የኔዓለም በየካቲት 12 ትምህርት ቤት ልበ ብርሃን ከነበሩት ማየት የተሳናቸው ተማሪ አንዱ ነበር።ነብሱን ይማረውና በወቅቱ እሱንና መሰሎቹ በሚገጥማቸው ችግሮች ዙሪያ ብዙ ጉዳዮችን አጫውቶኝ ስልነበር ዛሬ በግምት ከሰላሳ አምስት ዓመት በሁዋላ ታወሰኝ። በተለይ ስለ ሴት ዓይነ ስውራን ያጫወተኝ ችግር ዛሬም ድርስ የማይረሳኝ ነው። ዚህም በመነሻነት ቀዳማይ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ካስገነቧቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ እንደወርቅ የሚያበራ ታሪካቸውን የጻፉት አሁን መሆኑ ተሰማኝ።
በጋዜጠኛነት ሙያዬ የአማኑኤልን ሆስፒታል በመገኘት ተደጋጋሚ የምርመራ ሪፖርቶችን አቅርቤ ነበር።እግረ መንገዴንም ምርጥ ምርጥ የአማኑኤል ሆስፒታል የረዥም ጊዜ ታማሚዎችን ጓደኛ የማድረግና እድል አጋጥሞኝ እጎበኛቸው ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን የሪፖርተር ባልደረቦቼም ጭምር ልብ የሚነካና ለመስማት የሚከብድ የአስገድዶ መድፈር ታማሚ እንስቶች ላይ በሰራተኞች እንደሚፈጸም ሳይቀር በመረጃ ሪፖርት ማድረጋቸውን አስታውሳለሁ።
አማኑኤል ሆስፒታል ካገኘሁዋቸው ጓደኞቼ መካከል የምህንድስና በለሙያ ያላት አንድ እህት ደጋግማ ” ኢትዮጵያን አንገቷን አስቆረጣችሁ፣ አሳፋሪ ተውልዶች፤ ያታሪክ አተላዎች፤ ኢትዮጵያዬ …. ” እያለች የኢትዮጵያን የባህር አልባ መሆን እዳ በመንገብገብ ስሜት ስትነግረኝ የነበረውን ልረሳው አልችልም። እንደውም ” ማን ነው ዕብድ፣ ማንስ ነው ጤነኛ” በሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እንድጠይቅ አስገድዳኛለች። ይህ ጥያቄ እስካሁን መልስ አላገኘሁለትም።፡በነገራችን ላይ በርካታ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው።
የአማኑኤል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር አታላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን የቦርድ የበላይ ጠባቂ እንደሆኑ ነገሩኝኛ እንዲት እንደማገኛቸው ሳሰላ በሃዋሳ የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ እኔም ለስራ እሳቸውም ለስብሰባ ሄደው ተገናኘን።
በቀድሞው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ነጋ አማካይነት (እሳቸው ስብሰባው ላይ በተጋባዥነት ከነበሩት መካከል አንዱ ነበሩ) በሻይ የዕረፍት ሰዓት ከወይዘሮ አዜብ ጋር ቆመው ነበርና ጥሩ አግባብ ስላለን እሳቸውን ታክኬ ወይዘሮ አዜብን ለማናገር ቻልኩ።
ባጭሩ የጠየኳቸውን ጥያቄ ያቀረብኩላቸው ለጽሁፍ የሚበቃ እንዳልሆነ አስቀድመው ከነገሩኝ በሁዋላ ነበር። አማኑኤል ሆስፒታል ታማሚዎች “ታንክ ገደለን” ብለው ያሳዩኝን በመስከር ነበር። ክፍላቸው ውስጥ እንዳየሁት እነሱ “ታንከኛ” የሚሉት ቱሃን የተባለው ተባይ ነው።
ቱኳን ወይም ቱሃን ፍራሻቸውን፣ አንሶላቸውን ደም በድም አድርጎታል። የሚወስዱት መድሃኒት የማስተኛት ባህሪ ስላለው ችለውት እንጂ እንዳየሁት ከሆነ ቱካኑ …. ባጭሩ ይርመሰመሳል። መድሃኒት ቢረጭም ተመልሶ ይመጣል። እናም ለወይዘሮ አዜብ ይህንና ለጊዜው እዚህ ላይ ያላሳረፍኩትን ጉዳዮች አንስቼ መላ እንዲፈልጉ፣ እኔም አትሌቶችን ለማስተባበር እንደምሞክር ነግሬያቸው ግንባራቸውን አወዛውዘው ተለያየን። ዛሬ እንዲት ይሆኑ?፡መርጃው የለኝም። ወይዘሮ አዜብ ግን የለወጡት ነገር አልነበረም።
በተመሳሳይ ይህን ችግር ለአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ አጫውቼው ቢያንስ አንሶላ ስለሌላቸው ለጊዜው አንሶላና ጠንካራ መድሃኒት የሚረጭበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚቻልበትን ሁኔታ አንስቼ ደጋግሜ ነዳነጋገርኩት አልዘነጋም።በግሌ ፊሊት እየገዛሁ ጓደኞቼን እጠይቅ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዚህ ያለፈው ግን የግል ጉዳይ ነው።
