ባንኩ የክፍያ ሰነድ ቀረበለት። ማጣሪያ ጥያቄ ለህብረቱ አቀረበ። ሃሰት ሆኖ ተገኘና ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ያዘ። ጉዳዩ ወደ ህግ አመራ። አሁን ምኑ ነው አፍሪካ ህብረትን ስጋት ላይ ጥሎት አካውንቱን ወደ ሌላ አገር እንዲወስድ ያስገደደው? ከሆነም ህብረቱ ይህን አቋሙን ለምን በይፋ ከማስታወቅ ይታቀባል? ነገሩ በዚህ ደረጃ አሳሳቢ ከሆነ ቢያንስ ሁለት መስመር መግለጫ እንዴት ማውጣት ተሳነው …. ብዙ መወያያ ጥያቄዎች እየተሰሙ ነው።
ግርማ ሃብቴ ሰለሞን ከአዳማ – ነጻ አስተያየት
የአፍሪካ ህብረትን ማዕከል አድርጎ ማክሰኞ ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. የተሰማው ዜና የተለያዩ ሚዲያዎች እንደ አረዳዳቸው ቢዘግቡትም ሪፖርተር በአማርኛና በእንግሊዘኛ ያስነበበው ሁለት መልክ ያለው ዜና ምራቃቸውን ዋጥ ባደረጉ ዜጎች ዘንድ መነጋገሪያነቱ ከሌብነቱ በላይ ገኗል ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ልክ የዕርቅ ኮሚሽኑ በተቋቋመበት ዕለት ” … ስልጣኔን እለቃለሁ አለ” ተብሎ በዚሁ ሚዲያ እንደተዘገበው ማለቴ ነው። ዜናው ደግሞ የተወሰደው ከፓርላማ ፌስ ቡክ ላይ ነበር።
ቀሲስ በላይ መኮንን ” አታለውኝ ነው” ሲሉ የገለጹትና በማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው መስቀል እንደተሸከሙ እስር ቤት የወረዱበት ዜና ሪፖርተር በእንግሊዘኛ ዕትሙ አፍሪካ ህብረት የውጭ ምንዛሬ አካውንቱን በስጋት ወደ ሌላ አገር ለማዘዋወር እንደሚያስገድደው ወይም እንዳሰበ ገልጾ መዘገቡ ነበር ጉዳዩን ከቅሽም የሌብነት ሙከራው በላይ ጉዳዩን ያጋመው። ለሚገባቸው ማለቴ ነው።
ስማቸው እንዳይገለጽ የተፈለገውና ” የአፍሪካ ህብረት ምንጭ” በሚል ህብረቱ መረጃ የሚሰጠው እስር ፈርቶ፣ ዱላ ፈርቶ፣ ወይስ የመንግስትን ግልምጫ? አፍሪካ ህብረት በነሳነት ” ስጋት ገባኝ” የማይልበት ጉዳይ ምን ይህን? የህብረቱ የፋይናንስ አስተዳደ በገሃድ ስለ ጉዳዩ ካብራሩ በሁዋላ፣ ምን ነክቷቸው ” ምንጭ” እንዲሆኑ ጠየቁ? ወይስ የሳቸው ስልክ ሲዘጋ ፋይናንስን የሚመለከት ሌላ የፋይናስ ክፍል ሃላፊ “ስሜን ደብቁ” ብለው ይህን አሉ? አይነፋም!! ባራድኛው አድክም ነው።
እትብቱን አዲስ አበባ የቀበረው የአፍሪቃ ህብረት ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀሲስ በላይ መኮንን ቅጥር ግቢው ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ነገሩ ሲነቃ ከተሰወሩ ግለሰቦች ጋር ተገኝተው በሃሰተኛ ሰነድ 6.5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መጠየቃቸው “እንዴት የአፍሪካ ህብረትን ስጋት ውስጥ ጣለው?” የሚሉ ወገኖች፣ ዛሬም ድረስ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጣቸው አላገኙም። በተለይም ከማጭበርበሩ ተራነት፣ የግል የውጭ ምንዛሬ አካውንት ሳይኖራቸው የውጭ ምንዛሬ እንዲከፈላቸው ተደርጎ የቀርበበት አግባብ ሲታይ ሙከራው አፍሪካ ህብረት ግቢ ውስጥ ከመሄዱ የዘለለ ፍሬ የለውም። ቀሲስም የሰጡት ጮርቃ ምክንያት እንዲሁ።
