በምርጫ ዝግጅት የተጠመደው የአውሮጳ ሕብረት ሰሞኑን አዲሱን የሕብረቱን የስደተኞች ጉዳይ ደንብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። በተለይም ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞች አብዛኞቹም ከሶሪያና የአረብ ሃገራት ወደአውሮጳ ከገቡበት ከጎርጎሪዮሳዊው 2015 ወዲህ በመካከላቸው ለተፈጠረው አለመግባባት ስምምነቱ መፍትሄ ይሆናል በሚል ፖለቲከኞች ተስፋ አድርገዋል።
የአውሮጳ ሕብረት ምክር ቤት 27ቱ አባል ሃገራት ከዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ ለአስር ዓመታት ገደማ ሲደራደሩና ሲወዛገቡበት ቆይተዋል። በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት በአብላጫ ድምጽ ያጸደቁት አዲስ የስደተኞች ጉዳይ ስምምነት መሠረታዊ ማሻሻያዎችን ያካተተ ደንብና መመሪያ መሆኑ ተገልጿል። ምንም እንኳን አዲሱ የስደተኞች ደንብ በአባል ሃገራቱ አብላጫ ድምጽ ቢጸድቅም ሃንጋሪ እና ፖላንድ ግን ተቃውመዋል። አስር ሕጎችን ያካተተው የስደተኞች ጉዳይ ስምምነት የተሰኘው ይህ ደንብ፤ በዋናነት የስደተኞች ቁጥር መቀነስ፤ ደንቡ ለሚፈቅድላቸው የጥገኝነት አሰጣጥ ሂደቱን ማፋጠን እና የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኘውን ደግሞ ወደመጡበት የመመለስ እርምጃን ያካትታል። የአሶሲየትድ ፕረስ ጋዜጠኛው ሎረን ኮክ የሕብረቱ ሃገራት የደረሱበትን ስምምነት ትልቅ እርምጃ ነው ይላል።
«የአውሮጳ ሕብረት ሃገራት በስደተኛ ደንባቸው ላይ ትልቅ ማሻሻያ ነው ያደረጉት። እርምጃቸው ለዓመታት የዘለቀውን የፖለቲካ ሽኩቻ ያበቃል ተብሎ ይታሰባል። የስደት ጉዳዩ በፍጥነት ለአውሮጳ አቀፍ ምርጫ የምርጫ ቅስቀሳ ድምጽ ለማሰባሰብ የሚያስችል ነው።»
ደንቡ በነማን ላይ ተግባራዊ ይሆናል?
ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 3,5 ሚሊየን የሚሆኑ ስደተኞች ወደ አውሮጳ ገብተዋል። አንድ ሚሊየን የሚገመቱት ያለፈቃድ ወደ አውሮጳ ሕብረት ግዛት የገቡ ናቸው። አንድ ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ የይለፍ ፈቃድ ያላቸው፤ በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በባሕር ወደቦች በኩል የገቡ ሲሆን የመቆያ ፈቃዳቸው ቢያልፍም ወደመጡበት አልተመለሱም። ደንቡ ቁጥራቸው አነስተኛ በሆነው በቀሪዎቹ ላይ ተግባራዊ ይሆናል። እነዚህ ተሰዳጆች የአውሮጳ ሕብረትን ድንበሮች ያለፈቃድ ሲያቅርጡ እንደግሪክ፤ ጣሊያን ወይም ስፔንን በመሳሰሉ ሃገራት የተያዙ ናቸው። በአየርም ሆነ በየብስ የመጡትን ጥገኝነት ጠያቂዎች በገቡበት ሀገር በሰባት ቀናት ውስጥ ተመዝግበው በሕብረቱ ሰነድ ይካተታሉ። ከ20 በመቶ በታች ተሰዳጆች ከሚመጡባቸው ሃገራት የመጡት ለ12 ሳምንታት ያህል ጊዜ በሕብረቱ የድንበር አካባቢ ሃገራት እንደ ግሪክ፣ ጣሊያን፤ ማልታ፤ ስፔን፣ ክሮሺያ እና ቆጵሮስ በመሳሰሉ ሃገራት በመጠለያ ስፍራ ይቆያሉ። የትኞቹ ወደየሃገራቸው መመለስ እንዳለባቸውም የሚወሰነው እዚያው ነው።
የጥገኝነት ጥያቄ ሂደቱ ምን ይመስላል?
ጥገኝነት ጠያቂዎች መጀመሪያ በገቡበት የአውሮጳ ሕብረት ሀገር ማመልከትና ጉዳያቸው በባለሥልጣናት እስኪታይ እዚያው መቆየት ይኖርባቸዋል። ጥያቄያቸው ተቀባነት ካላገኘ ይግባኝ ለመጠየቅ ጊዜ ይኖራቸዋል። ዜጎቻቸው ጥገኝነት በብዛት ከማይሰጣቸው ሃገራት የመጡ አመልካቾች የጉዳያቸው ሂደት ሊፈጥን ይችላል። ተቺዎች ግን ይህ የጥገኝነት ሕጉን ያቃልላል እና ግለሰቦች ጉዳያቸው በተናጠል መታየት ይኖርበታል እያሉ ነው። ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ በየገቡበት ሀገር የጤና መድህን ዋስትና እና ትምህርት የማግኘት መብት ይኖራቸዋል። ተቀባይነት ያላገኙት ወደመጡበት እንዲመለሱ ትዕዛዝ ይተላለፍባቸዋል። ጋዜጠኛ ሎረን ኮክ፤
«ዋነኞቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስደተኞች አውሮጳ ሲደርሱ ማን ነው ኃላፊነት መውሰድ አለበት በሚል የሚነሳውን ውዝግብ ማብቂያ ያበጅለታል ብለው ተስፋ አድርገዋል። ሆኖም ግን ይህ በፍጥነት የሚከናወን አይደለም። የተሻሻሉት ደንቦች ተግባራዊ እስኪሆኑ ሁለት ዓመታት ይወስዳሉ። በዚህም ሁሉም ደስተኛ ነው ማለት አይቻልም።»
ምንም እንኳን አዲሱ የስደተኞች ደንብ መጽደቅ ለጥገኝነት ጠያቂዎች የተፋጠነ መልስ ለማግኘት ይረዳል ቢባልም፤ የሕብረቱ አንጋፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሳምንታት በኋላ ለሚያካሄደው ምርጫ ቀኝ አክራሪዎች ድጋፍ እንዲያጡ ለማድረግ የተጠቀሙት ስልት ነው የሚሉም አሉ። ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች የስደተኞችን በአውሮጳ ውስጥ መብዛት ለቅስቀሳ መጠቀማቸው የሕብረቱ ፓለቲከኞች የአውሮጳን የድንበር ቁጥጥር እንዲያጠናክሩ እና በስደተኞች ጉዳይም አባል ሃገራት የጋራ ኃላፊነት እንዲወስዱ ወደማድረግ እንዲሸጋገሩ ግድ ብሏል።
የሕብረቱ ስታትስቲክስ ተቋም ዩሮ ስታት፤ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር 1,14 ሚሊየን እንደሆነ ይገልጻል። ባለፉት ተከታታይ አራት ዓመታትም ቁጥሩ እየጨመረ መሄዱን ነው ተቋሙ ያመለከተው። በተጨማሪም ወደ አራት ሚሊየን የሚጠጉ የዩክሬን ስደተኞች በጎርጎሪዮሳዊው 2022 በአውሮጳ ሕብረት ሃገራት ተጠልለዋል።