ይህን ያነሳሁት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ያስገነቡትን የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ስመለከት ነው። ማየት የተሳናቸው ልበ ብረሃን የኢትዮጵያ ልጆች ለመማር ሲሉ የሚያልፉበት ፈተና ተመካች ያጣና አስታዋሽ ያልተገኘለ ነበር።
“ደባልነት ህይወታቸውን የበላባቸውን ቤት ይቁጠራቸው” ስትል ወደሁዋላ በትዝታ ሄዳ የምትናገረዋ ሃረግ (ስሟ የተቀየረ) ኢትዮጵያዊያን ማየት የተሳናቸውን ወገኖች የህይወት ውጣ ውረድ ታስረዳለች። ነገሩ እንዲህ ነው።
በኢትዮጵያ የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ያለው እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ ነው። በ1945 አጤ ሃይለስላሴ በስደት በነበሩበት ወቅት ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች የሚስተናገዱበትን ትምህርት ቤት ካዩ በሁዋላ ወደ አገራቸው ሲመልሱ ካስገነቡት የሰበታ መርሃ ዕውራን ትምህርት ቤት በቀር የሚታወቅ ነገር አልነበረም።
ንጉሱ የግል ይዞታቸውን ፈቅደው መርሃ እውራን ትንህርት ቤት ሰበታ ከተገነባ በሁዋላ በየደረጃው ሃዋሳ፣ በባኮ፣ ወላይታ፣ሻሸመኔ፣ ጊምቢና በቅርቡ ቢሾፍቱ በግል ከታነጸው አነስተኛ ትምህርት ቤቶች በዛ ሲባል አቅማቸው ከ1 እስከ 6 ድረስ ማስተማር ነው።ከዚህ በዘለለ በስም የሚጠራ ትምህርት ቤት የለም።ይህ ነው እንግዲህ የመከራው መነሻ።”ምንድን ነው መከራቸው” ለሚለው ጥያቄ …
የመጀመሪያውና አሳፋሪው መብት የሆነውን ትምህርት ለማግነት በልጅነት ለአቅመ አዳም ሳደርሱ አይነ ስውራን የአገር ስደት ሰላባ መሆናቸው ነው።ከሰባተኛ ክፍል በሁዋላ ለመማር አይነስውራን ዜጎች የሚያመሩት ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት እንደማንኛውም ተማሪ ነው።በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት የሌለ ከሆነ ወደ ከተሞች ይመጣሉ። ቤተሰብን ተለይተው በጋራ ወይም በደባልነት ቤት ተከራይተው ገና ጨቅላ እያሉ ይኖራሉ። በጋራም ሆነ በተናጠል ያገኙትን እየቀመሱ በጋር የሚኖሩት እነዚህ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ከሚገጥማቸው ፈተና ይልቅ በኑሮ ሳቢያ ወደ አልተፍለገ አቅጣጫ ማምራታቸው የጨቅላነት ፈተናቸው ህይወታቸውን የሚያመሳቅለው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በጨቅላልነት ጨቅላ ታቅፈው ስንቶች ለጎዳና እንደተዳረጉ መረጃው ያላቸው አስፍተው ሊያቀርቡት ይችላሉ።
“የደባልነት መከራ” ሳይፈልጉ መውለድ በቅድሚያ የሚጠቀስ ነው፤ ሃረግ በችግር ምክንያት ደባል ሆነው ትምህርት ለመግፋት ቀያቸውን ለቀው የመጡ ” የአገራቸው ስደተኞች” ሳይወዱና ሳያስቡት በጨቅላነታቸው እናት ሆነው ተሰናክለዋል።ከአንስተኛ ቀበሌዎች ወደ ትልቅ ከተማ አቅንተው ለመኪና አደጋ፣ ለአካል መጉደልና ለተመሳሳይ ችግር የተጋለጡ ጥቂት አይደሉም።የሞቱም ጥቂት አይደሉም።
ሃረግ በሰበታ መርሃ ዕውራን ትምህርት ቤት ስትማር ልብሷ ታጥቦ፣ ምግብ አማርጣ፣ የኪስ ገንዘብ እየተሰጣት፣ለሴትነት ንጽህና መጠበቂያ ቀርቦላት ነው የተማረችው። “አስበው” ትላለች ” ዓይነ ስውራን ከቤተሰብ ተለይተን፣ በማይመች ቤት ውስጥ፣ በጋራ እየኖርን፣ በማይመች መጸዳጃና መታጠቢያ ወዘተ የምናሳልፈው ህይወት ይታይሃል?” ትጠቃለች። ይህ ሁሉ የሚሆነው መብት የሆነውን ትምህርት ለማግኘት ሲባል በሚደረግ የአገር ውስጥ ስደት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማንኛውም ሰው የመማር መብት እንዳለው ይደነግጋል። ይሁንና ይህ መብት በተለይ በአዳጊ ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይከበር ይስተዋላል። ከነዚህ ምክንያቶች አንዱ ትምህርት ቤት የማግኘት እድል ነው። በተለይ ደግሞ አካለ ጉዳተኛ ሲሆን ፤ ፈተናው ይበልጥ ይከፋል።
