የሚነሳው ጉዳዩ ልብ ሰባሪ ነው፣ ያስቃል፣ ያዝናናል፣ ያስገርማል፣ ያሳዝናል፣ ይቀፋል፣ ያሳፍራል፣ ለማመን ያስቸግራል … አንባቢ ስም ይስጠው። እኔ ስጽፈው ግን በሃፍረት ስሜት ነው። ያፈርኩት ደግሞ በደርስንበት የሞራል ውድቀት ነው። እንደ ማህበረሰብ ይሁን እንደ ቡድን በውል ባላውቅም ግን ወድቀናል። የወደቅንበት የሃፍረታችን ገደል ርቀቱ እንዲሁ በቀላሉ የሚወጣበትም አይመስልም። ሃፍረቴና ተስፋዬ በኩል ደረጃ እየተናነቁኝ ስለ አብሮ አደጎቼ ጻፍኩ።
በንጹሃን ደምና ህይወት፣ በህጻናት፣ በአዛውንቶችና ሴቶች መፈናቀል የሚነግዱ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዘመኑ ታጋዮች፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ሁለት ቦታ የሚጫወቱ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የነዚህ ሁሉ ሚስቶች፣ ልጆች፣ ወዳጆችና ስራቸውን የሚያውቁ ሁሉ በየትኛውም ጊዜ ከፍርድ እንደማያመልጡ የምናውቅ ዕናውቃለን። አማኞች ሁሉ የጽድቅ ፍርድ በእነዚህ መዓተኞች ላይ እንዲወጣባቸው ያለቅሳሉና ፍርድ ሊበየን ግድ ነው።
ከማንም በላይ ግን ከእንዲህ መሰል የዘመን ጉዶች ጋር ትዳር መስርታችሁ በንጹሃን ደምና ሞት በሚቆመር ቁማር ኑሯችሁን ያደላደላችሁ ወይኔ ለናንት። ወላድን ባዶ እያስቀሩ፣ በምሲክን ልጆች ደም ገንዘብ እየሰበሰቡ በሚሰጥዋችሁ ገንዘብ ልጆቻችሁን የምትቀልቡ፣ የምታዘንጡ፣ የምታቆላምጡ፣ ልደታቸውንና ውሏቸውን እያደመቃችሁ በማህበራዊ ገጾች ለምታጋሩ፣ ራሳችሁን በውድ ልብስና የከበሩ ጌጣጌጦች እያስዋባችሁ፣ ውድ መኪና እየነዳችሁ፣ ዘመናዊ መኖሪያ ገዝታችሁ ለምትምነሸነሹ ሚስቶችና ቤተሰቦች፣ ወዳጆች ይብላኝልኝ ለናንተ። በንጹሃን ደም ንግድ በተገኘው የእርም ሃብት ሃጢያትን ቀለብና ማስጌጫችሁ አድርጋችሁዋልና ፍርድ በናንተ ላይ ይወጣል። ፍርድ ይሆንባችኋል።
የምታስጨርሷቸው ህጻናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ጎላማሶች ወዘተ ደም በጓዳችሁ ይጮሃል። ማንም ሆነ ማን፣ በሁለት ቢላ የምትበሉም ሆነ ሌሎች፣ ፣ የትም ኑሩ የት ይህ የሃጢያታችሁ ተራራ ሊሸፈን አይችልም። ገላችኋል። አስገርድላችኋል። አፈናቅካችኋል። ዘርፋችኋል። አግታችኋል። አሳግታችኋል። ይህ ሁሉ ሲሆን የ”ነጻ አውጪ” ታቤላ ሰጥታችሁ ይህን ሁሉ ወንጀል ህጋዊ እንዲሆን ያደረጋችሁ ቅጥረኛ ሚዲያዎች፣ ነጋዴ ዩቲይበሮች፣ አክቲቪስቶች፣ ይህንኑ ተግባር በገንዘብና በጉልበት የምታግዙ ሁላችሁም ፍርድ ይወጣባችኋል። በምንም መልኩ ይሁን ሰው ከሚያየው በላይ የንጽሃንን ስቃይና እንባ የሚያየው ሃያሉ አምላክ ይፈርዳል። ይብላኝ ለሴረኞች።
ነዋሪነቴ ሻሸመኔ ነው። ስሜ ለጊዜው ይቆይልኝና ምስክርነቴን ብቻ ላቅርብ። ሰዓትና ቦታ ካለመግለጼ በስተቀር የጻፍኩት ትክክለኛ ምስክርነቴ ነው። በጆሮዬ የሰማሁት አንዳንዱንም ያየሁትን ነው። እኔ ከማቅርበው ምስክርነት ጋር ስለሚዛመድ አንድ ሰሞኑንን በቴሌቪሽን ተማርከው የገቡ የሸኔ አባላት ከተናገሩት ልጥቀስ።
