አሜሪካ ተቀምጠው የኢትዮጵያን ሰላም የሚያውኩ ተፈላጊዎችን ሀገሪቱ አሳልፋ በመስጠት ትብብር እንድታደርግ የፌደራል ፖሊስ መጠየቁ ተገለጸ። በጀርመን በተመሳሳይ ስራ መጀመሩ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚኖሩ “ተፈላጊዎች” ተላልፈው እንዲሰጧት ጠየቀች፤ ኤምባሲው ንግግር መደረጉን አስታውቋል
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ጥያቄውን ያቀረቡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን በቢሯቸው ባነጋገሩበት ወቅት መሆኑን ኮሚሽኑ በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል።
“የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአሜሪካው የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር አምባሳደሩ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ኮሚሽነር ጀነራል ጥሪ አቅርበዋል” ሲል የውይይቱን ይዘት ያመለከተው የኮሚሽኑ መረጃ ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም።
“በተለይ በአሜሪካ ተቀምጠው የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ተፈላጊዎችን አሳልፎ በመስጠት ዙሪያ ትብብር እንዲያደርጉም ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጠይቀዋል” ያለው የፌደራል ፖሊስ ዜና አምባሳደሩ ምላሻቸው ቀና መሆኑን አመልክቷል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው በአሜሪካን መንግሥት የሚፈለጉ ወንጀለኞችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሳልፎ በመስጠት ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና ካቀረቡ በሁዋላ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተመሳሳይ ድጋፎችን እንድታደርግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መናገራቸውንም የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያስረዳል።
ዜናው አምብሳደሩን ጠቅሶ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም ” ዜናው በዚህ ደረጃ ዝም ብሎ ሊነሳ አይችልም። አምባሳደሩም ከዚህ በላይ መናገር አይጠበቅባቸውም” በሚል ጉዳዩ ውሎ አድሮ ተከታታይ ዜናዎችን እንደሚያስከትል አስተያት የሰጡ አሉ። በተቃራኒ መንግስትን የወቀሱም አልታጡም።
የአሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደሩ ከኮሚሽነሩ ጋር መነጋገራቸውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ስለውይይቱ ዝርዝር ባያነሳም፣ በህዝብና ፍትህ አካላት ላይ ባለው የህግ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት መደረጉን አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀደም ሲል በጀርመን በተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦ ጉዳዩ በሂደት ላይ እንደሆነ የአዲስ አበባ ተባባሪያችንን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።