በትምህርት ቤት የአየነ ስውራኑ ችግር እኔንና የኔ ዓለምን ያጎዳኘን ምክንያት ነው። እኔ የጽፍኩትን ማስታወሻ ወይም ከሰሌዳ ላይ እያየሁ የገለበጥኩትን አንብቤለት ካልጻፈ ምንም መረጃ አይኖረውም። እኔ ካልረዳሁት ትምህርት ቤት መጥቶ ተመለሰ ለመባል ካልሆነ በቀር ፋይዳም የለውም ነበር። ይህ የሁሉም አይነስውራን ችግር በመሆኑ እንዴት መፍትሄ ሊበጅ እንደሚችል እያሰበ ጭንቀቱን ያወራኝ ነበር።
ይህ ብዙ ምኞትና ልበ ብረሃን ባልደረባዬ በአደጋ ማለፉን ሰምቻለሁ። ዛሬ ዝናሽ ታያቸው ያስገነብሩትን ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አዳሪ ትምህርት ቤት ዜና ብስራት ስሰማ ያል ልባሙ ወዳጄ ታወሰኝ። ምነው ቀና ብሎ ባየው ስል ተመኘሁ።
ይህን የላቀ ትርጉም ያለው የትምህርት ቤት ግንባታ በመደገፋቸው ግርማዊት ሼካ ፋጢማ ቢንት ሙባረክን ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋና ሲያንስ ነው። ወይዘሮ አዜብ ለሁለት አስርት ዓመታት በተቀመጡበት ቢሮ፣ መቀመጫና ስልጣን ላለፉት ስድስት ዓመታት የተቀመጡት ዝናሽ ታያቸው እጅግ የላቅ ምስጋና ይገባቸዋል።
ሃረግ ዝናሽ ታያቸውን ለማመስገን ቃል ያጥራታል። በተለይ የሰበታ መርሃ እውራን ሲጎበኙ የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹ ሰው መሆናቸውን አሳይተዋታል። እሷ ችግሩን ስለምታውቀው ንግግራቸው ገብቷታል። ስለመጸዳጃ ሲናገሩ ትረዳቸው ነበር። “የገባው ያመስግናል።የገባቸው ያደንቃሉ።የገባቸው አድንቀው ይበልጥ እንዲሰራላቸው ይጠይቃሉ። የገባቸው ማስተዋላቸውን ጠብቀው የቀውረ ነገር ካለ ያሳስባሉ” ብላለች።
“ዛሬ አቅመ ደካሞችን ማዕከል ያደረገውና የሰው ተኮር ስራ ውጤት የሆነው የሼካ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት በመመረቁ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንኳን ደስ አለዎት ለማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ ባለቤታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።
የዚህን ድንቅ ህንጻና ሙሉ አገልግሎቱን አይተው ያደነቁ እንዳሉ ሁሉ ” ደግሞ ምን አስበው ነው፣ ብሩ ከየት መጣ?” ወዘተ በሚል የእርግማን ምድጃ ላይ የተቀመጡትን አስመልክቶ ” አልገባቸውም፣ ወይም እንዲገባቸው አይፈልጉም፣ ወይም እኛን ሆነው አላዩትም፣ ወይም እኛን ዜጋ አድርገው አያዩም፣ ወይም ስለ እኛ ፍጹም ደንታ የላቸውም ” ስትል ታሪክ አስተያየቷን ታበቃለች።
በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽ/ቤት የተገነባው የዐይነ-ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ምረቃ
በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ካድሬና ሰው ይለያይል የሚል እምነት አላቸው። ዝናሽ ታያቸው ፍጹም ሰው ናቸው። ንግግራቸው ሁሉ የሰው ነው። እንደካድሬ ነገር ከግራ ቀኝ እያላተሙ ብልጽግናን ሲያስተዋውቁና ሲያሞግሱ አይታዩም። አዜብ መስፍን ነብሳቸውን ይማራቸውና ባለቤታቸው እንደመሰከሩላቸው አንድበታቸው ትንታግ ካድሬ ናቸው። በንግግራቸው ሁሉ ” እብደ ኤህአዴግ፣ እንደ አጠቃላይ፣ እንደ ፓርቲያችን መርህ … እንደ ተገዳይነቴ፣ እንደ …” በሚሉ የካድሬ አጣቅሽ ቃላቶች በመጠቀም ይታወሳሉ። እናም “ሰውና ካድሬ” ይሏቸዋል።