የማንኮራፍት መዘዙ እንቅልፍ ማሳጣት ብቻ አይደለም። ማንኮራፋት ከሚያንኮራፉት ሰዎች ጎን በሚተኙ ሰዎች አካላዊ እና አእምሮ ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል። ትዳርንም ሊያፈርስ ይችላል።
“ስለ ባለቤቴ ማንኮራፋት ቀላል አድርጌ ከቤተሰብ እና ከጓደኞቼ ጋር እቀልዳለሁ። እውነታው ግን ውስጤ በእጅጉ ይረበሻል” በማለት የሲንጋፖር ዜጋ የሆነችው የ45 ዓመቷ ባለትዳር አሩኒካ ሴልቫም ትናገራለች።
ይህች ባለትዳር እና የልጆች እናት “ስለጉዳዩ ባለቤቴን ባናግረው ይከፋዋል ብዬ በመጨነቅ ለዓመታት በኃይል ከሚያንኮራፋው ባሌ ጎን ስተኛ ኖሪያለሁ” ትላለች።
የባለቤቷን ማንኮራፋት “ችዬው እኖራለሁ” ብላ ብታስብም በግንኙነታቸው እና በባለቤቷ የእንቅልፍ ጥራት ላይ ጫና መፍጠሩ ግን አልቀረም።
“ሌሊት ላይ በተደጋጋሚ መንቃት ጀመረ። ጥሩ እንቅልፍ ስለማያገኝ ጠዋት ላይ ስሜቱ ጥሩ አይደለም” ስትል ለቢቢሲ ተናገራለች።
በማንኮራፋቱ እንቅልፍ አጥቶ የሚያድረው እርሱ ብቻ አይደለም። እርሷም እንዲሁም በከፍተኛ ድምጽ በሚንኮራፋው ባለቤቷ ምክንያት እንቅልፍ ርቋታል። በእንቅልፍ እጦት ሥራዋን በሚጠበቅባት ደረጃ መከወን ተቸግራ እንደነበረ ጭምር ታስታውሳለች።
በብዙ ትዳር ውስጥ ማንኮራፋት ችግር ሆኖ ቢቀጥልም ብዙ ጊዜ ማንኮራፋት የሚያስከትለው ተጽእኖ በስፋት ሲነገር አይሰማም።
የጤና እና የግንኙነት ባለሙያዎች ማንኮራፋት በባል እና በሚስት ግንኙነት እና ጤና ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍ ያለ በመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት ይሻል ይላሉ።
ከፍተኛ ድምጽ ያለው ማንኮራፋት
ከፍተኛ ድምጽ ያለው ማንኮራፋት ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ ከሚባል የጤና ችግር ጋር ይያያዛል። በአንድ ግለሰብ ላይ ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ ተከሰቷል የሚባለው በተደጋጋሚ መተንፈስ እያቆመ በድጋሚ መተንፈስ ሲጀመር መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይህ የጤና ችግር የጉሮሮ ክፍል ግድግዳዎች እንዲፍታታ እና እንዲጠብ በማድረግ የተለመደ የመተንፈስ ሥርዓትን በማስተጓጎል የኦክስጅን እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል።
በዩናይትድ ኪንግድም የጀምስ ኩክ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የመተንፈሻ ሥርዓት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ራማሙርቲ ሳታያሙርቲ ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ የሚያስከትለው ጉዳት በጊዜ ሂደት እየተባባስ ሊሄድ ይችላል ይላሉ።
ሐኪሙ እንደሚሉት ይህ የጤና ችግር በሚያንኮራፋው እንዲሁም በትዳር አጋር የአካላዊ እና የአእምሮ ጤና ላይ አሉታዊ የጤና ችግር ያስከትላል።
የስሊፕ አፕኒያ መልክቶች ምንድን ናቸው?
