ሰሞኑንን ልዩ የደቦ ዘመቻ የተከፈተበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጎ እድሳት እና ማስፋፊያ ያደረገበትን የሀገር ውስጥ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ዛሬ አስመረቀ። ችግር የሚፈጥሩ ላይ እርምጃ እየወሰደ ስራውን አቀላጥፎ እንደሚቀጥልም አመልክቷል። ወደ ነቀምትና አክሱም በረራ እንደሚጀመር አስታውቋል።
አየር መንገዱ ካሉት ከ20 በላይ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች በቀን በአማካኝ ከ 200 በላይ በረራዎችን እንደሚያደርግ እና በዓመት 3.5 ሚሊዮን መንገደኞችን እንደሚያጓጉዝ ምረቃውን ተንተርሶ ተገልጿል።

ለረጅም ዓመታት ከፍተኛ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ መንገደኞች ማስተናገጃ ማእከል የተጓዦችን የፍላጎት እድገት መነሻ ተደርጎ የተሠራ የማዘመን ሥራ ነው ሲሉ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።
በቻይና የግንባታ ሥራ ድርጅት የተገነባው ይህ የእድሳት እና የማስፋፊያ ሥራ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሊኖር የሚችለውን የሀገር ውስጥ መንገደኞች ፍላጎት ታሳቢ ተደርጎ መሠራቱንም ስራ አስፈጻሚው ገልፀዋል።
“ይህ ዘመናዊ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በዓመት የሚያስተናግዳቸው መንገደኞች በእጥፍ እንዲያድግ ታሳቢ ተደርጎ የማስፋፊያ እና የእድሳት ሥራ የተደረገበት ነው”
የአገር ውስጥ በረራ መበራከቱንና ፍላጎቱ እያደገ የመጣበትን ምክንያት ፖለቲካዊ የሚያደርጉና ጉዳዩን ከጸጥታ ጋር የሚያያዙ ቢኖሩም አየር መንገዱ ” መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በከፍተኛ ደረጃ መጨመራቸው ፍላጎቱን አሳድጎታል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ይህን የሰሙና ነዋሪነታቸውን በስዊዲን ያደረጉ ኢኮኖሚስት ” ሁሉንም ጉዳይ በአንድ መነጽር አይቶ መደምደም ትክክል አይደለም” በማለት እሳቸው በሚኖሩበት አገርም ሆነ በድፍን አውሮፓ የአየር ትራንሶርት ልክ እንደታክሲ ህዝብ አዘውትሮ የሚጠቀመው እንደሆነ አመልክተዋል። የአየር ትራንስፖርት ድካምን፣ ሰዓትንና እንግልትን የሚቀንስ፣ ከዛም በላይ አስተማማኝነቱ ከሌሎች መጓጓዣዎች በላይ በመሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው ዓለም ሁሉ እንደሚያውቅ አስታውሰዋል።
“ታዲያ” አሉ እኙህ የስዊዲን ነዋሪ ” ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች አውሮፕላን ቢመርጡ ምን ይገርማል? ለደህነታቸው ሲሉ ቢመርጡት እንዴት ዜና ይሆናል? ” በሚል ይጠይቃሉ። አክለውም “አዎ ኢትዮጵያ ውስጥ አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግር አለ። ከሁሉም በላይ መንገድ እየዘጉ የሚዘርፉ ታጣቂዎች አሉ። ይህ ግን በራሱ ለአየር ትራንስፖርትብ ፍላጎት እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስና ዋናውን እውነት ሊሸፍን አይችልም” ብለዋል።
ተቋርጦ የነበረው የደንቢ ዶሎ በረራ መጀመሩን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በቅርቡ ወደ ነቀምት ከተማ አዲስ በረራ እንደሚጀመር ገልጸዋል። አየር መንገዱ በውስጡ ለሚፈፀሙ ብልሹ አሠራሮች “ምንም ቦታ እንደማይሰጥ” እና እርምጃዎችን መውሰዱን እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
በቀን በአማካኝ ከ 200 በላይ በረራዎችን በማድረግ አገልግሎት ይሰጣል የተባለውየኢትዮጵያ አየር መንገድበዓመት 3.5 ሚሊዮን መንገደኛ ይህንን የአየር መንገዱን አገልግሎት እየተጠቀሙ ስለመሆኑም ተገልጿል። ይሁንና የሀገር ውስጥ የበረራ ፍላጎቱ መጨመር ሀገሪቱ ከገጠማት የፀጥታ ችግር መነሻ የየብስ ትራንፖርት በተጋረጠበት ፈተና አውሮፕላን ምርጫ ውስጥ በመግባቱ ስለመሆኑ ይነገራል በሚል ዶቺቫሌ ላቀረበው ጥያቄ ፤በኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያደቻ “መካከለኛ ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው ያለው። የዚያ መጨመር የአገልግሎቱን ፍላጎት ያመጣ ነው ብየ አስባለሁ።” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያደረገው የሀገር ውስጥ ተጓዦች የማስፋፊያ ተርሚናል ግንባታ ለ22 ቱ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹ መንገደኞች የተሻለ ጥራት ያለው ግልጋሎት ለመስጠት ያስችላል፣ የጎብኝዎችንም እንቅስቃሴ ይደግፋል ተብሏል።
በተያያዘ ዜና ከመጪው ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ዳግም በረራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ገለጸ።
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ አቶ ለማ ያዴቻ፤ አየር መንገዱ ወደ አክሱም ዳግም በረራ ለመጀመር የሚያስችሉትን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በመሆኑም ከመጪው ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ወደሆነችው አክሱም ከተማ ዳግም በረራ እንደሚጀመር ገልጸዋል። በረራው መጀመሩ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው የሚያደርጉትን ጉዞ ለማሳለጥ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በረራው በሣምንት ሰባት ጊዜ የሚደረግ መሆኑንም መጠቆማቸውን፣ አየር መንገዱ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በረራውን በቀን ወደ 3 እንደሚያሳድግም ከሃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።