አቡነ ሉቃስ በተከሰሱበት የቅስቀሳ ወንጀል ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በሥድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ። ከፈጸሙት ወንጀል አኳያ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ እየተሰራ ነው።
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ሕገ-መንግሥታዊና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች የሚመለከተው ችሎት ነው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በአቡነ ሉቃስ ላይ ከሦስት ወራት በፊት÷ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 (ሐ) እና አንቀጽ 258 (ሀ) ሥር እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251 (ሐ) የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚሉ ሁለት ክሶች ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ተከሳሹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የምሥራቅ አውስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ በጠቅላይ ቤተክኅነት የገዳማት መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ-ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ ስለ ሰላም እና አንድነት የመስበክ ሐይማኖታዊ ግዴታቸውን በመተው ታኅሣስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ቴክሳስ እና አካባቢው በሚገኝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ-ክርስቲያን ታቦት ወጥቶ በቆመበት ዐውደ-ምኅረት ላይ የአመፅ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡
የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የተከሰሱባቸው ክሶች በአንቀጽ 247 (ሐ) ሥር ተጠቃልሎ የጥፋተኝነት ፍርድ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ካቀረባቸው ሦስት የቅጣት ማክበጃ አስተያየቶች መካከል ፍርድ ቤቱ አንዱን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት በመያዝ እና ተከሳሹም የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን መነሻ በማድረግ አንድ የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው ዛሬ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በእርከን 23 ሥር በሥድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በሌሉበት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እንደ ጎልያድ በማስመሰል በአንድ ምሳሌያዊ ዳዊት እንዲግደሉ የሃይማኖታዊ ግድያ ጥሪ ያስተላለፉት አቡን ሉቃስ የወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው። አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 እና 251 ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል ክስ እንደተከሰሱ ይታወሳል።፡
አቡን ሉቃስ ይህንን የግድያ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ የኦርቶዶክስ ቤተክስቲያን ጳጳሱን እንድታወግዝ ከተለያዩ አካላት ጥያቄ ቢቅርብላትም ሳትፈጽመው ቀርታለች። ይህም በርካታ በሚባሉ ምዕምናኖቿ ዘንድ ቅሬታን የፈጠረ መሆኑ በስፋት ይነገራል።
በወቅቱ ካለው የፖለቲካ ትኩሳት አኳያ በአደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ባያሰሙም ጥቂት የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች “ጠቅላይ ሚኒስትሩን የምንቃወም ብንሆንም በዚህ ልክ ግን ግድያ እንዲፈጸምባቸው በተለይ ከሃይማኖት አባት መስማታችን አሳፍሮናል” በማለት በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል።
“ጠላትህን ውደድ” የሚለውን የወንጌል ቃል ፍጹም በመጻረር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ግድያ እንዲፈጸም ሃይማኖታዊ ጥሪ ያስተላለፉትን አቡን ሉቃስ ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቡነ አብርሃም ከጥምቀት በዓል በፊት መልስ ሰጥተው ነበር። በአንድ በኩል ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ መታየት ነው ያለበት ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ልናወግዝና መግለጫ ልንሰጥ አስበን ነበር ግን የሚያስከትለውን መጠላለፍ ተመልክተን ትተነዋል ማለታቸው ይታወሳል።
በቅርቡ ፌደራል ፖሊስ በአሜሪካ የሚኖሩ ‘ተፈላጊዎች’ ተላልፈው እንዲሰጡ ትብብር እንዲደረግ ለአሜሪካው አምባሳደር መጠየቁ ቢቢሲ ዘግቧል። “የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት በማወክ እፈልጋቸዋለሁ” የምትላቸውን ሰዎች አሜሪካ አሳልፋ እንድትሰጥ ጥያቄውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ለሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሩ “በአሜሪካን አገር ተቀምጠው የሃገራችንን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ተፈላጊዎችን አሳልፎ በመስጠት” ከአሜሪካ በኩል ትብብር እንዲደረግ ለአምባሳደሩ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው አሜሪካ የምትፈልጋቸውን ወንጀለኞች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሳልፎ በመስጠት ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ተጠቅሷል።
አገራቸውም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተመሳሳይ ድጋፎችን እንድታደርግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መናገራቸው በዚሁ መግለጫ ላይ ሰፍሯል። ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ባይኖራቸውም፤ ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ትውልደ ኢትዮጵያዊውን እና በሁለት ሰዎች ግድያ አሜሪካ ስትፈልገውን የነበረውን ዮሃንስ ነሲቡ የተባለውን ግለሰብ አሳልፋ መስጠቷ ይታወሳል።
ክሱ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች መምሪያ መቅረቡና ወንጀሉም የዓመጽ ቅስቀሳ ማድረግ በሌላ አነጋገር ሽብር መንዛት የሚል በመሆኑ ጉዳዩን ዓለምአቀፋዊ ስለሚያደርገው ቅጣታቸውን ለመፈጸም አቡኑ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው ይሰጣሉ የሚለውን አጉልቶታል።
በአቡን ሉቃስ ደረጃ ያለ ሰው ተላልፎ መሰጠቱ ለሌሎችም ትልቅ ማስተማሪያ ከመሆኑ አኳያ መንግሥት በርት ቶ እንደሠራ የሚወተውቱም ጥቂቶች አይደሉም።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