“ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና አሠራር ውጪ የሚወጡ መግለጫዎች ተገቢነት የላቸውም” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ሲል ባልተለመደ መልኩ አምባሳደሩን ተችቶ መግለጫ አወጣ። ኢትዮጵያ ራስዋን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባት ምክር ለመለገስ መሞከራቸውን አንስቶ ሊያስተካከሉ እንደሚገባ ጠይቋል።
የውጭ ጉዳይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም አመላካች በሆነው የፖሊሲ ንግግራቸው፣ ምንም እንኳን ለስላሳ፣ ለኢትዮጵያ በተቆርቋሪነት መንፈስ የተቃኘ የሚመስል ቢሆንም፣ ጠብ መንጃ ያነሱ ወገኖች ወደ ስለማ እንዲመጡ አበክሮ ያሳሰብ ቢሆንም መንግስ ተቃውሞውን ያሰማው “እንዴት ከዘራፊዎች፣ አጋቾች፣ ህዝብን ከሚያሰቃዩ ሽብርተኞች ጋር በንጽፅር እንቀርባለን” የሚል ነው። ከዚህም በላይ አምባሳደሩ ያለ በቂ ግንዛቤና ዝግጅት ከዓለም የዲፕሎማሲ ግንኙነት አሰራር ያፈነገጠ አካሄድ መከተላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮንኗል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሰጡትን መግለጫ አስመልክቶ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው።
ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር “ሰብዓዊ መብቶችን እና ምክክሮችን የሚመለከት የፖሊሲ ንግግር” በሚል ርዕስ ባስተላለፉት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ መሠረት የሌላቸው ክሶችን አሰምተዋል፡፡ አገራችንን በምን መልክ ማስተዳደር እንደሚሻለንም በራሳቸው ተነሳሽነት ምክር ለመለገስ ሞክረዋል፡፡ ከዚህም አልፈው በህዝብ የተመረጠውን መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚንቀሳቀሱ እና ሰላማዊ ዜጎችን በማዋከብ፣ በማፈን እና በማሸበር የሚታወቁ ቡድኖችን በመግለጫቸው በስም እየጠሩ ማጠቃለያ ሰጥተዋል፡፡
ይህ መግለጫ የተሰጠበት አውድ እና ፋይዳ ገንቢነት የሌለው ነበር፡፡ የያዛቸው ጉዳዮችም በሚገባ ተጢነው የተዘጋጁ አይደሉም፡፡ በመሆኑም መግለጫው በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ታሪካዊ እና ወዳጃዊ ግንኙትን አይመጥንም፡፡ ሁለቱ ሀገራት ባላቸው የጠበቀ ግንኙነት በጋራ ግንዛቤ በያዟቸው ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ምክክር ማድረግ የተለመደና ተጠናክሮ የቀጠለ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ግልፅ ምክክሮችን ለማድረግ ያላትን ዝግጁነት በተግባር አሳይታለች፡፡
ከላይ በተመለከተው መሠረት አገራችን ሰላምና ደህንነት ለማስፈን፣ ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥ፣ በሀገራችን ዲሞክራሲን ለማስፈን ስለምታደርጋቸው ጥረቶች እና በሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለመምከር ዝግጁ እንደሆነች በተጨባጭ አሳይታለች፡፡ በመሆኑም በመግለጫው የተካተቱት ስህተቶችን ለማረም እንዲቻል ሚኒስቴሩ አዲስ አበባ ከሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ጋር የሚሰራ ይሆናል፡፡
ከዚህም አልፎ መደበኛ የሆኑ እና የተለመዱ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አሰራሮች እና አካሄዶችን መከተል ተገቢ እንደሆነ ለዩናይትድ ስቴትስ ወገን ጥሪ ያቀርባል፡፡ እነዚህ አሰራሮች በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ የዲሞክራሲያዊ ሂደቶችን እና ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን በሚያከብር መንገድ እንዲከወኑ ለኤምባሲው ሀሳብ ሲቀርብ ቆይቷል፤ ይኸው እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመከባበር ላይ የተመሠረተ የሁለትዮሽ ምክክር እና ወዳጅነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ግንቦት 09 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