“ከግድያ ባሻገር የመስጅድ ሚናራ በመሳሪያ ተደብድቧል” ሲሉ የባህርዳር ከተማ ሙስሊሞች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ሀሩን ሚዲያ አመለከተ። በሰልፉ ” መገደላችን፣ መታፈናችንን፣ መዘረፋችንን፣ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል” የሚል መፈክር ጎልቶ ታይቷል።

በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ቀበሌ 14 ትላንት መጋቢት 29 የመግሪብ ሰላት ሰግደው ሲመለሱ የነበሩ አባት ከሶስት ልጆቹ እንዲሁም አንድ ጎረቢታቸውን ጨምሮ በድምሩ አምስት ሰዎችበድንገት በተከፈተባቸው የጥይት እሩምታ መገደላቸው ይፋ ሆኗል።
ግድያውን በአደባባይ የተፈጸመና ማስተባበያ ሊቀርበበት የሚችል ባይሆንም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የዕምነት ተቋማት፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ገለልተኛ ነን የሚሉ ሚዲያዎች ድርጊቱን በሚፈለገው ደረጃ አለማውገዛቸው ጥቃቱን በተቀበሉት ዘንዳ ክፉኛ ሃዘንን ፈጥሯል። “እንኳን በሚፈለገው ደረጃ መቃወም፣ ዜናውንም እንደዜና የዘገቡት ለቁጥር የማይመቹ ናቸው” ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰሙት አስታውቀዋል።
ይህን ተከትሎ በዛሬው ዕለት የባህርዳር ከተማ ሙስሊሞች በክልሉ በሚልኖሩ ህዝበ ሙስሊም ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እና እገታ መበርካቱን ተከትሎ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረርጋቸውና ሰልፉም በሰላም መከናወኑን ከስፍራው የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።
በባህርዳር ከተማ ከሶላት መልስ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ፣ አባይ ማዶ በሚገኘው መስጂድ ላይ ከፍተኛ የመሳሪያ ድብደባ እንደተፈፀመበት፣ ይህም ለዛሬው ሰለፍ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ የሃሩን ሚዲያ ዜና አመልክቷል።
ትላንት ምሽት “በግፍ ተገድለዋል” የተባሉት አቶ ሙሄ፣ ልጃቸው አበባዉ ሙሄ፣ሽኩር ሙሄ፣ሙላት ሙሄ እና ጎረቤታቸው አቶ እንድሪስ የተባሉት አምስት ሰዎች በዛሬው ዕለት ስርዓት ቀብራቸው ተፈፅሟል። ከአንድ ቤት አራት ሰው መሞቱ ሃዘኑን ከባድ፣ ቁጣውንም መራራ እንዳደረገው ተመልክቷል። በዚህ ምሬትና ቁጣ ላይ አባይ ማዶ የሚገኘው መስጊድ በመሳሪያ መደብደቡ ህዝቡን አስቆጥቷል።
ከባህርዳር በተጨማሪ በተለያዩ የክልሉ ከተሞችና አካባቢዎች መስሊሞች ላይ ያነጣጠሩ ግዲያ፣ አፈናና፣ ዘረፋ እንዲሁም ለይቶ የማስፈራራት ድርጊት እየተፈጸመ መሆኑ ሰልፈኞቹ ገልጸዋል። የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሔ ያበጅ ዘንድ ጠይቀዋል። መዘረፋቸን፣ መገደላቸውን፣ መታፈናቸውን ህዝብ እንዲያውቅላቸውም ድምሳቸውን አሰምተዋል።
ሰላም ወዳድ የባህር ዳር ነዋሪዎች ” ከወንድምና እህቶቻችን ጋር አታጣሉን” በሚል በሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን ኢትዮ12 ሰምታለች። በተደጋጋሚ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታወሱ ድርጊቱ አብሮነትን የሚንድና ዓላማው ፍጹም ልዩ መሆኑንን መረዳት እንደሚያስፈልግ እነዚሁ ወገኖች አመልክተዋል።
በአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ በሁለት ቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ በፈነዳ ቦምብ ሃያስ ሰባት ሰዎች መጎዳታቸውን ይታወሳል።
በከተማዋ በሚገኝ የገበያ ስፍራ ላይ ባጋጠመው በዚህ የቦምብ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ግብይት ላይ የነበሩ ንጹሃን መሆናቸው ተገልጿል።
ቢቢሲ አማርኛው እንዳለው ፍኖተ ሰላም ከተማ፤ የቦምብ ፍንዳታው ያገጠመው ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 28/2016 ዓ.ም ነው። ፍንዳታው የተፈጸመው የከተማዋ እና አጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች በየሳምንቱ ቅዳሜ በሚገበያዩበት ሳምንታዊ የገበያ ስፍራ ላይ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመንግሥት ኃላፊዎች “የቦምንብ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል” የሚል ስጋት መኖሩን በመጥቀስ ነዋሪዎች እንዳይሰበሰቡ ሲናገሩ እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪው፤ በዕለቱም የፀጥታ ኃይሎች በገበያ ስፍራው ላይ “ፓትሮል” እያደረጉ እንደነበር አስረድተዋል። ይሁንና የፀጥታ ኃይሎች ከስፍራው ከሄዱ በኋላ የቦንብ ፍንዳታው ማጋጠሙን ተናግረዋል። ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ “እንደማይታወቅ” ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ እስከታተመ ድረስ ለጥቃቱ ፊትለፊት ወጥቶ ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም። የባህር ዳሩን ግድያ ፈጻሚዎች ስለመያዛቸውም የተባለ ነገር የለም።