ታይታኒክ የተገነባችው ሰሜን አይርላንድ ውስጥ “White Star Line” በተባለ ካምፓኒ ነው፡፡ ታይታኒክ 269 ሜትር ርዝመት፣ 28 ሜትር ስፋት፣ 32 ሜትር ቁመት እንዲሁም ከ47 ሚሊዮን ኪ.ግ በላይ ክብደት ነበራት፡፡
ታይታኒክ የተሰራችው በ7.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ እ.አ.አ በ1997 ለእይታ የበቃው የጀምስ ካሜሮን ፊልም ታይታኒክ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡ ታይታኒክ በቀን 600 ሺህ ኪ.ግ ከሰል ትጠቀም ነበር፡፡

ታይታኒክ ከእንግሊዝ ሳውዝ ሀምፕተን ከተማ ወደ ኒውዮርክ ጉዞ የጀመረችው እ.አ.አ ሚያዚያ 10 ቀን 1912 ነው፡፡
መርከቧ ለ4 ቀናት የተሳካ ጉዞ ካደረገች በኃላ 30 ሜትር ቁመት ካለው የበረዶ ግግር ጋር የተላተመችው ሚያዚያ 14 ቀን 1912 ከሌሊቱ 5 ሰዓት ከ40 አካባቢ ነው፡፡ መርከቧ ሙሉ በሙሉ ለመስጠም 2 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ፈጅቶባታል፡፡
በአደጋው ወቅት ከ2 ሺህ 200 በላይ ሰዎች መርከቧ ውስጥ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በህይወት የተረፉት 706 ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
ታይታኒክ ውስጥ 20 ህይወት አድን ጀልባዎች ነበሩ፡፡ ጀልባዎቹ እያንዳንዳቸው እስከ 64 ሰው የመያዝ አቅም ቢኖራቸውም መርከቧ ውስጥ በተፈጠረው ትርምስ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነበር እየያዙ የወረዱት፡፡
በታይታኒክ አደጋ የሞቱት አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው፡፡ ይህም የሆነው ወደ ማምለጫ ጀልባዎች እንዲገቡ ቅድሚያ ለሴቶች እና ለህጻናት በመሰጠቱ ነው፡፡
ከሟቾች ውስጥ 26ቱ ጫጉላ ላይ የነበሩ ጥንዶች ናቸው፡፡
የታይታኒክ የሙዚቃ ባንድ አባላት መርከቧ እስክትሰጥም ድረስ ሙዚቃ መጫወት አላቆሙም ነበር፡፡
መርከቧ ውስጥ የነበሩ አንድ ቄስ ሁለት ጊዜ ወደ ህይወት አድን ጀልባዎች እንዲገቡ ተጠይቀው እሺ ሳይሉ ቀርተዋል፡፡ ቄሱ እስኪሰጥሙ ድረስ ከሞት ጋር የተፋጠጡ ክርስቲያኖችን ኑዛዜ (ንስሐ) ሲሰሙ እና ስርየት ሲለምኑ ነበር፡፡
የታይታኒክ ዋና ካፒቴን ኤድዋርድ ስሚዝ ለመርከቧ ሰራተኞች ያስተላለፉት የመጨረሻ መልዕክት እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “ወድ ሰራተኞች የሚጠበቅባችሁን ሁሉ አድርጋችሁል፡፡ ከዚህ በላይ እንድታደርጉ የምጠይቃችሁ ምንም ነገር የለም፡፡ የባህር ላይ ህግን ታውቃላችሁ፡፡ አሁን ሁሉም ሰው ለራሱ ነው፡፡ ፈጣሪ ይባርካችሁ”፡፡
ታይታኒክ ከባህር በታች በ3 ሺህ 840 ሜትር ጥልቀት ነው የሰጠመችው፡፡
ታይታኒክ ከመስጠሟ ከ14 ዓመታት በፊት በ1898 ሞርጋን ሮበርትሰን የተባለ እውቅ ደራሲ ‘ሊሰጥም የማይችለው መርከብ (unsinkable ship) ከበረዶ ግግር ጋር ተላትሞ ሰጠመ’ የሚል ጭብጥ ያለው መጽሐፍ ለንባብ አብቅቶ ነበር፡፡ ደራሲው በምናብ ለፈጠራት መርከብ የሰጣት መጠሪያም “ታይታን” የሚል ነበር፡፡
የታይታኒክ መርከብ ፍርስራሽ የተገኘው አደጋው ከደረሰ ከ73 ዓመታት በኋላ ዶ/ር ሮበርት ባላርድ በተባለ አሜሪካዊ የስነ ውቅያኖስ ተመራማሪ ነበር፡፡ ጊዜውም እ.አ.አ 1985 ነበር፡፡
የታይታኒክ ፊልም መሪ ተዋናይት ኬት ዊንስሌት “ማይ ኸርት ዊል ጎ ኦን” የተሰኘውን የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ እንደምትጠላው ተናግራ ነበር፡፡ ኬት “ሙዚቃውን ስሰማው ሊያስመልሰኝ ይደርሳል“ ነበር ያለችው፡፡
ታይታኒክ ፊልም በ11 ዘርፎች ኦስካር (አካዳሚ አዋርድ) አሸንፏል፡፡ ከሽልማቶቹ ውስጥ ግን አንዱም በተውኔት ዘርፍ የተገኘ አይደለም፡፡ የፊልሙ መሪ ተዋናዮች ኬት ዊንስሌት እና ሊዮናርዶ ዲ ካፔሪዮ በምርጥ ትወና አልተሸለሙም፡፡
በእዮብ መንግስቱ ETV