“የተጠየቅነውን ለማምጣት ወደ ምንላክበት ቦታ እንሄዳለን። ሄደን አድርጉ የተባልነውን ካደረግን በሁዋላ ገንዘቡን ይዘን መጥተን ሰማኒያ ከመቶውን ለአዛዦች እንሰጣለን። ቀሪውን እንወሳዳለን። አለቆቻችን በየመኖሪያቸው ቤትና ንብረት ገዝተዋል። ሃብት ሰብስበዋል። ያሳደገንን ህዝብ ዘርፈናል…” ጨዋታው ንግድ ነው። ወደ ራሴ ምስክርነት ልመለስ
“ሰራ ሰራ አድርጌ ቶሎ እመለሳለሁ” ሲል የተናገረው ለአንድ ዓመት ተኩል ግድም ጫካ ከርሞ የተመለሰው ሚሊየነሩ የሸኔ የ”ነጻነት” ታጋይ ነው። ይህን ያለው ወደ ጫካ ሲገባ ስንብት ላይ ነበር። ይህ ሲል ሰምቻለሁ። አንዱን አነሳሁ እንጂ በርካቶች በተመሳሳይ የሚያደርጉት ነው። ሊሰሩና ሊመለሱ በቡድን አለቃ ሰይመው ይወጣሉ።
ውጭ ያሉት አፈ ቀላጤዎች መረጃ አልባውን ዲያስፖራ “ትግሉ ተጧጡፏል” እያሉ ሌትና ቀን ያልቡታል። “ሰራ ሰራ አድርገን…” የሚሉት ደግሞ ወገናቸውን በስሙ እየማሉ፣ ብሄሩን መለያቸው አድርገው፣ በስሙ አጀንዳ ፈጥረው ይዘርፉታል። ይገሉታል። በስሙ እየማሉ ንጽሃንን ያሰቃያሉ፣ ያግታሉ፣ ይገላሉ፣ ይሰውራሉ በጅምላ ያፈናቅላሉ … ብዙ ብዙ ያደርጋሉ። ቅምጥ “ጋዜጠኞች” ሽፋን ይሰጣሉ። የዴያስፖራ ጋጋኖዎች አውቀውም ሳያውቁ ያጨበጭቡላቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ክልል ገዳይና ተገዳዮች እኩል ጀግና ሆነው ሲወደሱ፣ እኩል ሃውልት ሲቆምላቸው የማይጠይቅ ዳያስፖራ በደምና ዝርፊያ የተጨማለቁትን እያደነቀ ይደግፋል።
ወደ ሻሸመኔ ምስክርነቴ ስመለስ ጎረምሶች ሰብሰብ ብለው ” ለስራ ” ብለው ከሰፈር መሰወር የተለመደ ነው። ” ትንሽ ሰራ ሰራ አድርገን ..” ብለው እንደተሰወሩ በጥቂት ጊዜ ” እገሌ መሬት ገዛ” ይባላል። መሬቱ ጫካ በገባው ሰው ወኪል ስም ተገዝቶ ቤት ይገነባል። የንግድ ተሽከርካሪ ይሸመታል። ንብረት ይገዛል። ብር ይያዛል።
አንድ ቀን መጠጥ እንደጉድ እየወረደ ፌሽታ ሆኗል። ፌሽታው “የእንኳን ደህና መጣህ ነው” ልጁ “ሰራ ሰራ አድርጌ መጣሁ” ብሎ ተሰውሮ የነበረው ነው። ባለኝ መረጃ አሁን ሚሊየነር ሆኗል። ወይም በንብረት ከያዘው ጋር ተዳምሮ በሚሊየን የሚቆጠር ሃብት አለው። በድል አድራጊነት ስሜት፣ በስኬት ምሳሌነት አቀባበል ተደርጎለት አልኮሉን እየተጋተ የሚገለፍጠው “ታጋይ” ስንት ገድሎ፣ ስንት አግቶ፣ ስንቱን ዘርፎና አፈናቅሎ እንደመጣ እጁ ላይ የሚጮኸው የንጹሃን ደም፣ እሱን ታጋይ አድርገው የሚጮሁለት የውጩ አገር አክቲቪስቶችና እነ መረጃ ቲቪ፣ እዛም እዚህም የሚፈለፈሉት የብሄር ዕጢ አናታቸው ላይ የበቀለባቸው ተላላኪዎችና በእርም ገንዘብ የሚሽቀረቀሩት ሚስቶቻቸው ብቻ ናቸው።
“ቤቴ መጡ። ባሌንና ወንድ ልጄን ወሰዱ። ሶስት ሚሊዮን ክፈይ አሉኝ። የተባልኩትን አደረኩ። ለወራት ባለቤቴንና ልጄን አልመለሱልኝም። ቆይተው ‘ ገድለናቸዋል’ ብለው አረዱኝ። ማን ይፍረደኝ። ፍርድ ወዴት ነው?” ስትል እንባ ይራጨችን የሻምቡ አካባቢዋ ጉዳተኛ ታወሰችኝ። እንዲህ ላሉት ነው የሚጮኸው። እንዲህ ላሉት ነው “ታጋይ” የሚባለው ታቤላ የሚሰጠው።