መልክቶቹ ብዙ ጊዜ የሚታዩት በእንቅልፍ ወቅት ነው። ከመልክቶቹም መካከል በከፍተኛ ድምጽ ማንኮራፋት፣ መተንፈስ አቁሞ ዳግም መጀመር፣ በትንፋሽ መቆራረጥ ድንገት ከእንቅልፍ መንቃትም ይገኙበታል።
ቀን ላይ ደገፍ ራስ ምታት፣ የድካም ስሜት፣ ትኩረት ማጣት፣ የመርሳት ችግር፣ የስሜት መቀያየር፣ አናሳ የሆነ የወሲብ ፍላጎት ተጠቃሽ ናቸው።
በማንኮራፋት ምክንያት በድንገት በደም ውስጥ ያለ የኦክስጅን እጥረት የደም ግፊትን ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
አንዳንድ ጥናቶች ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ የልብ የሥራ ማቆም ዕድልን በ140 ፐርሰንት፣ በስትሮክ የመመታት ዕድልን 60 በመቶ እንዲሁም ለልብ ህመም የመጋለጥ ዕድልን 30 በመቶ ይጨምራል።
በትዳር ውስጥ ያሉ ጥንዶች በማንኮራፋት ምክንያት ክፍል ለይተው እስከመተኛት ሊደርሱ ይችላሉ።

በሲንጋፖር ነዋሪ የሆነችው እና 15 ዓመታትን በትዳር ውስጥ የቆየችው አሩኒካ ሴልቫም በባለቤቷ ማንኮራፋት እንቅልፍ በማጣቷ አልጋ ለይታ ሌላ ክፍል ውስጥ ለመተኛት መገደዷን ትናገራለች።
ሴልቫም ባለቤቷ የህክምና ድጋፍ እንዲያገኝ የጤና ባለሙያ ጋር እንዲሄድ ብትጎተጉተውም ባለቤቷ ፍቃደኛ ሳይሆን ቆይቶ ነበር።
“አባቱም እና አያቱ ያንኮራፉ ስለነበር ማንኮራፋት የተለየ ነገር እንዳልሆነ በማሰብ ባለሙያ የህክምና ባለሙያ ላለማማከር ብዙ አንገራግሮ ነበር” ትላለች።
ከዚህ በተጨማሪ በእስያ አገራት ማንኮራፋት ‘ከወንድነት’ ጋር ስለሚያያዝ የወንዶች በኃይል ማንኮራፍት እንደ ጤና ችግር አይወሰድም ትላለች።
እንደ የብሪታኒያ የማንኮራፋት እና ስሊፕ አፕኒያ ማኅበር ከሆነ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ በእንቅልፍ ወቅት የሚያኮራፉ 15 ሚሊዮን ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ በእነዚህ ሰዎች ማንኮራፋት ደግሞ ከ30 ሚሊዮን ያላነሱ ሰዎች ተጎጂ ናቸው።
በቅርቡ የተካሄዱ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ከሴቶች በላይ ብዙ ወንዶች ያንኮራፋሉ።
በአንድ አልጋ የተኙ የትኛውም ፆታ ቢያንኮራፋ መዘዙ ሁለቱንም የሚጎዳ ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም ጠበቃ የሆነችው ሪፓ ጉፕታ በማንኮራፋት ምክንያት የበርካታ ጥንዶች ትዳር ሲፈርስ መመልከቷን ትናገራለች።
“ማንኮራፋት ለትዳር መፍረስ ምክንያት እየሆነ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል” ትላልች የቤተሰብ ሕግ ጠበቃዋ ሪፓ።
“ቀላል የማይባሉ ደንበኞቼ ‘ለበርካታ ዓመታት በተለያየ ክፍል ውስጥ ስንተኛ ኖረናል፤ በጊዜ ሂደት ተራርቀናል’ በማለት ማንኮራፍት በትዳር ላያ ያመጣውን ተፅእኖ ይነግሩኛል” ትላለች።
ለማንኮራፋት መፍትሄው ምንድንነው?
ማንኮራፋትን ወይም ስሊፕ አፕኒያን ለማስቀረት ከሚረዱ አማራጮች መካከል አንዱ የሕይወት ዘዬ ለውጥ ማድረግ ነው።
ክብደት መቀነስ፣ ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ የአልኮል መጠን መቀነስ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለአንዳንድ ሰዎች ኮንቲኒየስ ፖዘቲቭ ኤየርዌይ ፕሬዠር የተባለ በእንቅልፍ ወቅት የሚደረግ ማሽን መጠቀም የግድ ሊሆን ይችላል።
ይህ ከማሽን ጋር የተያያዘ አፍ እና አፍንጫ የሚሸፍን ጭምብል በእንቅልፍ ወቅት ለመተንፈስ መቸገርን ያስቀራል።
የሳልቫ ባለቤትም የማንኮራፋት ችግሩን ለመቅረፍ በማሰብ የሰውነት ክብደቱን ለመቀነስ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል።
ከቢቢሲ አማርኛ የተሰወሰደ