጵያ ታሪክ ቢኖር በጦርነት፣ በግጭት እና በምስቅልቅል ውስጥ ስለማለፏ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ሥልጣኔዋ መዳከም ማግስት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ጦር መማዘዝ ተለምዷል፡፡
በእርግጥስ ከጥንታዊዉ እስከ ዘመናዊው የኢትዮጵያ የሥነ-መንግሥት አሥተዳደር ታሪክ ውስጥ ከአጼ ገብረመስቀል በቀር የመሪነት ዘመኑን በሰላም ጀምሮ በሰላም የቋጨ ማን ይኖራል? ሙሉ በሙሉ ዜጎቿ አማኞች ናቸው በሚባልላት ኢትዮጵያ ውስጥ መንፈሳዊነት የሚመስጣቸውን ያክል ጦረኞች ስለመኾናቸውም አብዝቶ ይነገራል፡፡ የሀገርን ሉዓላዊነት ላለማስደፈር ከውጭ ጠላት እና ወራሪ ጋር የሚደረገው ተጋድሎ እንደተጠበቀ ኾኖ እርስ በእርሳቸው የሚፈጥሩት ግጭት ሀገሪቷን ለጉስቁልና ሕዝቦቿን ለድህነት ዳርጓቸው ኖሯል፡፡
እንደ እውነቱ ከኾነ ሀገራዊ ትርክታችን ዛሬም ድረስ ከአምራችነት ይልቅ ሽፍትነትን የሚያጀግን ይመስለኛል፡፡ ስያሜ፣ ምሥጋና፣ ምኞት፣ ቀረርቶ፣ ፉከራ፣ ለቅሶ እና መሰል ማኅበራዊ መሥተጋብሮቻችን በአብዛኛው ጀብደኝነት ይጠናዎታቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለዘመናት የተሻሩ ችግሮችን በንግግር መፍታት እንደ ፍርሃት እንደተቆጠረ አስተውላለሁ፡፡ ተነጋግሮ ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ወደ እልህ እና ቁርቁስ ውስጥ ዘው ብሎ መግባት የሀገሪቷ መገለጫ ነበር፤ ነውም፡፡ የቀደመው የሀገሪቷ የውስጥ ሰላም ማጣት ችግር በትምህርት፣ ሥልጣኔ እና ዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር ውስጥ ፍጻሜ ያገኛል ቢባልም የተሻለ ሳይኾን የከፋ ኾኖ ብቅ አለ፡፡
ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የመጎሳቆሏ ምክንያት የማንሰራራቷ ተምሳሌት፤ የቅራኔዋ ዋና ምንጮች የመዳኗ መፍትሔ አምጭዎች በተለምዶ ልሂቅ እየተባለ የሚጠራው የተማረው የማኅበረሰብ ክፍል ኾነ፡፡ ለዘመናት “የተማረ ይግደለኝ” ሲል የኖረው መከረኛው አርሶ አደር እንደ ቃሉ ኾኖለት የሀገሩ መጻዒ እጣ ፋንታ እንዳለውም ከተማረው የማኅበረሰብ ክፍል መዳፍ ውስጥ ወደቀ፡፡
አሁን ላይ ተጸጽቶ መካስ እና አገናዝቦ መመለስ ወይም ልክ እንደ ትናንቱ በስሜት መነዳት እና እርስ በእርስ መጎዳዳት ምርጫው ያለው በልሂቃኑ ልብም፤ አዕምሮም ውስጥ ነው፡፡
ጦሩን ወደ ሰገባው መልሶ ለንግግር እና ለምክክር መቀመጥ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ በታላላቆቹ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄዎች እና ልዩነቶች ላይ ሕዝባዊ ውይይቶች እና ምክክሮች አሁኑኑ መጀመር አለባቸው ሲባል ከሰማን ሰነባብተናል፡፡
ይህንን የሕዝብ ጥያቄ መሠረት አድርጎም ገለልተኛ የኾነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ ትናንት በሀገሪቷ ሕገ መንግሥት ላይ የነበረው የአሳታፊነት ችግር ዛሬም በሀገራዊ ምክክራችን ላይ እንከን እንዳይፈጥር ምን ያክል ተዘጋጅተናል? ምክክራችንስ መሠረቱ ምን መኾን ይኖርበታል? ስክነት ወይስ ስሜት? ዕውቀት ወይስ ግትርነት? ቅንነት ወይስ ልግመኝነት? ምርጫው አሁንም በልሂቁ ትክሻ ላይ ወድቋል፡፡ በየትኛውም መንገድ መመካከር ግን ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ቆመናል፡፡
