በወንጀል የተገኘን ንብረት ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን የመከላከልና መቆጣጠር ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ላይ የተዘጋጀ የግብዐት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሄደ
በመድረኩ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ በሀገራችን ያለው የፋይናንስ ስርዐት ደህንነቱ የተጠበቀ እና አለማቀፋዊ ግዴታዎችን በሚያሟላ መልኩ በተቀረፀ ስርዐት መመራት የሚኖርበት በመሆኑ የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት አብራርተው ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዩን ጢሞቲዮስ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩም የመድረኩን ተሳታፊዎች አመስግነው በሚቀረበው ሰነድ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለረቂቁ መዳበር አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ በንግግራቸው አስታውሰዋል፡፡
በወንጀል የተገኘን ንብረት ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣን አዋጅ ለማሻሻል አለማቀፍ መለኪያዎችን እና ግዴታዎችን ማሟላት የሚገባው በመሆኑ እና ከዚህ በፊት በአዋጁ ትግበራ እና አተረጓጎም ግዜ የገጠሙ ችግሮችን በመቅረፍ ድንጋጌዎችን ግልፅ እና ለትርጉም በማያሻማ መልኩ መደንገግ በማስፈለጉ አዋጁን ለማሻሻል ምክንያቶች ሆነዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በተለያየ የመሰረታዊ እና ሥነ-ሥርዐታዊ ህጎች ተበታትነው ሲሰሩባቸው የነበሩ የሀብት ማስመለስ ህጎችን አንድ ወጥ ወደሆነ ስርዐት መሰብሰብ በማሰፈለጉ እና ለአሰራረም የህግ ክፍተት የነበረባቸውን ጉዳዮች በህግ መምራት በማስፈለጉ የንብረት ማስመለስ እና ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ይዞ መገኘትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ረቂቅ ህጎችም ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ባለድርሻ የመንግስት ተቋማት፣ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የህግ ምሁራን እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