መንግስት ጥቃቱን ለማስቆም ምንም አይነት ተጨባጭ ርምጃ ካለመውሰዱም በላይ በጉዳዩ ዙሪያ አቋሙን በግልፅ አለማሳወቁ የህወሓት ታጣቂዎች ለሚፈፅሙት ጥቃት እና ለሚያደርሱት ጉዳት እንዲሁም ለራያ ህዝብ በህወሀት ለሚደርስበት ያልተቋረጠ መከራና ጉስቁልና ይሁንታ እንደሰጠ የሚያስቆጥር ነው
ከአብን የተሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል
የትህነግ ታጣቂዎች በራያ ወረዳወችና በአላማጣ ከተማና ዙሪያውን የሚገኙ አካባቢዎችን በወረራ በመቆጣጠር በንፁሃን የአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ እንደፈፀሙ፣ በብዙ አስር ሽህ የሚቆጠሩ ወገኖችን እንዳፈናቀሉ እና ከፍተኛ መጠን ያለው የህዝብ ሃብትና ንብረት እንደዘረፉና እንዳወደሙ፣ በገጠር ቀበሌወች የአርሶ አደሩን እህል ጭነው እንዳጓጓዙ ተረጋግጧል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የህወሓት ኃይል የፈፀመውን ጥቃት እና ያደረሰውን ጥፋት በማጋለጥ የፌዴራሉና የአማራ ክልል መንግስት የወራሪው ሃይል ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመለስ፣ ለፈፀመው ጥፋት ሃላፊነት እንዲወሰድ፣ ወደፊትም ተመሳሳይ ድርጊቶችን ከመፈፀም እንዲቆጠብ እና የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ በግልፅና በጥብቅ አሳስቧል።
ነገር ግን በሀገርና ህዝብ እንዲሁም በመንግስት ላይ ጭምር የጥላቻ ስሜትና የንቀት አባዜ የተጠናወተው ህወሓት ሰፊ ወታደራዊ ዝግጂት ሲያደርግ ቆይቶ ከቀናት በፊት በአፋር አካባቢዎች እና ባሳለፍነው ሳምንንተ መጨረሻ በአለማጣ ከተማ ላይ የወረራ ጥቃት በመክፈት ኗሪዎችን እየገደለ፣ ንብረታቸውን እየዘረፈ እና እያፈናቀለ ይገኛል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ታጣቂዎቻቸው ከአለማጣ ከተማ ዙሪያ አካባቢዎች መውጣታቸውን በማህበራዊ ድረ-ገፃቸው ላይ ያሳወቁት በአለማጣ ከተማ ህዝብ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ለማወጅና ለፈረንጅ ግብረ-አበሮቻቸው ይህንኑ ለማብሰር ጭምር ነበር!
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት ጥቃቱን ለማስቆም ምንም አይነት ተጨባጭ ርምጃ ካለመውሰዱም በላይ በጉዳዩ ዙሪያ አቋሙን በግልፅ አለማሳወቁ የህወሓት ታጣቂዎች ለሚፈፅሙት ጥቃት እና ለሚያደርሱት ጉዳት እንዲሁም ለራያ ህዝብ በህወሀት ለሚደርስበት ያልተቋረጠ መከራና ጉስቁልና ይሁንታ እንደሰጠ የሚያስቆጥር ነው። በተለይ የህወሓት አመራሮች ድርጊቱን የሚፈፅሙት በፌዴራል መንግስት ፈቃድ ተሰጥቷቸው መሆኑን ደጋግመው ከመግለፃቸው አኳያ ሲታይ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢና አደገኛ ጭምር ያደርገዋል። ይህም በመሆኑ በራያ አካባቢወች በህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ግድያ፣ መጠነ ሰፊ መፈናቀል፣ ውድመትና ዘረፋ መንግስት በዝምታ ያየው በመሆኑ፣ በህወሓት አመራሮች የሚደረግ የ”መንግስት ፈቅዶልን” ፕሮፓጋንዳ ዙሪያ ምንም ባለማለቱ ለሚጠፋው ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል።
በሌላ በኩል በአማራ ህዝብ ስም እታገላለሁ የሚሉ በርካታ ሀይሎች በዚህ ቀጠና ያለው የአማራ ህዝብ ለተደጋጋሚ ጥቃት ሲዳረግ ካለማውገዛቸው ባለፈ እየደረሰ ያለው የህዝብ መከራ እንዳይነገር መፈለጋቸው ምን ያህል የፖለቲካና የሞራል ዝቅታ ላይ እንዳሉና በህወሓት ተፅእኖ ስር እንደወደቁ ማረጋገጫ ነው። ይህ ችግር በህልውና ትግሉ ወቅት ጭምር የታየ ገመና ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በተደራጃ አግባብ በግልፅ እየተፈፀመ ይገኛል።
በተጨማሪ ለዚህ ሁሉ ችግር ባልተናነሰ ደረጃ ሃላፊነት የሚወስደው በተለይ በችግሩ ዙሪያ ላለው የግልፅነት ጉድለትና በማህበረሰቡ ላይ ለሚደረሰው ያልተቋረጠ ጥቃት የክልሉ መንግስት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
ስለሆነም:-
1).የፌዴራል መንግስት የህወሓት ታጣቂዎችን በወረራ ከያዟቸው አካባቢዎች ባስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ እንዲያደርግ እና በተደጋጋሚ ወረራ እየተፈጸመበት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጠው ህዝብ አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፤
2 ).የአማራ ክልል መንግስት ህዝቡን ከወረራና ጥቃት የመከላከል የሚበልጥ ኃላፊነት እንደሌለ በመገንዘብ ህዝቡን በማስተባበር ግንባር ቀደም ሃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን፤
3).መላው የአማራ ህዝብ የህወሓት ፖለቲካዊ ፍልስፍና እና የየዕለት ተግባራቱ በአማራ ህዝብ ህልውና ላይ አደጋ የሚጥል መሆኑን ለአፍታም ባለመዘንጋት በአንድነት እንዲቆም፤
4). አለማቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህብረሰብ በህወሓት አማካኝነች በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ያልተቋረጠ ግፍና ወረራ እያስከተለ ያለውን ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ቀውስ እልባት እንዲያገኝና ህወሀት ለፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ እንዲሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃልን