ጥናትና ምርምር ላይ መሠረት በማድረግ የሠራዊቱን የትጥቅ አቅም የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ጥናትና ምርምር ላይ መሠረት በማድረግ የሠራዊቱን የትጥቅ አቅም የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በሪቨርስ ኢንጂነሪንግ ዘዴ የተለያዩ መሳሪያዎችን፣ ሮኬቶችንና ታንኮችን ለማምረት እያደረገ ያለውን ሰፊ ሥራ ተመልክተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መከላከያ የሚፈልገውን ስትራቴጂክ ፍላጎት መሠረት በማድረግ የመከላከያ ኢንዱስትሪና የመከላከያ ሎጂስቲክስ ጥገና ማዕከል ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ተደርጓል።
በተለይም ለሠራዊቱ የሚያስፈልጉ ትጥቆች እንዲያመርቱና እንዲያሻሽሉ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሠራዊቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም የተቋማቱን የሥራ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ መመልከታቸውንና መመሪያ መስጠቱን ገልፀዋል። በመከላከያ የተካሄደውን ሪፎርም ተከትሎ ኢንዱስትሪውና የጥገና ማዕከሉ ማሻሻያ እንደተደረገባቸው አስታውሰዋል።
የመከላከያ ኢንዱስትሪ ቀደም ሲል ከሜቴክ ጋር እንደነበር አስታውሰው፤ ከለውጡ በኋላ ወደ መከላከያ እንዲመለስ መደረጉን አስረድተዋል።
ይሁንና ተቋሙ ከእነ ኪሳራው ወደ መከላከያ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በተካሄደው ሪፎርም የተቋሙ አስተዳደርና የአሠራር መመሪያው ተስተካክሎ እንዲሁም ምን ዓይነት ምርት ማምረት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጦለታል ብለዋል።
በዚህም ተቋሙ አሁን ላይ ቀደም ሲል ከነበረበት ከኪሳራ ወጥቶ ትርፋማ መሆን ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ነገሮችን እየፈጠረና እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አገሪቱ ሁሉንም ነገር ከውጭ እየገዛች መኖር አትችልም ያሉት ኢታማዦር ሹሙ፤ አገር ውስጥ ያለውን አቅም በመጠቀም መሸጥ የሚቻልበት ደረጃ መድረስ እንደሚቻል ታምኖ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።
የሎጂስቲክስ የጥገና ማዕከሉ ቀደም ሲል በጣም የተዳከመ እንደነበር ጠቅሰው፤ ተቋሙ ሪፎርሙን ተከትሎ በተደረገለት ማስተካከያ ወደ ትክክለኛ አቋሙ መመለሱንም ተናግረዋል።
በተለይም ባለሙያዎቹን በከፍተኛ ወኔና እልህ ወደ ሥራ በማስገባት የተበላሹና የወደቁ መሳሪያዎች ጥናትና ምርምር ተደርጎባቸው እንዲጠገኑና ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም ተሽከርካሪዎች በተለይም ብረት ለበሶች፣ ታንኮች እንዲሁም የመድፎች የሞቢሊቲ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ የሚያስችል ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል።
የማዕከሉ ሠራተኞች በዘርፉ እውቀት ያላቸው በመሆናቸው መመራመር፣ መፍጠርና ማሻሻል የሚችሉ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህም በርካታ የጦር መሳሪያዎች ወደ ሥራ ማስመለስ መቻላቸውን ገልፀው፤ በዚህም የሠራዊቱ የተኩስ፣ የታንክ፣ የብረት ለበስና የመድፍ አቅም አድጓል ብለዋል።
በቀጣይም ሌሎች ትጥቆችን ወደ ሥራ የማስገባቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ኢዜአ እንደዘገበዉ ዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች መሆኑን አንስተው፤ የመከላከያን የዲጂታል አቅም ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በዚህም የሠራዊቱን አቅም ለማጠናከርና ለመገንባት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የገለጹት።