የንግድ ባንክ ገዢ አቶ አቤ ሳኖ፣ “ሰውየው አልገባውም” ሲሉ ወሬውን በሙያዊ ቋንቋ ሲያጣጥሉት ባንኩ በተጭበረበረ ሰነድ የተጠየቀው ዶላር እንዲከፍል እንዲከፍል የተሞከረበት አግባብ የማጭበርበሩ ቅንብር ተራ እንደሆነ ያሳያል። ይህ ለአፍሪካ ህብረት ስራ እንደተሰራ አድርጎ ክፍያ እንዲፈጸም የሚጠይቀው ሰነድ ለአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ ለተቀመጠ ገንዘብ እንዴት ስጋት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ማብራሪያ እንዲሰጡበት፣ ራሱ አፍሪካ ህብረትም በገሃድ የስጋቱን ልክ የሚያስረዳበት አግባብ ቢፈጠር ሲሉ እኔን ጨምሮ በርካቶች ይመኛሉ። አክለውም መንግስት የሚቀልባቸው ሚዲያዎችም እንዲህ ያለ አገር ላይ ያነጣጠር damage ሲሰራ የቻሉትን ያህል ሄደው ትክክለኛ መረጃ ለማቅረብ አለመሞከራቸውን ከነ ሃላፊዎቻቸው ጭምር ይወቅሳሉ።
በአደንቋሪ ቅሰቀሳ፣ የፌስቡክ የባለስልጣጣናትን እስትንፋስ እየተቀባበሉ የሚዘግቡ የመንግስት ሚዲያዎች የሆነውን ለመሸፋፈን ሳይሆን በትክክል መረጃ አጣቅሰው፣ አፍሪካ ህብረትን አንቀው ይዘው መረጃ የማይቀበሉበትና ጉዳዩን አጥርተው የማይሰሩበት ምክንያት በዚህ ዜና ብቻ ሳይሆን በበርካታ ጉዳዮች ላይ ዳተኛ መሆናቸው አሳዥኝ ነው።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን የሚባለውም ተቋም ስብሰባና ውይይት ላይ ከሚታዩት፣ አልፎ አልፎ ሪፖርት መሳይ መግለጫ እየተፈራረቁ ከሚሰጡት በዘለለ አገርና ህዝብ ላይ በሚነጣጠሩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ፈጥነው ሲረባረቡ አለመታየታቸው ” አይ የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት” ብሎ ከማዘን የዘለለ አማራጭ የሚያሳጣ ደረጃ ደርሷል። በአጭሩ የሞተ ተቋም ነው።
ዜናውን ለአገር ውስጥ የጾም፣ ለነጮቹ ደግሞ የፍስክ አድርጎ ያቀረበው ሪፖርተር ቀደም ሲል ይታወቅበት ከነበረው እጅግ ሃላፊነት የተሞላበት ዘገባ በዚህ ደረጃ አገርን የሚጎዳ ዜና ለነጮች ያሰራጨበት አግባብ ብዙዎችን አስገርሟል። ፍላጎቱስ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
የአፍሪካ ህብረትን ከኢትዮጵያ ለማስነሳት ጋዳፊ በገፉበት ወቅት ነብሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ ዜናዊ ሩቅ ሄደው የጋዳፊን ዘመቻ ያኮላሹበትን አግባብ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ልዩ ክብር በምስጠት፣ አስቀድሞ ደሞ የመለስ ዘመቻ እዲሳካ ግብዓት በመስጠት ሪፖርተር የሰራው ስራ በታሪክ የማረሳ ነው። ባድመ ለኢትዮጵያ እንደተወሰነ ተደርጎ የሃሰት ዜና ሲሰራጭ ሪፖርተር ሃላፊነት ወስዶ ጉዳዩን ያጋለጥበት ታሪኩም አብሪ ታሪኩ ነው። ለአልጀርሱ ስምምነት መንግስት ይዞት የነበረው መከራከሪያ እንደማይጠቅም አማርጭ እያሳየ፣ ብቁ ባለሙያዎችን እያቀረበ መንግስትን ሲያስጠነቀቅ የነበርበትን ጊዜ ለሚያስቡ አሁን ላይ ” ምንነው ሪፖርተር አገርና መንግስት ተቀላቀሉበት?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ አግባብ የሚሆን ይመስለኛል።
“የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ኃላፊዎችም የተጠቀሰውን የክፍያ ሰነድ እንደማያውቁትና ኅብረቱም የተባለውን የክፍያ ትዕዛዝ እንዳልሰጠ ማሳወቃቸውን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል። ይህንንም ተከትሎ የክፍያ ሰነዱን ይዘው ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማዘዋወር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ በአካል የተገኙት ቀሲስ በላይ፣ የኅብረቱ የፀጥታ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ካዋሉዋቸው በኋላ ለፌዴራል ፖሊስ አስረክበዋቸዋል” ሲል በአማርኛ የዘገበው ሪፖርተር በእንግሊዝኛው ያተመው የፍስኩ ዜና ያስገረመኝ ለዚህ ነው።