የኢዲሲቷ ኢትዮጵያ መሠረት ሲጣል የማዕዘን ድንጋዮቹ ፍትሕ፣ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና እኩልነት መኾን ይኖርባቸዋል ሲሉ የሚሞግቱት በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መሠረቶች የሚመጡት ደግሞ በምክክር ነው፡፡ ግጭቱንማ ኖረንበት አየነው! ከመፍረስ ውጪ የገነባው ሰላም ያጸናው ሀገራዊ አንድነት ተፈልጎ አይገኝም፡፡ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ውስጥ ደግሞ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጫወተው የየራሱ ድርሻ ቢኖረውም የምሁሩ ኢትዮጵያዊ ድርሻ በዓይነቱም ኾነ በመጠኑ እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡
ያለፈውን ግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ሥነ መንግሥት ታሪክ በጥሞና የተከታተለ ኢትዮጵያዊ የግዛት አንድነቷን እና የፖለቲካ ነጻነቷን በአንጻሩ ጠብቃ የኖረች ሀገር፤ ከአሁን በኋላ በዜጎቿ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሃቀኛ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስርታ ሁሉንም ዜጎቿን በእኩልነት ማቀፍ ካልቻለች እንደ ሀገር በጋራ የመቀጠል እጣ ፋንታዋ የመነመነ መኾኑ ይገለጥለታል፡፡
ነገር ግን ከሀገሪቷ መጻዒ እጣ ፋንታ በላይ ደግሞ የሚያስፈራው የሀገራቸውን ሉዓላዊ አንድነት ከራሳቸው ሕይወት በላይ የሚወድዱ፤ ነገር ግን የሚወዷት ሀገራቸው ሉዓላዊ አንድነት ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መምጣቱን እየተመለከቱ እጅ እና እግራቸውን አንደበት እና ብእራቸውን አጣጥፈው የተቀመጡት ልሂቃን ልግመት እና ፍርሃት ዝምታ እና ቸልታ በእጅጉ ያስፈራል፡፡
የሩቁን እና ጥንታዊውን የሀገሪቷን ታሪክ ትተን፤ ትናንት እንደ ዋዛ አይተው እንዳላዩ “የት ይደርሳሉ?” ብለው የናቋቸው የሀገሪቷ ችግሮች ዛሬ ላይ ሥር ሰድደው እና አድገው “እኛ እና እነርሱ” አሰኝተው እያተራመሱን እና እየጎዱን መመልከት ምን ያክል ጸጸት ውስጥ እንደሚከት መመልከት የሚከብድ አይመስልም፡፡ ይህ በምክክር ካልኾነ በሌላ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ እንደማይችል ከማንም በላይ ልሂቁ ያውቃል፡፡
ለልሂቁ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያን መውደድ ችግሮቿን ነቅሶ እና አብጠርጥሮ ከማወቅም ባሻገር ለሚያውቋቸው ችግሮች በዕውቀት እና በቅንነት፤ በምክክር እና በንግግር የተቃኘ ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ወቅቱ የሚጠይቀው አርበኝነት ነው፡፡ እናስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት የሚገዳደሩ የውስጥ ልዩነቶችን በምክክር እና በንግግር ለመፍታት፤ የሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ቅራኔ ለማከም፣ ልዩነት ለማጥበብ እና የታፈረች እና የተከበረች ኢትዮጵያ ለማጽናት ምን ያክል ተዘጋጅተናል?
በታዘብ አራጋው አሚኮ

ዕርዳታ – ኢትዮጵያ ጊዜ እየተጠበቀ የምትደቆስበት የስንዴ ፖለቲካ
ዓላማው በሰብአዊ እርዳታ ስም ሰላዮች መንግስትን ለማፍረስ፣ ያሻቸውን ተላላኪ ለማንገስ፣ ለበለጸጉ ማዕድናት ዝርፊያና ወዘተ ስለሚጠቀሙበት ችጋርን ያበረታቱታል