በአገራችን ብዙ ችግሮች አሉ። ትግልና መንግስትን ወጥረው የሚይዙ ፖለቲከኞችና መሪዎች ያስፈልጋሉ። ታግለው የሚያታግሉ ታጋዮች ያሹናል። ይህን ለአፍታ አልጠራጠርም። በተቃዋሚነት ዘመናቸውን ፈጅተው፣ የትግልና የተቃውሞ ስልታቸውን ሳይቀይሩ ባረጀ አመለካከታቸው ላይ ተችክለው ዘወትር ጥላቻና ቂም የሚዘሩ ፖለቲከኞች ሰልችተውናል።
ዓላማዬ ዘርን ተገን አድርገው፣ በብሄር “ነጻ አውጪ” ካባ ተከልለው፣ በህዝብ ጥያቄ ስም ታጅበው በመናበብ ዝርፊያ ላይ የተሰማሩትን ሞራል አልባዎች ለማንሳት ነው። ውድቀታቸው ልክ ስለሌለው ገለው፣ አግተውና አስገድደው ዘርፈው በሰበሰቡት የግፍ ሃብት ይኩራራሉ። ሲሄዱ ሽኝት፣ ሲመለሱ አቀባበል የሚያደርጉላቸው እዛና እዚህ የሚጫወቱት ሹማምንትን ጨምሮ ወዳጆቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ሚስቶቻቸው ወዘተ. በጠቅላላው ሞራላቸው ሊጠገን በማይችል ደረጃ እንክትክት ብሎ መውደቁን ማሰብ ይከብዳል።
በሻሸመኔ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በየአቅጣጫው መከረኛ ብሄርን የተነተራሰና ከላይ በዘረዘርኳቸው ሚዲያዎች የዘረፋ፣ የግድያ፣ የእገታ ምስክር ወረቀት የተሰጣቸው መንገድ ሲዘጉ፣ ተቋማት ሲያቃጥሉ፣ ማዳበሪያ ከአርሶ አደር ጉሮሮ ሲነጥቁ፣ እህል ሲዘርፉና ህዝብን ሲያሰቃዩ ሲያፈናቅሉ በ”ሰበር ዜና” መንግስትን ለማሳጣት የምትጮሁ፣ ለቀጠሯችሁ ወገኖች ዓላማ ስትሉ ጉዳዩ ለዓመጽ እያመቻችሁ የምታሰራጩ እስከመቼ በዚህ የረከሰ ጎዳና ትቀጥላላቹህ?
ሰሞኑን በገፍ እጃቸውን የሰጡ እንዳሉት ከሆነ ጨዋታው ዝርፊያና ዝርፊያ እንጂ ሌላ ዓላማ የለውም ብለዋል። በቀጣይም ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ልባቸው የተመለሱ ምስክርነት ይሰጣሉ።
ሰልጥን ብለን የፈጀውን ቢፈጅም በሰላማዊ መንገድ በመታገል መንግስትን ለመቀየር ከመትጋት ውጭ በዚህ መልኩ መቀጠል አገሪቱን ለዘራፊ አሳልፎ ከመስጠት ውጪ ሌላ ትርፍ የለውም። በሁዋላ በስፋት የሚሆነው አሁን ተጀመሮ ያየነው ነው። በሁዋላ ላይ የሚስፋፋው ዛሬ የተጀመረው ተስፋፍቶና ሃይ ባይ አጥቶ መኖርና አለመኖር ተመሳስለው ማየት ነው።
ምንም ይሁን ምን የዚህ ውጤት ተጠቃሚዎች አፍርሰውን በፍርስራሻችን ላይ ራሳቸውን ሊተክሉ ሲሰሩ የነበሩትና እነሱን የሚደግፉና የሚያስታጥቁት ብቻ ናቸው። ከዚህ ውጪ ሌሎች የምናተርፈው አጅ አጨብጭቦ በቁጭት ሃዘን ደረት መድቃት ብቻ ነው። ድሮ እንቁላል ሲሰራቅ ያልቀጣች እናት ተብሎ እንደተተረተው እንዳይሆን መጠንቀቁ ይበጃል። አምቡላንስ የሚዘርፍና የሚያቃጥል፣ ጤና ጣቢያ የሚዘርፍ፣ ትምህርት ቤት የሚዘርፍ፣ የሚያግቱና የሚገድሉ፣ ህዝብን በግልና በደፈና የሚያፈናቅሉ እያጀገንን ወዴት እንደምንሄድ ለመረዳት ብዙ ምርምር አያስፈልግምና እንንቃ!!
በሌላ እይታዬ ኢተያ አርሲ በሆነው ጉዳይ እመለሳለሁ።
አመንሲሳ ጉዲና ሻሸመኔ