የአፍሪካ ህብረት ለተሰራለት የፈጠራ ፕሮጀክትና ለማሽነሪ ክፍያ ወደ አራት አካላት የውጭ ምንዛሬ ከአካውንት ለሌላቸው ሰዎች የተጠቀሰው ብር መጠን ተከፋፍሎ እንዲገባላቸው የሚጠይቀውን የተጭበርበረ ሰንድ እንደማያውቀው ጠቅሶ ምላሽ ሰጥቷል። ባንኩም ለማጣራት ህብረቱን ጠይቆ ክፍያውን ማገድ ብቻ ሳይሆን የራሱን እርምጃ ወስዷል።
ባንኩ የክፍያ ሰነድ ቀረበለት። ማጣሪያ ጥያቄ ለህብረቱ አቀረበ። ሃሰት ሆኖ ተገኘና ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ያዘ። ጉዳዩ ወደ ህግ አመራ። አሁን ምኑ ነው አፍሪካ ህብረትን ስጋት ላይ ጥሎት አካውንቱን ወደ ሌላ አገር እንዲወስድ ያስገደደው? ከሆነም ህብረቱ ይህን አቋሙን ለምን በይፋ ከማስታወቅ ይታቀባል? ነገሩ በዚህ ደረጃ አሳሳቢ ከሆነ ቢያንስ ሁለት መስመር መግለጫ እንዴት ማውጣት ተሳነው …. ብዙ መወያያ ጥያቄዎች እየተሰሙ ነው።

Madalisto Muuso Lowole, head of the Financial Management division at the AU Commission, ሙሶ ሎዎል የሚባሉት የህብረቱ የፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ጉዳዩ እንደተሰማ ወዲያውኑ ለፖሊስ ደብዳቤ መጻፋቸውን ጨምሮ ማጭበርበሩ እንዴት ሊፈጸም እንደነበር፣ ገንዘቡ እንዲዛወርላቸው የተጠየቀላቸው የሰዎቹን ስምና ገንዘቡ የተተይቀበትን የአየር በአየር ፕሮጀክት ዘርዝረው ለሪፖርተር የሰጡት መረጃ ሌብነቱ እንዴት እንደታቀደ የሚያስረዳ በመሆኑ የሪፕርተር ዘገባ እዚህ ላይ ሙሉ መሆኑንን መመስከር ግድ ነው።
ከዚህ ዜና ግርጌ ሙሶ ሎዎልን ይተዋቸውና ” የአፍሪካ ህብረት የሪፖርተር ምንጮች” ብሎ ስም ሳይጠቅስ ህብረቱ ዕምነት ማጣቱን፣ ይህ ዓይነት የማጭበርበር ሙከራ ለሶስተኛ ጊዜ መደረጉን። ማጭበረበሩ የተሞከረው በሚከበሩ ሰው መሆኑንና ነገም በተመሳሳይ ስላለመሞከሩ ዋስትና ስለሌለ መጠነኛ የደሞዝ ገንዘብ በማስቀረት ሌላውን የህብረቱን የውጭ ምንዛሬ ወደ ሌላ አገር ለማዘዋወር ማሰባቸውን… በእንግሊዘኛው ዜና “የፍስክ” አድርጎ አቅርቧል። ” Sources at the AU told The Reporter that the organization’s financial officers are considering keeping its forex outside of Ethiopia. “This is the third time our accounts have faced fraud. We are worried because the fraud is now being attempted by respected people. We have no guarantee that officials won’t do the same one day. We are losing trust so we’ve decided to hold only a small amount of forex in Ethiopia for salaries. It’s forcing us to consider keeping the organization’s money abroad,” said an AU official who spoke on condition of anonymity.
