የጅብ መንጋ ከፍተኛ የሆነ ስጋት በመፍጠሩ ነዋሪዎች በጊዜ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ፤ መጠጥ ቤቶችም ከምሽት 12:00 ሰዓት በኃላ እንዳይሰሩ ተከለከሉ።
በዲላ ዙሪያ ወረዳ የጅብ መንጋ በሰው ላይ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል። ከዚህ በፊት ባልተለመደው መልኩ በዲላ ዙሪያ ወረዳ አንዳንድ አከባቢዎች የጅብ መንጋ ጉዳት እያደረሰ ነው ተብሏል። ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
ግንቦት 11/2016 በሽጋዶ ቀበሌ ልዩ ቦታው ” ባፋኖ ” ተብሎ በሚጠራበት አከባቢ አንድ ግለሰን አምሽተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በጅብ መንጋ መበላታቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቡ ወደ ቤት ሳይመለሱ በመቅረታቸው ቤተሰቦች ፍለጋ በወጡበት ወቅት መንገድ ላይ ልብስ ፣ ጫማ እና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ፣ የቀሩ ስጋና አጥንት ማግኘታቸውን ተከትሎ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ነው ግለሰቡ በጅብ መበላታቸው የተረጋገጠው።
በአከባቢው ላይ ከፍተኛ የጅብ ጩኸት እንደነበረ ከአከባቢው ማህበረሰብ ማረጋገጥ መቻሉን ፖሊስ አመልክቷል።
የጅብ መንጋ እንቅስቃሴ ስጋት በመጨመሩ ፦
° ነዋሪዎች በጊዜ ወደየቤታቸው እንዲገቡ
° ነዋሪዎች ማንኛውም የማህበራዊ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኃላ በጊዜ ወደቤት እንዲመለሱ
° ገበያ ከሄዱም በጊዜ ወደ ቤት እንዲገቡ
° ልጆች የቤት እንስሳትን ሲጠብቁ ጥንቃቄ እንድያደርጉ ወደ ጫካ ውስጥ እንዳይሄዱ አሳስቧል። በተጨማሪ ማነኛውም መጠጥ ቤቶች እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ብቻ መስራት እንዳለባቸው ከዚህ ውጭ እንሆናለን ትዕዛዙን አናከብርም በሚሉት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቋል ሲል የዘገበው ቲክቫህ ነው።
በቅርቡ በስልጤ ዞን፣ በሀላባ ዙሪያ ፣ በሀዋሳ ዙሪያ የተራቡ ጅቦች ጉዳት ማድረሳቸውን የሚገልጹ መረጃዎችን ሰሞኑንን በተመሳሳይ ሲሰማ ከርሟል። ይህ ባልተለመደ ሁኔታ እየተከሰተ ያለው የጅብ መንጋ ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ ነው።