ዜናው እንደተሰማ ማህበራዊ ሚዲያዎች ቀድመው በወሬ ደረጃ ቢሆንም አግመውታል። ከተማኝ ምንጭ ሰማን” በሚል የዘገቡ ሚዲያዎች ዜናውን ዜና ያደረጉት ማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃውን ከወቀጡት በሁዋላ ነው።
እንደ ዜና ጉዳዩ ትልቅ ነው። ዜናውን ከስሩ መርመሮ፣ የሚመለከታቸውን ጠይቆ ማቅረብ አግባብ ይሆናል። አንዴ ብቻ ሳዮን በተከታታይ ሂደቱን ተከታትሎ ማሳወቅም ይገባል። ነገር ግን አፍሪካ ህብረት በአንድ ተራና ለማጭበርበር የሚያደርስ ስልት ያልታከለበትን ያለ አዋቂዎች የዘረፋ ሙከራ ኢትዮጵያና አፍሪካ ህብረትን ለመለየት በሚያደርስ ደረጃ ሰማይ አድርሶ ማራባት “አንድ አገሬ ኢትዮጵያ ናት” ከሚል ሚዲያም ሆነ ዜጋ አይጠበቅም።
መንግስትን፣ ፓርቲን፣ መሪዎችን፣ ብሄራቸውን ወይም አመለካከታቸውን መጥላት ግላዊ ወይም ድርጅታዊ መብት ነው። ይህን መብት ግን 120 ሚልዮን ህዝብን በሚጎዳ ጉዳይ ማጣፋት በየትኛውም መስፈርት አጋብብ ነው ብዬ አላምንም።
ቀሲስ በላይ መስቀል ተሸክመው አፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ከሚገኘው ንግድ ባንክ የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲጠይቁ የተደርገበት መንገድና እሳቸው ፍርድ ቤት የሰጡትን ምላሽ የሰሙ ጉዳዩን ” ኮሞዲ” እያሉ እያላገጡበት ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ከሃይማኖት “አባትነታቸው” የህግ ባለሙያ መሆናቸውን ለሚያውቁ ” እኔ ወንጀሉ ላይ የለሁበትም፣ አታለውኝ ነው” ማለታቸው የኮሜዲው ምርጥ የተውኔቱ ክፍል እንደሆነ እነዚሁ የሚዝናኑባቸው ወገኖች ሲገልጹ እየሰማሁ ነው።
ጉዳዩ በህግ የተያዘ በመሆኑ ብዙ ማለት ባይቻልም፣ በሆነ አንድ ውል ቀሲስ በላይን እየነዱ ባንኩ ደጅ አድርሰው ሲነቃ ሞተራቸውን ተረክ አድርገው የተሸበለሉት ወገኖች ” እነማን ይሆኑ?” የሚለው ጉዳይ የቀሲሱን የተውኔቱ የአክተርነት ደረጃ ከመቀየሩ ውጭ አዲስ ነገር ያመጣል የሚል ግምት የለኝም።
ነገር ግን ከብሄር ፖለቲካና ነውጥ ያለወጣችው ኢትዮጵያ ከቅረብ ሳምንታት ጀምሮ አየር መንገዷን፣ ባንኳን፣ መብራት ሃይሏን ወዘተ ታላላቅ ተቋማቶቿን የሚዞራቸው ሴራ ግን ዜጎች ቆም ብለው ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል።
የጫካው መንገድ ሲያደክም የሃይማኖት፣ የሃይማኖቱ ሰሚ ሲያጣና የታሰበውን ያህል ሳይሆን ሲቀር ወደ ተቋሟቷ ጊዜ እየለየ ዘመቻ የሚፋፋምባት ኢትዮጵያ አሁን ላይ መንግስትንና አገርን ለይተው፣ ፓርቲንና ህዝብን ነጣጥለው የሚያዩ አስተዋዮችን ትሻለች። የኢትዮጵያ የፕሬስ ካውንስልም ሆነ ራሳቸው ፕሬሶች በከባድ ሃላፊነትና ጥንቃቄ መረጃዎችን ማሰራጨት እንዳለባቸው ሊረዱ ይገባል። አያቶቻችን እንደሚሉት “ውሃ ሲወስድ እያሳሰቀ ነው”